የቶሮንቶ ንዑስ ማእከል በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልዩ የሕይወት ጉዞ መርሐ ግብር አካሄደ፡፡

የቶሮንቶ ንዑስ ማእከል በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልዩ የሕይወት ጉዞ መርሐ ግብር አካሄደ፡፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ካናዳ ማእከል በቶሮንቶ ንዑስ ማእከል አዘጋጅነት መነሻውን ከቶሮንቶ ደብረ ገነት አቡነ ተክለ ሃይማኖት አድርጎ ወደ ብራምፕተን ቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ተክላ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሕይወት ጉዞ በማድረግ፤ጉዞው ተተኪ ትውልድን ከማነጽና የጋራ ትስስርን ከማጠናከር አንጻር ከኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልምድና ተሞክሮዎች የቀረቡበት ልዩ መርሐ ግብር እንደሆነ ተጠቁሟል።

ከ150 ምእመናን በላይ የተሳተፉበት ይህ መንፈሳዊ ጉዞ ምእመናን ከቶሮንቶ ደብረ ገነት አቡነ ተክለሃይማኖት በመነሣት ወደ ብራምኘተን ቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ተክላ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተካሄደ ጉዞ ነው፤ከመነሻ ጀምሮ በመንገድ ላይ ተሳታፊ ምእመናን በመንፈሳዊ ትምህርት እና በመዝሙር ምስጋና እያቀረቡ ለ1 ሰዓት ተጉዘው ብራምፕተን ቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ተክላ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ በቤተ ክርስቲያኑ አባቶች አቡነ ማርቆስ እና አባ ሚካኤል አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን። አቡነ ማርቆስ ለምእመናኑ እንኳን ወደ እኅት ቤተ ክርስቲያናችሁ በሰላም መጣችሁ ስለመጣችሁ በጣም ደስ ብሎናል ለሁላችሁም የአባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትን ስዕል በስጦታነት አዘጋጅተናል ብለው መርሐ ግብሩን አስጀምረዋል። በመቀጠልም መርሐ ግብሩ በጸሎት ከተከፈተ በኋላ የቁርስ ፕሮግራም ተካሂዷል። ከቁርስ መርሐ ግብር በኋላ ምእመኑን በእድሜ ከፋፍሎ ለማስተማር እንዲያመች በ3 ቡድን (ሕጻናት፣ወጣቶች፣ወላጆች) በማድረግ የቀኑ መርሐ ግብር ተከናውኗል።

የመጀመሪያው ቡድን የአዋቂዎች (ወላጆችን አባት እናት ወንድሞች እኅቶችን) የያዘ ሲሆን በዚህ ቡድን ላይ ምክረ አበው በክርስቲያናዊ የ‍ዕለት ከዕለት አኗኗር እና ክርስቲያናዊ የልጆች አስተዳደግ ላይ ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን እና ከኢትዮዽያ ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር ውይይት ጥያቄ እና መልስ ተካሂዷል። ሁለተኛው ቡድን ወጣቶችንና ታዳጊዎችን የያዘ ነበር (ከ 9 ዓመት እስከ 21 ዓመት) በዚህ ክፍል ላይ ወጣቶች እና
ታዳጊዎች ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆናት ጋር በወጣትነት እና ክርስቲያናዊ ሕይወት ላይ ትምህርት ውይይት እንዲሁም የጥያቄና መልስ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

በ3ተኛው ቡድን ሕጻናት ከ3 አመት እስከ 9/10 ዓመት የተሳተፉበት ሲሆን ሕጻናቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የቅዱስ ዳዊትን ታሪክ የተማሩ ሲሆን መዝሙር ፣ጥያቄና መልስ ፣ቤተ ክርስቲያኒቱ ተተኪ ትውልድን ለማነጽ ሕጻናት ልዩ የማስተማሪያ ዘዴ በመኖሩ ሕጻናት የተለያዩ መንፈሳዊ ጨዋታዎችን እየተጫወቱ ተምረዋል። ከዚያም በጉዞው የተሳተፉት ሁሉ የብራምፕተን ቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ተክላ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካቴድራል የጉብኝት መርሐ ግብር አካሂደዋል። በየመርሐ ግብራት መካከል ዝምሬዎችና መልእክቶች ቀርበዋል፡፡ ስለ ጉባኤው አጠቃላይ ከግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያለውን ትስስርና አንድነትን ብሎም አጠቃላይ መርሐ ግብሩን በተመለከተ ከኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ወጣት አገልጋዮች፣ ከአባቶች ካህናት፣ከወላጆች፣ከወጣቶች በጣም ገንቢ የሆኑ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም የጉባኤው መርሐ ግብር በጸሎት ተዘግቶ ጉዞ ወደ ቶሮንቶ ደብረ ገነት አቡነ ተክለሃይማኖት የተካሔደ ሲሆን በመንገድ ላይ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ካናዳ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤ ስለ ቶሮንቶ ንዑስ ማእከል አገልግሎት በማኅበሩ ወንድሞች እና እኅቶች ገለጻ ተደርጓል፤ከዚያም ምእመናን በመዝሙር እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደ ቶሮንቶ እንደደረሱ፤የጉዞው መርሐ ግብር በቶሮንቶ ደብረ ገነት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በጸሎት ተጠናቋል።

አምናለሁ አትቀሪም

አምናለሁ አትቀሪም

/በ ሃይማኖት ተካ/

የታደለ ድንጋይ በአምላክ ተቀድሶ ታቦት ያሳድራል፤
ስሙ ተቀይሮ እየተሳለምነው ከብሮ ያስከብራል፤
የረገጥነው አፈር የተደገፍነው ግንድ ልጅሽ ከወደደ፤
ዘግነን ተቀብተን ቆርጠንም አጭሰን መዳኛ ይሆናል
እሱ ከፈቀደ::

ርግበ ጸዓዳ ሀገረ ክርስቶስ ቤተ ሃይማኖቴ፤
የመማጸኛዬ ቃልና ቀለሜ የምታረቅብሽ ርቱዕ አንደበቴ::
ነያ ሠናይት ጎትተሽ ውሰጂኝ አቅርቢኝ ከደጁ
ነያ ዕፀ ሕይወት ከበሩ አዝልቂኝ አስዳሺኝ በእጁ::
እንደተራራቁት እንደኒያ ድንጋዮች እንደታነጹብሽ፤
እጠብቅሻለሁ አንድ እስክታደርጊኝ አማልደሽ ከልጅሽ::
አምናለሁ አትቀሪም. . .

እንደሚለመልም ሰም እሳት ሲያቀልጠው፤
በስምሽ ተጠርቶ ድንጋዩ ተስቦ በእጅ በታነጸው::
ከምሥጢር እንዳንጎድል በቤተ መቅደሱ ተሰብስበንበት፤
በተሠራልን ልክ አውቀን እንድንኖር እንድንበቃበት፤
ነይ እመብርሃን ቦዶነታችንን ፍቅርሽን ሙይበት::
አምናለሁ አትቀሪም::

‹‹እንደተናገረ ተነሥቷልና በዚህ የለም›› (ማቴ. ፳፰፥፮)

እንኳን ለበዓለ ትንሣኤ አደረሳችሁ!

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን                                           ክርስቶስ ከሙታን ተነሣ

በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን                                            በታላቅ ኃይልና ሥልጣን

አሰሮ ለሰይጣን                                                          ሰይጣንን አሠረው

አግዐዞ ለአዳም                                                         አዳምን ነጻ አወጣው

ሰላም                                                                            ሰላም

እምይእዜሰ                                                                     ከእንግዲህ

ኮነ                                                                                  ሆነ

ፍስሐ ወሰላም                                                                   ደስታና ሰላም

ሆሳዕና

ኒቆዲሞስን ተመልከቱ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

« ኒቆዲሞስን ተመልከቱ»

/በቀሲስ አዳነ ገቢ/

መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወት አብነታቸው ምሳሌ የሚሆኑንን እንድንመለከታቸው ፤ከፍ ሲልም እንድንመስላቸው ያስተምረናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በፊል 3፥17 « እኛ እንደምሳሌ እንደምንሆንላችሁ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ።» እንዳለ በዚህች አጭር መልእክት ለክርስቲያኖች ታላቅ አብነት የሚሆን ከጥንካሬውም ከድክመቱም የምንማርበት ኒቆዲሞስን እንመለከታለን። የምናስተውልበትን አእምሮ ለሁላችን ያድለን አሜን፡፡

ኒቆዲሞስ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ድል ማድረግን ወይም አሸናፊነትን ያመለክታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ የዚህን ሰው ስም ባነሣበት ስፍራ ሁሉ ‹አስቀድሞ በሌሊት መጣው› የምትል ቅጽል ያስቀድማል፡፡ ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ብቻ ሳይሆን የፈሪሳውያን አለቃ በሹመቱ የአይሁድ ሸንጎ /synagogue/ አባል፣ በሀብቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለ ባለጸጋ፣ የኦሪት መምህር ብቻ ሳይሆን የኦሪት ምሁርም ነበር፡፡ በእርሱ ደረጃ የነበሩ ታላላቅ የአይሁድ ምሁራን መንፈሳዊ ስልጣናቸውና ሹመታቸው የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ረስተው በሕዝቡ ላይ የሚመጻደቁ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው እውቀትን የሚገልጥ እውነተኛ አምላክ፣ የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም ሲገለጥ የአይሁድ ምሁራን የጌታን መገለጥ አልወደዱትም፡፡ የእርሱ ትህትና የእነርሱን ትዕቢት የሚያጋልጥ ነበርና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሄዱትን ሁሉ ይነቅፉ ይከስሱ ነበር፡፡

ኒቆዲሞስ ግን ከእነዚህ ከፈሪሳዊያን መካከል የተገኘ ልዩ ምሁረ ኦሪት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ራሱን ለእውነት ልቡን ለእምነት አዘጋጅቶ ከሁሉ ቀድሞ በሌሊት ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ ከእነዚህ ፈሪሳዊያን ወገን ተለይቶ እንደ አባታችን አብርሃም ወደ ጽድቅ መንገድ የተጠራ ነው፡፡ ሹመት እያለው ሁሉ ሳይጎድልበት በዙሪያው የነበሩት ከእኛ በላይ ማን አዋቂ አለ የሚሉ ከእውነት ጋር የተጣሉ ጌታችንን የሚያሳድዱ በእርሱም የሚቀኑና ጌታችንንም ለመግደልም ዕለት ዕለት የሚመክሩ ሁነው ሳለ ኒቆዲሞስ ግን እውነትን ለማወቅ እልቅናው ሳይታሰበው ከአካባቢው ጋር መመሳሰልን ሳይመርጥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሊማር በሌሊት መጣ፡፡የዚህን ታላቅ አባት ሕይወት በሦስት ክፍሎች ከፍለን እንመለከተዋለን፡፡

ሀ. የኒቆዲሞስ የቀደመ ሕይወት

ለ. ወደ ክርስቶስ ከመጣ በኋላ

ሐ. ክርስቶስ በተሰቀለበት ጊዜ

1. የኒቆዲሞስ የቀደመ ሕይወት፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ ያደረገውን ተአምር ተመልክተው ብዙ ሰዎች በስሙ አምነው ነበር፡፡ ታዲያ ይህንን ምልክት ተከትለው ካመኑበት ብዙ ሰዎች አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ይህ ሰው በጌታችን ቢያምንም ባመነበት ወቅት እምነቱን በልቡ ብቻ ይዞ አቆይቶ ነበር፡፡ ከዚያም በማታ ወደ ጌታችን መጣና “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን” አለው፡፡ (ዮሐ 3፥2) ኒቆዲሞስ ጌታችንን እግዚአብሔር በረድኤቱ ተአምራትን እንዲያደርጉ ከሚያስችላቸው ጻድቃን እና ነቢያት ለይቶ አላየውም ነበር፡፡ ንግግሩም ከእርሱ ጋር ምልክቱን አይተው አምነው ከነበሩት ሰዎች ቁጥር መሆኑን በሚያሳይ መንገድ “እናውቃለን” የሚል የብዙዎች ወኪልነት ንግግር ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር እንግዲህ አምላካችን በዝርዝር ያስተማረው፡፡

ኒቆዲሞስን እንዲህ በሌሊት ያስመጣው ምንድን ነበር? ክርስቶስን በቀን በአደባባይ ሊያናግረው አይችልም ነበር? እሱ እንደሆነ በሔደበት መንገድ የሚለቀቅለት የአይሁድ አለቃ ነውና ጌታችንን ለማግኘት ሰዎች አገዱኝ ሊል አይችልም፡፡ ይህ እንግዲህ የኒቆዲሞስ የመጀመሪያው የክርስትና ደረጃ ነበር፡፡ እሱ አምላካችንን ስላደረገው ተአምር ሊያደንቀው ፈልጓል “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” ብሎ አመስግኖታል ፤ ሊከተለው ግን አልፈለገም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከጌታችን ጋር ሆኖ ሰዎች እንዲያዩት አልፈለገም፡፡ የጌታ ተከታይ ደቀ መዝሙር ሆኖ መታሰብ አልፈለገም ፤ ጉዳዩ ክብሩን የሚነካበት መሰለው፡፡ የተማረ ነውና ‹ገና ይማራል እንዴ› ብለው እንዳይንቁት ለክብሩ ሳሳ ፣ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆኖ መታየት በዚያን ወቅት የሚያስከብር ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህ ፈራ ተባ እያለ በጨለማ መጣ፡፡ በሌሊት መምጣቱን በሁለት መንገድ እንማርበታለን አንደኛ ቀን ቀን በብዙ ኃላፊነት ውስጥ የነበረው ኒቆዲሞስ ሌሊቱን ለበለጠ እውቀት ለተሻለ ክብር ይጠቀምበት እንደነበር እኛም በሌሊት መትጋት በርትተን ከምክንያት ርቀን ወደ ቤተክርስቲያ መገስገስ በጸሎት መበርታት እንዳለብን እንማራለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሌሊቱን ጊዜ የመረጠበትን አይሁድን መፍራት ከሕይወታችን መወገድ ያለበት በምንም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን በክርስትናችን በአገልግሎታችን ልናፍር እንደማይገባ፣ በክርስትናችን የቱንም ያህል መገለል ቢደርስብን በአኮቴት ልንቀበለው እንደሚገባ ከድካሙም እንማራለን፡፡

2. ወደ ከርስቶስ ከመጣ በኋላ፡- በእውቀት ጎልምሶ ታላቁን ትምህርት ምስጢረ ጥምቀትን ከምንጩ ተምሮ በሒደትም ከአይሁድ ፍራቻ በመውጣት ምስክርነትም ጭምር ሲሰጥ እንመለከተዋለን፡፡ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህንን የኒቆዲሞስን ምስክርነት ሲጽፍ “ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው። እነርሱም መለሱና፡- አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።” በማለት ገልጾታል፡፡ (ዮሐ 7፥50-52) እንግዲህ ኒቆዲሞስ ያለፍርሐትና ያለ ኀፍረት በካህናቱ ፊት እውነትን መስክሯል፡፡ እኛም በዚህ ክህደት በበዛበት እውነትን መመስከር ወንጀል በሆነበት ዘመን ምስክር ሆነን መገኘት እንዳለብን ያስተምረናል፡፡

3. ክርስቶስ በተሰቀለበት ጊዜ፡- ኒቆዲሞስም ከጌታችን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ለመኖር የበቃ አባት ነው፡፡ የሃይማኖቱ ጽናትም በተግባር የተፈተነ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የአይሁድን ድንፋታ ሳይፈራ “እሱን ያገኘ ያገኘኛል” ሳይል በድፍረት የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን በንጹሕ የተልባ እግር በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር፣ በጌቴሴማኒ የቀበረ ሰው ነው፡፡ (ዮሐ 19፥ 38) . ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ የጌታችንን ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው ክቡር ሥጋውን ለመገነዝ የበቃ አባት ነው፡፡ የጌታችንን ክቡር ሥጋ ገንዘው ሲቀብሩም በጸናች የተዋሕዶ እምነት ጌታ እንደገለጠላቸው “ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት” የሚለውን ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ዕለተ ምጽአት የክርስቶስን ሥጋና ደም ስታዘጋጅ የምትጠቀምበትን ጸሎት እስከ ፍፃሜው እየጸለዩ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ ምስጢረ ጥምቀትን ከጌታ እንደተማረ፣ የሐዲስ ኪዳንን የምስጢራት አክሊል ምስጢረ ቁርባንንም እንዲሁ ተማረ፡፡ ይህንንም በሚመለከት ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ አብሮት ይቀድስ የነበረውን ንፍቅ ካህን በባረከበት አንቀጽ “በዚህ ምሥጢር እየተራዳኝ ከእኔ ጋር ያለ ይህንን ካህን እርሱንም እኔንም ሥጋህን እንደገነዙት እንደ ዮሴፍና እንደ ኒቆዲሞስ አድርገን” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 115) ብሏል፡፡

እኛም እንደ ኒቆዲሞስ፡ በዕውቀታችን፣ በስልጣናችን፣ በሀብታችን፣ ባለን ማንነት ሳንታበይ ራሳችንን ዝቅ በማድረግ የእውነተኛ አባቶችን ትምህርት፣ ምክርና ተግሳፅ ልናዳምጥ በተግባርም ልናውለው ይገባናል፡፡የያዝነውን እውነተኛ እምነት በማጠንከር በሃይማኖት ልብ የቤተክርስቲያንን ምስጢራት በትህትና ለመሳተፍ ልቡናችንን ከፍ ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ምድራዊ ሐሳብ ሳያሰናክለን በቀንና በሌሊት ወደ አማናዊት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ለምስጋና እና ለመማር መሔድ ይኖርብናል፡፡ እውነትን በማድረግ ሕይወት የሚገኝበትን ቃለ እግዚአብሔርን ያለኀፍረትና ያለፍርሐት ልንመሰክር ያስፈልጋል፡፡ ክርስትና ምድራዊ ስጦታና ተአምራት በሚገለጥበት በገሊላ ባሕር አጠገብ ብቻ ሳይሆን መከራና ስቃይ ባለበት በቀራንዮም መገኘትን ይጠይቃልና በፈተናና በመከራ ጊዜም ቢሆን በእምነት ልንጸና የበለጠም በመታመን ልናገለግል ይገባል፡፡ ከኒቆዲሞስ ሕይወት ተምረን በሃይማኖት እንድንጸና የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

አሜን!

ደብረ ዘይት