ቅድስት

    ተክለማርያም ( ኪችነር )

በቅዱስ ያሬድ የዓቢይ ፆም ሳምንታት አሰያየም መሠረት ሁለተኛው ሳምንት ቅድስት ተብሎ ይጠራል እንዲሁም በዚሁ ሳምንት ዋናው ፆመ ኢየሱስ ይጀምራል:: ይኸውም “የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ አክብር” ዘጸ 20፥7 በማለት የሰንበትን ቅድስና እና ክብር መሠረት በማድረግ “እኔ ቅዱስ ነኝ እና ቅዱሳን ሁኑ” ዘሌ 19፥2 የሚለውን ቃል መርኅ እያደረገ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል የሚያደርስ መንፈሳዊ ዕድገት እንዲኖረን ክርስቲያኖችን የሚያሳስብ ነው:: የሰንበት ጌታዋ ልዑል እግዚአብሔር የሚከብርበት ቅዱስ ( ልዩ ) ቦታ ደግሞ የእኛ የክርስቲያኖች ቅዱሱ ሰውነታችን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሆኑ ቅ. ጳውሎስ ሲገልፀው እንዲህ ብሏል “ሰውነታችሁ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆኑን አታውቁምን” 1ቆሮ 6:19::     

          “ቅዱስ” የሚለው ቃል የተለየ ንጹህ እና እንከን አልባ እንዲሁም ቀደሰ (ለየ)ከሚል ግስ የመጣ ሲሆን ይህ በመንፈሳዊ ምሥጢሩ ሲቀመጥ እጅግ ጥልቅ የሆነው ቃል እግዚአብሔርን እና የእግዚአብሔር ሆነው የተለዩትን ሁሉ ለመጥራት በቀዳሚነት ይጠቀሳል:: እግዚአብሔር ከማንኛውም ዓይነት አማልክት የተለየ እና በባህርይው እርሱን የሚመስለው የሌለ ልዩ ሲሆን “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም “ዘዳ 33፥26 እንዲል የእግዚአብሔር የሆኑ ሁሉ ደግሞ ልዩ እና ቅዱስ ( የተለዩ እና የተቀደሱ ) ናቸው:: እነዚህ ቅዱሳን ከምን የተለዩ ናቸው ቢባል ደግሞ አሁንም ልክ እንደ አምላካቸው እነርሱን የሚመስላቸው የለም እና ከማንኛውም ምድራዊ ሃላፊ ጠፊ ነገር ወደው ፈቅደው ተለይተው ስጋቸውን እና ነፍሳቸውን ሃሳብ ልቦናቸውን በምልዓት ለእግዚአብሔር የሰጡ ናቸው:: እነዚህ ቅዱሳን ሰዎች ወይም ለእግዚአብሔር የተለዩ ህዝቦች ለእግዚአብሔር ለአምላካቸው ሲሉ ከተለዩለት የቅድስና ህይወት የሚነጥላቸው ምንም ዓይነት የዚህ ከንቱ ዓለም ሃሳብ: ስጋዊ ፈቃድና ምድራዊ ምኞት አይኖርም::  እናም የእምነት ቃል ኪዳናቸው እስከ ሞት ድረስም ቢሆን የፀና የታተመ ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ እንዳለው ” ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ ስለመንግስተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ”::  

     የክርስቲያኖች ቅድስና የሚጀምረው በጥምቀት ልጅነትን አግኝተው ቅዱሱን ቅብዓ ሜሮን በመቀባት የቅዱሱ የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ ቤተ መቅደስ ከሆኑበት ግዜ ጀምሮ ነው:: መፅሐፍ ቅዱስ እና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረንም ይኸው በዚህ የጥምቀት ዕለት የተጀመረው የቅድስና የእርምጃ ምዕራፍ በዘመነ ሐዋርያት “ጉዞ ወይም መንገድ ” እየተባለ ተጠርቷል:: በመጨረሻም ደቀ መዛሙርት በአንፆኪያ ክርስቲያን ከተባሉ በኃላ ይኸው የቅድስና መንገድ ወይም ጉዞ አቅጣጫውን ሳይቀየር መድረሻውን መንግስተ ሰማይ በማድረግ ፍፃሜ ወደሌለው ወደ ዘለዓለማዊው የመለኮት ክብር ተካፋይነት በፀጋ እያደገ ይኖራል:: 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ቅድስት የተባለችበት ምክንያት ቅድስና የባህርይው የሆነው የእግዚአብሔር የቅድስና ግምጃ ቤት ስለሆነች ነው : በዚህ ግምጃ ቤት ውስጥም የሚኖሩ ከሰው ጀምሮ እስከ ህንፃውና በውስጡም ያሉ ንብረቶች ድረስ ለእግዚአብሔር የተለዩ ቅዱሳን ናቸውና ቅዱስ መፅሐፍ ለእኛ ለክርስቲያኖች እንዲህ ይለናል

 ” እናንተ ግን ከጨለማ ወደ ብርሃኑ የጠራችሁ የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ : የንጉስ ካህናት: ቅዱስ ህዝብ : ለርስቱ የተለየ ህዝብ ናችሁ::” 1ጴጥ 2፥9

               እግዚአብሔር በነቢዩ ናሆም አድሮ “ፆምን ቀድሱ” ( ኢዩ 1፥14 ) እንዳለው እኛ ክርስቲያኖች ፆምን የምንቀድስበት መንገድ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሆነው በቅዱሱ ሰውነታችን እና በፆሙ ወራት በምናደርጋቸው ምግባረ ትሩፋቶች መሆኑን ልብ ይሏል:: እኛ ቅዱሳን ( የተለዩ ) የተባልን ክርስቲያኖች ፆማችን የተለየ ነው (የተቀደሰ) ነው የምንልበትም መንገድ ከሌሎች ዓለማዊ አፅዋማት እንዲሁም መንፈሳዊ መሳይ የተሳሳቱ አፅዋማት የተለየ ስለሆነ ነው::         “እኔ የመረጥኩት ፆም ይህ ነውን ?…ለጥል እና ለክርክር ትፆማላችሁ..”ኢሳ 58፥4 :- እንግዲያውስ ፆማችን ከላይ ነቢዩ ኢሳያስ ከተናገረው አሳዛኝ አፅዋማት መካከል የተለየ መሆን እንዳለበት ልብ ይሏል:-ነቢዩ በዚህ አላበቃም የተቀደሰውን እንዲሁም ልዩ እና የተወደደ የተባለውን ፆም ዓይነቱን ጭምር ነግሮናል ” የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ : እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ : ስደተኞችን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ: የቀንበርን ጠፍር ትለቁ ዘንድ :…”  ይለናል:: እናም እኛ ክርስቲያኖች ሁላችንም የቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን ልዩ እና ቅዱስ ፆምን በእግዚአብሔር ፊት አቅርበን መንፈሳዊ መንገድ ጉዞአችንን ወደ መንግስተ ሰማያት እንዲያደርግልን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን::

     ወስብሃት ለእግዚአብሔር::