“ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” ኢሳ 7÷14

++ ፈኑ እዴከ እምአርያም
አድኅነኒ ወባልሐኒ እማይ ብዙኅ
ወእምእዴሆሙ ለደቂቀ ነኪር መዝ ፻፵፫፥፯ ++

ትርጉም፦

እጅህን ከአርያም ላክ
ከብዙ ውኃም አድነኝ
ከባዕድ ልጆችም አድነኝ

ምሥጢር፦

ረድኤትህን ከአርያም ላክ አንድም ልጅህን በሥጋ ላክ ከብዙ ጦር/ሠራዊት አድነኝ አንድም ከፍትወታት እኩያት ከኃጣውእ ርኩሳት ከፍዳ ከመከራ ነፍስ ፈጽመህ አድነኝ ከነናምሩድ ከነሳኦል ልጆች እጅ አድነኝ አንድም ከዲያብሎስ ወገኖች ሥልጣን አድነኝ:: እጅ/ክንድ ከአካል ሳይለይ የወደቀ እንደሚያነሣ፤ የራቀ እንደሚያቀርብ፤ የቀረበ እንደሚያርቅ፤ የተበተነ እንደሚሰበስብ የወደቀ አዳምን አንሥቷል የራቀ አዳምን አቅርቧል የተበተነውን መንጋ ሰብስቧልና እጅህን ላክልን እያለ ዳዊት የተማኅፅኖ ጸሎት አቀረበ።


አንድም የሰው ኃይሉ በክንዱ እንዲታወቅ የአብም ኃይሉ በወልድ ታውቋልና እጅህን ላክ አለ።
አንድም ኃጥአንን ሑሩ እምኔየ ብሎ ያርቅበታልና ጻድቃንን ንዑ ኀቤየ ብሎ ያቀርብበታልና ፈኑ እዴከ አለ።

መጣ ስንልም የሌለበት ስፍራ ኖሮ ወዳልነበረበት ዓለም ወይም ቦታ መጣ ማለታችን አይደለም። ሁሉ በመሐል እጁ የተያዘ ነውና የሌለበት ስፍራ የለምና ካለበት ዓለም ወዳለበት ዓለም መጣ እንላለን።

በዘመናችን ካሉ ሊቃውንት አንዱ ሊቅ እንዲህ ብለዋል
“ሰው በያዘው ነገር ላይ መቀመጥ አይችልም በያዘው ዓለም ላይ መቀመጥ የታቸለው እግዚአብሔር ብቻ ነው” ሰማይ ዙፋኑ ምድር የእግሩ መረገጫ ሲሆኑ ተወስኖ ታይቷልና።

ምሥጢሩ የዚህን ያህል ጥልቅና ረቂቅ ከሆነ በምሥጢረ ሥጋዌ ዙሪያ አምላክ እንዴት ሰው እንደሆነ ሰውም እንዴት አምላክ እንደሆነ ተመራምሬ እደርሳለሁ ማለት የውቅያኖስን ውኃ በእንቁላል ቅርፊት ቀድቶ ለመጨረስ እንደመሞከር ነው።

የዕለቱ ወንጌል፦ ዮሐ ፩፥፵፬ – ፍጻሜ

ቅዳሴ፦  ዘእግዚእነ

ከወንጌሉ ንባብ በጥቂቱ፦

የቅዱስ ፊልጶስ ጥሪና ምስክርነቱ ጌታችን ፊልጶስን ተከለኝ ብሎ ካስከተለው በኋላ ያለመዘግየት ስለተከተለው ወይም እንዲከተለው ስለፈቀደለት አምላክ ለመመስከርና ሌሎችን እሱ ወደተጠራበት ለመጥራት ጊዜ አላባከነም። ሙሴ በኦሪት ነቢያትም በትንቢት መጽሐፍ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘው ብሎ ለናትናኤል ምስክርነቱን በመስጠት ወደዚህ ሕይወት እንዲመጣ ጠርቶታል።
እዚህ ላይ የዮሴፍ ልጅ የሚለው ኃይለ ቃል በትርጓሜያችን የተቃና መሆኑን ልብ ይሏል። አይሁድ ባለማወቅ የዮሴፍ ልጅ የሚሉት፤ ሙሴ በኦሪቱ የጻፈለት፤ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት፤ እኛም አምላክ ወልደ አምላክ ብለን የምናምንበት የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘው ብሎ ለናትናኤል እንደመሰከረለት ተብራርቷል። ዮሴፍ ስንኳን በገቢር በሐልዮ ይህን ነጥብ አያውቀውም። ይህም በመልአኩ ቃል ተረጋግጧል። “ይህ ሁሉ የሆነው ከእግዚአብሔር ዘንድ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው” በማለት ዮሴፍ የተጨነቀበትን ሐሳብ ሲያርቅለት እናያለን። ማቴ ፩፥፳፤


በነቢይ የተነገረውም “ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” የሚለው ነው።
የሚሰመርበት ነጥብ፦ “ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች” የሚለው ነው። ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቀር በድንግልና የፀነሰች ፈጽማ የለችም አትኖርምም። ይህም ከሆነ ዮሴፍ አባት የተባለው ወይም ሊባል የቻለው አሳዳጊ በመሆኑ ብቻ እንደሆነ ንጹሕ ሕሊና ያለው ሰው የሚረዳው እውነት ነው። ስለ ዮሴፍ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ጻድቅ ስለሆነ” በማለት ነው። ጻድቅ ከሆነ ደግሞ የእግዚአብሔርን ሥራ አይዳፈርም አይጋፋምም። በረድኤት የተገለጠባትን ደብረ ሲና እንኳ ማንም ሊነካት አልደፈረም። በኩነተ ሥጋ የተገለጠባትን አማናዊቷን ቤተ መቅደስ ጻድቅ ተብሎ የተገለጠው ዮሴፍ እንዴት ሊዳፈር ይችላል? ቴዎዶጦስ የተባለ ሊቅ ነገረ ሥጋዌን በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል። “ወህየንተ እድ ዘዝየ ዘይለክዖ ለቃል በጽሒፍ አእምር በህየ ከመ እግዝእትነ ድንግል ማርያም ይእቲ ዘወለደቶ ለቃል በሥጋ” ብሏል። ወደአማርኛ ሲመለስም “በጽሕፈት ጊዜ ቃልን ስለሚጽፈው እዚህ ስላለ እጅ ፈንታ በወዲህ ቃልን በሥጋ የወለደችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሆነች እወቅ” ማለት ነው። ሃይ አበው ፶፫፥፳
ሊቁ ይህን የተናገረበት ምክንያት፦
ከልብ የተገኘ ቃልን ለመጻፍ ብንፈልግ በልባችን ያለውን ቃል በሠሌዳ ስንቀርፀው ቃል አካላዊ በመሆን ይገለጣል። ይሁን እንጂ በጽሑፍ የተገለጠው ቃል በጽሑፍ ከመገለጡ በፊት በልብ ህልው እንደነበረ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ ማርያም ከመገለጡ በፊት በአብ ህልው እንደነበረ ማስረጃ ነው። የአምላካችን ልደት በእንዲህ ዓይነት ምሥጢር የተከናወነ መሆኑን ብርዕና ቀለም ሆና ያላየነውን እግዚአብሔርን እንድናየው ያደረገችን እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት ሲል ሊቁ ቴዎዶጦስ በምሳሌ አስተማረን።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ፦
“አንተሰ ኦ ብእሲ ኢታስተንዕስ መጠና ለሃይማኖት ቅድመ አዕይንቲከ – አንተ ሰው የሃይማኖትን መጠን በልቡናህ አታሳንስ አንድም አዋርደህ አትያት” ብሏል። ድር. ዘዮሐ አፈ ወርቅ ፱፥፺፭

ለእኛ ያልተረዳን ሁሉ ስሕተት፤ እኛ ልክ ነው ያልነው ሁሉ እውነት ሊሆን አይችልም። የእኛን ስሜት ብቻ ተከትለን በሄድን መጠን የሃይማኖታችንን ምሥጢር እያሳነስነው ልንሄድ እንችላለንና።

አዲስ ዓመት – ሐዲስ ሕይወት

ጳጉሜን ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

እንኳን ለዘመነ ማርቆስ አደረሰን!

ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ወቅቶችን ያፈራርቃል፤ ዝናብን ያዘንባል፤ ፀሐይን ያወጣል፡፡ ይህን ማድረጉ ለሰው ሁሉ ነው እንጂ በእርሱ ለሚያምኑ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ግን ለሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር የተሰጠ (የሚሰጥ) መክሊት ነው፡፡ የጊዜያዊውን ፀሐይ መውጣት፤ ዝናቡን መዝነብ ተመልክቶ ዘለዓለማዊ የምትሆን የጽድቅ ፀሐይ እንድትወጣለት፤ አምላካዊት የምትሆን የምሕረቱ ዝናብም በሕይወቱ እንድዘንምለት በእውነት የሚናፍቅና ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው በተሰጡት መክሊቶች ያተረፈ ሰው ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ዕድሜ ተሰጥቶት፤ የወቅቶች መፈራረቅ፤ የፀሐይ መውጣትና የዝናማት መዝነምን እንደ ሕይወቱ የመጨረሻ ግብ አድርጎ በምድር ላይ የሚኖር፤ ማለትም በዚህ ጊዜያዊ ዓለም የተዋጠ ሰው እግዚአብሔርን አያስብም፤ ጽድቁንም በእርሱም የሚገኘውን ሐዲስ ሕይወት አይናፍቅም፡፡ ይህ ደግሞ ከሕይወት መስመር መውጣት ነው፡፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ የሕይወትን አዲስነት ካልያዝንበት አዲሱ ዓመት ጥቅሙ ምንድነው? ለዚህም ነው ከኀጢአት ዕርጅና ወጥተን አዲስ የምንሆንበትን ንስሐን ያስተማረንን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ማሰባችን፡፡ ሰው ለንስሐ የሚገባ ፍሬ የማያደርግ ከሆነ ዓመቱ ብቻውን እንዴት አዲስ ይሆናል? 

ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆኑ ምክንያት ለሰው የጠፋበትን ሰውነት (ሰው መሆንን) ዳግም ለመስጠት ነው፡፡ ሐዲስ ሕይወትን ጸጋ አድርጎ ለመስጠት መድኅን ክርስቶስ በሥጋ ወደ እኛ መጣ፡፡ መጥቶም የመጀመሪያው ትምህርቱ ያደረገው ንስሐን ነው፡፡ ያለ ንስሐ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አይቻልምና፡፡ የሕይወት ባለቤት የሆነ እግዚአብሔር አዲስ ሕይወትን የሚሰጥ ወደ እርሱ በንስሐ ለቀረቡት ነውና፡፡ ይልቁንስ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር በመተው አዲሱን ሰው (ክርስቶስን) በሃይማኖትና በምግባር ለሚለብሱት አዲስ ሕይወት ጸጋ ሆና ትሰጣዋለች (ቆላ. 3፥9)፡፡ አዲስ ዓመትን ስንታደል በሐዲስ ሕይወት ለመመላለስ መፈለግና መናፈቅ አለብን፡፡ በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር ከተቀበርን ከክርስቶስ ጋር በሐዲስ ሕይወት እንደምንኖር ዳግመኛ ይህ የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ያስተምረናል (ሮሜ 6፥4)፡፡

ዛሬ አዲስ ዓመት አድርገን የምናከብራት ቀን፤ በብሉይ ኪዳን የተቀደሰች ቀን መሆኗ የተነገረላት፤ እስራኤል መሥዋዕትን የሚያቀርቡባት፤ መለከት የሚነፋባት የተባረከች ቀን ናት፡፡ እስረኤል ይህችን ቀን ያከብሩ ዘንድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታዘዋል (ዘሌ 23፡ 24-25፤ ዘኁ 29፡ 1-2)፡፡ የምስጋና ዝማሬዎችም በዚህች ቀን ይቀርቡባታል፡፡

ለእኛ ለክርቲያኖችም ይህ ቀን እውነተኛውን ምስጋና የምናቀርብበት ዕለት ነው፡፡ ዘመናት የሚሰጡን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ሆነን እንድንኖርባቸው በመሆኑ አዲስ ዓመትን ስንታደል የምናተርፍበትን መክሊት የታደልን አድርገን መረዳት ይገባናል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብም መሠረታዊው ጉዳይ ንስሐን መያዝ ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ እንደሚስተምረን የንስሐን ፍሬ ማድረግ ይገባናል፡፡ ለአይሁድ አብርሃም አባት አለን ብላችሁ እንደምትሉት አይደለም ብሎ አስተምሮ ነበር፡፡ ዛሬም እኛ ተጠምቀናል፤ ኦርቶዶክሳውያን ነን ማለታችን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ፍቅርን ይዘን በንስሐ ወደ መድኅን ክርስቶስ ብንቀርብ ሕይወታችን በጸጋ እና በጣዕም የተመላች ትሆናለች፡፡ አምላካችን በአዲሱ ዓመት ወደ ሐዲስ ሕይወት ያስገባን ዘንድ ቸርነቱን ያድርግልን፡፡ አሜን!

ፍሬውን ለመብላት ሥሩን ውሃ ማጠጣት

/ሊቀ ጠበብት ማኅቶት የሻው/

> ፍሬውን ለመብላት ሥሩን ውሃ ማጠጣት

ይህ በምሳሌነት የቀረበ የአንድ ዕጽ /ዛፍ/ የእድገት ባህርይ ሲሆን ለሚሰጠው ፍሬና ጥቅም እውነተኛ አባባል ነው ። አንድ  ዛፍ አድጎ አንሰራፍቶ ጥሩ ፍሬ አፍርቶ ጥቅም ሊሰጥና ሊበላ የሚችለው ፣ ከምግብነት አልፎ በዛፍነቱም ለአዕዋፋት እና ለእንስሳት መጠለያ መከላከያ ሊሆን የሚችለው ቀጥ ብሎ አድጎ ሲፈለግ ለተለያየ አገልግሎትም እንዳደረጉት የሚሆነው ሥሩ ውሃ ሲጠጣ ነው ሉቃ 13፥8 ። በተጨማሪም የሚስማማውን ማዳበሪያ ፣ ልዩ ልዩ ማዳበሪያ ከሥሩ ሲያስታቅፉት ሲኮተኩቱትና ሲንከባከቡት ጥሩ ዛፍና ጥሩ ፍሬ ይወጣዋል ዮሐ 15፥1። ነገር ግን ችግኙ እንደተተከለ ምንም አይነት እንክብካቤ ካልተደረገለት ላያድግና ፈጽሞ ሊደርቅም ይችላል:: ምናልባት በተፈጥሮው ችግርን ተቋቁሞ ሊያድግ ቢሞክርም ይቀነጭራል እንጅ አያድግም:: ስሙም ዛፍ ሳይሆን ቁጥቋጦ ይባላል:: ቁጥቋጦ ደግሞ ለምንም አይሆንም። የደረሰ ሁሉ እንደፈለገ ይጎነትለዋል ፣ ይቆርጠዋል ረብ የለሽ ይሆናል። እንግዲህ ይሄ ለራሱ ለዛፉ የቀረበ እውነተኛ ታሪኩ ነው ። ምሳሌነቱ ወይም ንጽጽሩ ደግሞ ስለሕፃናት ወይም ስለሰው አስተዳደግ ነው ። ዛፍ ይተከላል ፣ያድጋል፣ይሞታል ለዚህ ነው ሳይንስ ዛፍ ሕይወት አለው እሚለው ። ሰውም ይወለዳል፣ያድጋል፣ይሞታል ክቡር የሆነው የሰው ልጅ በእናቱ ማኅጸን ከተቀረጸ ጀምሮ እንክብካቤ ይፈልጋል። ምክንያቱም በአዕምሮም በአካልም ለማደግ እንክብካቤ በመሆኑ በተለይም ተወልዶ በቋንቋ መናገር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ልክ እንደዛፉ በጥሩ ሁኔታ አድጎ ሰው ለመሆን ሥሩን ውሃ ማጠጣት ነውና ከዛፉ እጅግ በተለየ መልኩ እንክብካቤ ያስፈልገዋል ።

ዛፍ ለራሱ ምግብ ብቻ ነው እሚፈልገው አያስብም ፣አይናገርም ፣አይሠራም ምንም ኃላፊነት የለበትም ሰው ግን ያስባል፣ይናገራል፣ይሠራል በዚህም የተነሳ ነገ ከነገ ወዲያ በሥጋዊም በመንፈሳዊም ህይወት አድጎ ሰው ብቻ ሳይሆን መልካም ሰው ፣ጥሩ ዜጋ፣ ቀና አመለካከት፣ በጥሩ እውቀት የተሞላ ሆኖ  ጥቅሙን ለማየት«ፍሬውን ለመብላት ሥሩን ውሃ ማጠጣት» ተገቢ ነው:: ወላጆች በልጆች አስተዳደግ ሂደት ይህን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው:: ልጆችን የመንግሥተ ሰማይ አርበኞች ፣የክርስቶስ ወታደሮች አድርገን በማሰልጠን በተሰማሩበት ህይወት ያለፍርሃት በፅኑ እምነት የእግዚአብሔርን መንግስት የሚመሰክሩ እንዲሆኑ ካረግናቸው ፍሬውን በላን ማለት ነው::

«ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው መዝ 127፥3» ይህን ውድ ስጦታ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ህይወት ኮትኩቶ ማሳደግ ያስፈልጋል:: በሥጋዊ አስተዳደግ በአሁኑ ሰዓት ብዙ ወላጅ ራሱን ጎድቶም ቢሆን የልጆቹን ፍላጎት ለማሟላት አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል:: ልጆች ግን ይህን ውለታ ያውቁት ይሆን?  በተለይም በውጭው አለም ያለው የልጅ አስተዳደግ ዘይቤ /ሲስተም/ እጅግ የተለየና እንክብካቤውም የበዛ  ከመሆኑም በላይ፣ ልጆችን ጭራሽ ግዴለሽ እንዲሆኑ ሲያደርጋቸውና በፍቅር ፈንታ ለወላጆቻቸው ግድ ከማጣት አልፎም አንዳንዶቹም ጥላቻ ሲያሳድርባቸው ይስተዋላል:: ከዚህም አልፎ ጥቂት ነገር ከጎደለባቸው ወይንም አጥፍቶ ከተቆጡት ለፖሊስ ስለሚደውሉ  ወላጅም ፖሊስ መቶ እኔንም ከሚያሥረኝ ልጄንም ከሚቀማኝ ይልና እንደ አደራ /እንደሌላ ሰው/ ልጅ ተሳቆ አንጀቱ እያረረ የራሱ ልጅ እስከማይመስለው ድረስ ሲያጠፋ ማለትም ተጣሞ ሲያድግ እያየ ዝም ይላል።  እንደ ሀገራችን የዘመናዊ ተማሪ ቆይ 18 አመቴ ይድረስ እያለ ወላጁን ሲያስፈራራ ከመታየት አልፎም ልጆች በውጭው አለም እውነተኛ ምስክሮች ናቸው ተብሎ ይታመናል ። ስለዚህ ወላጅ «ከነገሩ ጦም እደሩ »ብሎ ችግሩ ቀጥሏል። ልጅን ሲያጠፋ እያረቁ፣ ጥሩ ሲሆን እየሳቁ፣ እያስተማሩ፣ እየመከሩ በቁምነገረኛነቱ እየኮሩ እንዲያድግ ማድረግ ነው::  ታዲያ አንድ ወላጅ አጥፍቶ ቢቆጣ ምንድነው ችግሩ ? ጉዳቱ ምን ይሆን? ወላጅ ልጁን እንደሰው ልጅ መሳቀቁ ለምን ? በሥጋዊ ህይወት ማሳደግ ሲባልኮ እንዲወፍርና የማይጠቅም ሥጋ ተሸክሞ እንዲቀጥል ፣ ስለሥጋ ብቻ እያሰበ  እንዲያድግ አይደለም::  ልጅን መቅጣት በጡት እሸት መብላትን በጥቅምት እንዲሉ አድጎ  ብዙ ለሚጠብቀው ነገር ሰዶ ማሳደድ  እንዳይሆን ስለቤተሰብ ፍቅር፣  ስለባህል፣ስለሃይማኖት ፣ስለ ሥነ-ምግባር እንደሙሴ እናት እንደ  ቆስጠንጢኖስ እናት አድርጎ ማሳደግ ያስፈልጋል::

መንፈሳዊ ህይወት

መንፈሳዊ ህይወት ሲባል ብቻውን መንፈሳዊ ህይወት ሳይሆን ሥጋዊ ህይወትን ይዞ  መንፈሳዊነትን መጨመር ማለት ነው፡፡ የዛሬን አያድርገውና ቀደም ሲል አባቶቻችን ንጉሥ ሁነው ካህን ካህን ሁነው ንጉሥ ነበሩ:: ንግሥት ሁነው ዳዊት ደጋሚ ቆራቢ አስቀዳሽ ጸሎተኛ ነበሩ:: በዚህም የተነሳ የተናገሩት ተደማጭነት እያገኘ ሀገርን አኩርተው ወገንን አክብረው በፈራሄ እግዚአብሔር በእዉነት ሲያስተዳድሩ ህዝቡም እጅግ በጣም ያከብራቸው ነበር። ምክንያቱ ደግሞ በሥጋዊም በመንፈሳዊም ህይወት በግብረ ገብ ተኮትኩተው በማደጋቸው ነበር። ይህን ተረት ተረት እሚመስል እውነት እንድናይ ከተፈለገ ዛሬም የሙሴን እናት ዮካብድን የመሰለች እናት ኦ .ዘኁ 26፥29 እንደ እስዋ ያለ እናት ካለች እንደ ሙሴ ያለ ጎበዝና ሃይማኖተኛ በሥጋዊም በመንፈሳዊ የተዋጣለት ጠንካራ ልጅ መውለድ ብቻ ሳይሆን ማሳደግም ይቻላል ፣ ሙሴ እናቱ የነገረችውን እንደጡት እየጠባ በሥጋዊ ሲጠነክር ግብጻዊውን ገሎ ወገኑን ከሞት ሲታደግ በዚሁ አድጎበት በኋላም ፈርኦንን ያህል ኃያል አስፈሪ ንጉሥ ሣይፈራ ወገኖቹን ከባርነት ቀንበር ነጻ አውጥቷል እግዚአብሔርም አግዞታል ።

 • በመንፈሳዊም ሲጠነክር 40 ቀን እና 40 ሌሊት በሲና ተራራ ጹሞ ጸልዮ ለማንም ፍጡር ያልተሰጠ ሽልማት ታቦተ ጽዮንን ከእግዚአብሔር እጅ ተቀብሏል ።
 • የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒም በአሕዛብ እጅ ቁጥጥር ሥር ሁና ልጅ ብትወልድ ልጅዋን ለሃይማኖቱ ስለሀገሩ ስለፈራሄ እግዚአብሔር በሚገባ እያስተማረች አሳድጋዋለች። በሃይማኖት ቆራጥዋ እናት በገባችዉ ብጽዓት መሠረት በአካልም በመንፈስም ጠንክሮ ልጅዋ ለንግሥና ሲደርስላት በእርስዋ አሳሳቢነት ቢሆንም የእናቱን ትእዛዝ የሚቀበለዉ ቆስጠንጢኖስ የፈጣሪዉን የክርስቶስን ዕጸ መስቀል ለ6 ተከታታይ ወራት ቆፍሮ ያወጣ ያገኝ ታላቅ መሪ ነበር። እኛስ ? የኛ ልጆችስ ? እኛማ ሦስት ነገር እንኳን ማስተማር አቅቶናል የራሳችነን ቋንቋ ፣ባህል፣ ሃይማኖት እነዚህን ካስተማርን ሥነ-ምግባሩም በዚሁ ሊመጣ ይችላል ግን ስንቶቻችን ነን በነዚህ ጉዳዮች ከቤተሰባችን ጋር የምንግባባው ? ያልሆነ ምክንያት እየደረደርን ይደጉ ገና ናቸው፣ አናስጨንቃቸውም፣ የሀገሩ ህግ አይፈቅድም ወዘተ በማለት እንቆይና ገና ከፍ ሳይሉ ውሃ በብርጭቆ ቀድተህ አጠጣኝ ተብለው ቢታዘዙ እራስህ ተነስተህ ቀድተህ ጠጣ ሲሉ በዚህ መራገምና እራስን መውቀስ እንጀምራለን:: እንክብካቤ እንደጎደለው ቁጥቋጦ ተንጋዶ ስላደገ የት የተማረውን ያድርግ ቤተሰብ አላስተማረውማ:: እጅ ማስታጠብ፣ታላቅን ማክበር፣እግር ማጠብ አብርሐም ከነዘሩ የተባረከበት ይሄ ሥርዓት ነበር። ስለዚህ ለ8ኛው ሺህ ትውልድ ተጠያቂው የ8ኛው ሺህ ወላጅ ነው ። እስኪ ወገኖቸ ሁላችሁም በዓይነ ህሊናችሁ ወደኋላ ተመልከቱ እንዴት ነበር እናንተ ያደጋችሁት? አንዳንዱ ያልገባዉ ልጅማ እንደእኔ ሁኖ እንዲያድግ አልፈልግም ይላል። እንዲርበው እንዲጠማውኮ አይደለም የነገው ትልቅ ሰውነት የሚለካው ዛሬ ባሳደግንው ልክ ነው:: አንድ ሕጻን  በወላጆቹ፣በአካባቢው ማሕበረሰብ እና በትምህርት ቤት ተቀርጾ ያድጋል፤  ዋናዉ መሠረቱ ግን ቤት ውስጥ ነው:: ትልቁ ፈተናም ልጅ መውለዱ ሳይሆን ማሳደጉ ነው ። ቤተሰብ ትልቅ ተቋም ነው ።

ወላጆች ልጆቻችሁን እንደምትወዱ ምንም ጥርጥር የለውም:: ልጆችስ ወላጆቻችሁን ትወዳላችሁ? መልሱን ለራሳችሁ መልሱ:: በውጭው አለም ያለ ሁሉን ነገር ልመና ነው ብሉ፣ ጠጡ፣ ልበሱ፣ ተማሩ፣ ጎድሎበት ወላጁን በፍቅር የጠየቀው ነገር የለም በፍላጎት ያላደረጋው ነገር ስለሆነ ከላይ እንደተባለው ደንታቢስ ያደርገዋል የወላጅንም ዉለታ ከቁምነገር ካለመቁጠር አልፎም ከራሱ ፍላጎት ዉጭ ከሆነ ማን ውለደኝ ብሎሃል እስከማለት ይደርሳል። በዚህም የተነሳ የዘመኑ ልጆች ከወላጅ ይልቅ ገንዘብን፣ ከሰው ይልቅ ቁስ ነገርን የሚወዱት አሳዳጊ አጫዋቻቸዉ ሞባይል ስለሆነ እምታጎርሰው እናቱን እንኳን ቀና ብሎ ሳያይ እየተለመነ እየጎረሰ ስላደገ አይገነዘበውም:: ታዲያ በዚህ መልኩ ያደገ ልጅ ለየትኛዉ ቤተሰብ ለየትኛዉ አባትና እናቱ ለየትኛዉ እህት ወንድሙ ለየትኛዉ ዘመዱ ነው ፍቅር የሚያድርበት? በውነት እጅግ ያሳስባል፣እንቅልፍ ያሳጣል፣ ጉዳዩ ከባድ ነው::

መፍትሄዉ ምን ይሁን ?

 • ስልክ ይወዳሉ እያልን በር አንክፈት፣
 • እሚያስፈልገዉን ወላጅ ሊመርጥለት ይገባል፣
 • ቋንቋን ፣ባህልን፣ ሃይማኖትን ፣ሥርዓትን ፣ሥራንም ጭምር በአግባቡ ልናስተምራቸው ይገባል። 
 • በተቻለ መጠን ክጥሩ ጓደኛ ጋር እንዲውሉ ማድረግ «፡ከቅን ሰው ጋር ከዋልክ ቅን ትሆናለህ ከጠማማ ጋር ከዋልክ ጠማማ ሁነህ ትገኛለህ » መዝ 18- 25 ፣ አትሳቱ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋዋል 1ኛ ቆሮ 15-33       
 • ለተወሰን ደቂቃም ቢሆን መንፈሳዊነትን ለማስርጽ ከልጆች ጋር መጸለይ፣ ምግብ ሲቀርብ ጸሎት አድርጎ /አባታችን ሆይ/ ብሎ መብላትን ማሳየት
 • ቅዱሳት ሥዕላትን በቤታችን አስቀምጠን መማጸኛ መለመኛ መጸለያ መማለጃ መሆናቸዉን ማስተማር/ በስእሉ ላይ በመንፈስ አድሮ እግዚአብሔር እንደሚሰማን መንገር፣ለሥእሉም ክብር መስጠትና ማሳየት
 • በተገኘው አጋጣሚ ሁልጊዜ ስለቤተ ክርስቲያን መወያየት፣ፍቅሩ እንዲያድርባቸው ተነሱ ብሎ የባህል ልብስን ለባብሶ ቤተ ክርስቲያን ሄደን እንሳለም ማለት ፣መሄድ አይወዱም እያልን አለማመካኘት ፣ ስለመስቀል መሳለም፣ ስለእምነት፣ ስድንግል ማርያም ክብርና አማላጅነት ፣ስለቅዱሳን ክብርና አማላጅነት፣እንዴት ማማተብ እንዳለብን ማሳየት፣ ሙዳየ ምጽዋት ማጠራቅምና መባ መስጠት ማሳየት ፣እንዲያደርጉ ማበረታታት ያስፈልጋል ለዚህ ሁሉ እንግዲህ የግድ ሰባኪ በየቤቱ አያስፈልግም። ቤተሰቡ በየቀኑ ትንሽ ትንሽ መጽሕፍ ቅዱስ በየተራ ማንበብ ፣  አይደለም ለነፍስ ጥቅም ለሥጋም ጥቅም ቢሆን ስንፍናን የምናበረታታ እንጀራ መቁረስ እንኳን የማናስተምር መሆን የለብንም::
 • በዚህ የግንኙነት ሰንሰለት ውስጥ እግዚአብሔር ሕጻናትን እንደሚወድ ማስረዳት እግዚአብሔር ሕጻናትን ይጠብቃልና
 • ሕጻናት ወደኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ማቴ 19፥14
 • ማቴ18፥3 ካልተመለሳችሁ እንደሕጻናትም ካልሆናችሁ ወደመንግሥተ ሰማያት አትገቡም
 • እግዚአብሔር ሕጻናትን አስተዋዮች ያደርጋል መዝ 119፥130
 •  ከሕጻናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዝጋጀህ መዝ8፥2

ማጠቃለያ

በአግባቡ ጊዜና ትኩረት በመስጠት ከያዝናቸው ልጆቻችን መምህሮቻችን ይሆናሉ:: አለባበስንም ሥርዓትንም ሁሉንም ካሳየናቸው በደንብ ያኮሩናል በመንፈሳዊ ህይወት እንዴት እንደምናሳድጋቸው ልዩ ትኩረት መስጠት ግድ ይለናል:: ብንችል በተገኘው አጋጣሚ አስፈላጊውን መሥዋዕትነት እየከፈልን በኦን ላይንም ሆነ በአካል ከፊደል ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲማሩ ማድረግ አለብን:: የአባቶቻችን ማንነት በዚህ የተመሠረተ ነውና ። « ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደሆነ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደተወለዱ ሕጻናት  ተንኮል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ » 1ጴጥ. 2፥2።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ክብረ ክህነት

በክህነት አገልግሎት ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ማዕረጋት አሉ። እነርሱም ጵጵስና፣ ቅስና እና ዲቁና ናቸው። የየራሳቸው ዋና ዋና የአገልግሎት ድርሻም አላቸው። ለምሳሌ፡-

ጳጳሱ፡- አንብሮ እድ ላዕለ ጳጳስ ማለት ጳጳሳት ሲሾሙ እጁን በመጫን መሳተፍ፣ ቀሳውስትን መሾም፣ ዲያቆናትን መሾም፣ ማጥመቅና ቀድሶ ማቍረብ ናቸው።

ቄሱ፡- ማጥመቅና ቀድሶ ማቍረብ ናቸው።

ዲያቆኑ፡- መላላክ ነው።

በማቴዎስ ወንጌል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ያስተማረው ትምህርት ይህን ያስረዳል። “መንገድ እንደሚሄድ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት፣ ለአንዱ ሁለት፣ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ” (ማቴ.፳፭፥፲፬-፲፭) ይህን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት መተርጕማኑ ባለአምስት ጳጳስ ባለሁለት ቄስ፣ ባለአንድ ዲያቆን ብለው ተርጕመውታል። ባለአምሰት ባለሁለትና ባለአንድ ብለው ለጳጳስ፣ ለቄስና ለዲያቆን የሰጧቸውም ካላቸው ድርሻ አንጻር ነው።

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የአገልግሎት ድርሻዎች በእያንዳንዱ የክህነት ማዕረግ የሚከናወኑ ናቸው። ከላይ ወደታች መጥቶ ማገልገል ይቻላል። ለምሳሌ ጳጳሱ ዝቅ ብሎ የቄሱንም የዲያቆኑም አገልግሎት ማከናወን ይችላል። ቄሱም ዝቅ ብሎ የዲያቆኑን አገልግሎት ማከናወን ይችላል። ከታች ወደላይ ግን አይቻልም። ለምሳሌ ዲያቆኑ የቄሱን አገልግሎት ማከናወን አይችልም። ቄሱም እንዲሁ የጳጳሱን አገልግሎት ማለትም ከእርሱ የአገልግሎት በላይ የሆኑትን አገልግሎቶችን ማከናወን አይችልም። ለምሳሌ ካህናትን መሾም የጳጳስ እንጂ የቄስ ድርሻ አይደለም። ቄስ ክህነት መሾም አይችልም።

ከማሰር ከመፍታት ሥልጣን አንጻርም ፍትሕ መንፈሳዊ በየማዕረጉ ያለውን ሁኔታ “ወኢይደሉ ለአሐዱሂ እምሊቃነ ጳጳሳት፣ ወጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት ከመ ይፍታሕ ዘአሠሮ ካልኡ ዘእንበለ እምድኅረ ሞቱ፤ ከሊቃነ ጳጳሳት ከጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳት ለአንዱስ እንኳን አንዱ ያወገዘውን አንዱ መፍታት አይገባውም ከመሞቱ በኋላ ቢሆን ነው እንጂ” (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፬ ቁጥር ፵፩) በማለት ያስረዳንና “ወሊቀ ጳጳሳትሰ ብውሕ ውእቱ ከመ ይፍታሕ ማእሠሮሙ ለእሉ ኵሎሙ ሶበ ርእየ ዝክተ፤ ሊቀ ጳጳሳት ግን ነገሩን መርምሮ ካወቀ በኋላ እሊህ ሁሉ ያወገዙትን መፍታት ይገባዋል። እስመ ውእቱ ከመ እግዚአ ቤት በላዕሌሆሙ፤ እርሱ በእነርሱ ላይ የሹመት ባለቤት ነውና” ብሎ ያለውን የሥልጣን ደረጃ ያብራራልናል። ይህን ምንባብ በአንድምታ ትርጓሜው የበለጠ ግልጽ ሆኖ ተብራርቶ እናገኘዋለን። “ሊቀ ጳጳስ ያወገዘውን ጳጳስ፣ ጳጳስ ያወገዘውን ኤጲስ ቆጶስ፤ ኤጲስ ቆጶስ ያወገዘውን ቄስ ሳለም ከሞተም በኋላ አይፈታውም። ቄስ ያወገዘውን ኤጲስ ቆጶስ፣ ኤጲስ ቆጶስ ያወገዘውን ጳጳስ፣ ጳጳስ ያወገዘውን ሊቀ ጳጳስ ሳለም ከሞተም በኋላ ይፈታዋል። ሊቀ ጳጳስ ያወገዘውን ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስ ያወገዘውን ጳጳስ፣ ኤጲስ ቆጶስ ያወገዘውን ኤጲስ ቆጶስ፣ ቄስ ያወገዘውን ቄስ በሕይወት እያለ መፍታት አይችልም ከሞተ በኋላ ግን ይፈተዋል።” እንዲል። ይህ የክህነት ማዕረግ የቤተ ክርስቲያንን ጽኑዕ የሆነ መዋቅራዊ አደረጃጀትና “እናት አባትህን አክብር” ብላ የምታስተምር ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ደረጃውን የጠበቀ አደረጃጀት እንዳላት ያስረዳናል።

ይህ በእያንዳንዱ የክህነት ማዕረግ የሚከናወን የአገልግሎት ድርሻ ነው። በአጠቃላይ ግን ካህናት በክህነት አገልግሎት ሲኖሩ ምን ምን ኀላፊነቶች አሉባቸው ቢባል የሚዘረዘሩት በርከት ያሉ ቢሆኑም በዚህ ጽሑፍ የሚከተሉትን ብቻ እንመለከታለን።

ካህናት ጠባቂ ናቸው

ካህኑ መንጋዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገቡ ዘንድ ቁልፉ በእጁ ያለ በረኛ ነው። ምእመናን ዘለዓለማዊውን ርስት ይወርሱ ዘንድ ተግቶ መሥራት ይጠበቅበታል። “የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል” (ማቴ.፲፮፥፲፱) ተብሎ ይህን ያህል ኃላፊነት የተሰጠው ካህን ምእመናን መንግሥተ ሰማያት ቢዘጋባቸው የእርሱ ድርሻ እንዳለበት ማመን ይኖርበታል። ምክንያቱም መክፈቻው በእጁ አለና። ስለዚህ ካህን ይህን ያህል ኃላፊነት ያለበት ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው ትምህርት እና አንቀጸ አባግዕ ተብሎ በሚጠራው የወንጌል ክፍል “እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደበጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ ወንበዴም ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎቹ ጠባቂ ነው። ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል።) (ዮሐ.፲፥፩-፫) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። በዚህ ምንባብ ጠባቂው በጎችን ከመጠበቅ ባለፈ በጎችን የሚጠብቀው እረኛ በበሩ የሚገባ፣ በጎቹን በየስማቸው የሚጠራቸው፣ በጎቹ የሚከተሉት፣ በጎቹን የሚያሰማራ እየተባለ ተገልጾ እናገኘዋለን። በበሩ የሚገባ ሲል በር የተባለው ሃይማኖት፣ ወንጌል፣ ንስሓ ነው፤ በሃይማኖት የሚኖር፣ በአማናዊት ሕግ በሕገ ወንጌል አምኖ የሚኖር እንደሰውነቱ የንስሓን አስፈላጊነት የተረዳና በንስሓ የሚመላለስ ማለት ነው። በጎቹን በየስማቸው የሚጠራቸው የተባለው ደግሞ የሚጠብቃቸውን ምእመናን በትክክል የሚያውቃቸውና አስፈላጊውን ጥበቃ የሚያደርግላቸው ማለት ነው። በጎቹ የሚከተሉት ሲልም ርትዕት የሆነችውን ሃይማኖት የሚያስተምራቸው፣ በሃይማኖት እርሱን መስለው እንዲኖሩ የሚያደርግ በጎቹ በትክክል በአባትነቱ አምነውበት የሚከተሉት ሲል ነው።

ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በሃይማኖተ አበው “የካህኑን ምክሩን፣ ትእዛዙን፣ ተግሣጹን አንሰቀቅ፤ ነፍስን የሚያድን ባለመድኃኒት ነውና፤ የነፍስን ደዌ የሚያርቅ ይቅርና የሥጋ በሽታ የሚያድን ባለመድኃኒትስ ወደ ሥጋዊ በሽተኛ በመጣ ጊዜ ለመድኃኒቱ ከማይስማሙ ምግቦችን ከመመገብ ይከለከል ዘንድ ያዝዘዋል፤ መራራ መራራ ቅጠልን ምረቱ ጭንቅ ሽታው ክፉ የሚሆን ከብዙ ወገን የተቀመመ መድኃኒትን ያጠጣዋል። በድውዩ አካል የተለያየ ሕዋሳትን አንድ ያደርግለት ዘንድ። (ሃ.አበ.፴፯፥፫) በማለት እንደገለጸው ቃሉን በትክክል ሰምተው የሚከተሉት መሆን አለበት።

በጎቹን የሚያሰማራ ሲልም የበጎች መሠማሪያ የተባለች ቤተ ክርስቲያን፣ መንግሥተ ሰማያት ናትና ወደቤተ ክርስቲያን የሚያቀርባቸው በቤተ ክርስቲያን እንዲኖሩ የሚያደርግ ማለት ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸው ጽኑ አደራ በመጽሐፍ ቅዱስ “አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (ሐዋ.፳፥፳፰) ተብሎ ተጽፎ እናገኘዋለን። ስለዚህ ካህናት የምእመናን ጠባቂዎች ናቸው። ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው ‹‹ኦ ካህናት አንትሙ ውእቱ አዕይንተ እግዚአብሔር ብሩሃት፤ እናንተ ካህናት ሆይ የእግዚአብሔር ዐይኖች ናችሁና ኃጢአተኛውን እንደ ወንድማችሁ ገሥጹት።” በማለት በቅዳሴው ገልጾት እናገኛለን። ይህም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም ፤ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ በማለት የሰጣቸውን ክህነት እንዳይዘነጉ በማስታወስ ያላቸውን ልዕልና ያስረዳል።

ከላይ በገለጽነው ሐሳብ ልዕልናቸውን ብቻ ሳይሆን ኀላፊነታቸውንም ያስረዳል። ምክንያቱም ካሀናት ባያስተምህሩ በሚጠፉት ነፍሳት ሁሉ የመጀመሪያ ተጠያቂዎች እነሱ ናቸውና። የእግዚአብሔር ዐይኖች ከፈጠሯቸው ፍጥረታት ለቅጽበት ያህል እንኳ በጥበቃቸው አይለዩም። ካህናትም ከንስሓ ልጆቻቸው መለየት እንደሌለባቸው ሲያስረዳ አዕይንተ እግዚአብሔር ይላቸዋል።

ሊቁ ካህናትን ብቻም ሳይሆን ዲያቆናትንም እንዲህ ይላቸዋል። “ኦ ዲያቆናት ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ወላዕካኒሃ ምልሑ ውስቴታ ኢየሀሉ ተኵላ ምስለ በግዕ አንቄ ምስለ ርግብ፤ የቤተ ክርስቲያን ፋና የምትሆኑ ዲያቆናት አገልጋዮቿም የሆናችሁ ተኵላ ከበግ ጭልፊትም ከርግብ ጋር እንዳይኖር ለዩ።›› ተኵላ የተባሉ መናፍቃን ናቸው። እነዚህ ከምእመናን ጋር ጭልፊት የተባሉት ደግሞ ኃጥኣን ናቸው። እነዚህም ከጻድቃን ጋር ተቀላቅለው እንዳይኖሩ ለዩ እያለ ዲያቆናትም እንደ አቅማቸው ያስተምራሉና የየድርሻቸውን በትጋት መወጣት እንዳለባቸው ሲያስረዳ እናገኛለን። በቅዱስ ወንጌል “ምሳም ከበሉ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው እርሱም አዎን ጌታዬ ሆይ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው ፤ ጌታችን ኢየሱስም በጎቼን ጠብቅ አለው። ዳግመኛም የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን አለው፤ እርሱም አዎን ጌታዬ ሆይ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው ፤ ጠቦቶቼን አሰማራ አለው። ሦስተኛ ጊዜ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን? አለው፤ ጴጥሮስም ሦስት ጊዜ ትወደኛለህን ስላለው ተከዘ ጌታየ ሆይ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው፤ እንኪያስ ግልገሎቼን ጠብቅ አለው።” (ዮሐ.፳፩፥፲፭-፲፯) የሚል ኀይለ ምንባብ እናገኛለን። በዚህ ምንባብ ለቅዱስ ጴጥሮስ ከተሰጠው የጠባቂነት ድርሻ በተጨማሪ ልብ የምንለው ጉዳይ አለ። እርሱም አደራውን ለመስጠት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ነው። በጎቹን በአደራ ለመቀበል የበጎቹን ባለቤት መውደድ መቻል አለበት። እርሱን ደግሞ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስላላወቀ አይደለም የጠየቀው። እንደሚያውቅማ ራሱ ቅዱስ ጴጥሮስም “እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” በማለት ወዳጅነቱን ገልጾአል። ይሁን እንጂ የእርሱን አሰረ ፍኖት ተከትለው በእርሱ መንበር ተቀምጠው ለመንጋው እረኛ የሚሆኑ ካህናት አደራው እጅግ ጥብቅ እንደሆነ እንዲረዱት፣ አስቀድመውም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጆች መሆን እንዳለባቸው እንዲያውቁት ነው። ምክንያቱም በጎች የደም ዋጋ የተከፈለላቸው ናቸው። በወርቅ በብር ሳይሆን በደም የተገዙ ናቸውና ኀላፊነቱን በትጋት የሚወጣና የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጆች መሆን ይኖርባቸዋል። መንጋውን ይጠብቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር በአደራ የተቀበለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቋቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን” (፩ጴጥ.፭፥፪) በማለት እርሱም እረኞች እንዲጠብቁ ብቻ ሳይሆን በምን መንገድ መጠበቅ እንዳለባቸውም ይናገራል።

ካህናት መሪ ናቸው

ጌታቸን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው የእረኝነት ትምህርት “ሁሉንም አውጥቶ ባሰማራቸው ጊዜ በፊት በፊታቸው ይሄዳል በጎቹም ይከተሉታል ቃሉን ያውቃሉና” (ዮሐ.፲፥፬) የሚል ኀይለ ምንባብ እናገኛለን። በዕብራውያን ባህል እረኛ በፊት በፊት እየሄደ በጎቹ ይከተሉታል። እረኛው ካልተንቀሳቀሰ እነርሱም አይንቀሳቀሱም። ካህኑ የምእመናን እረኛ ነውና ከምእመናን ቀድሞ መገኘት አለበት።

እረኛው መሪ ነው ሲባል እንዲሁ በፊት ሆኖ ተከተሉኝ የሚል ብቻ አይደም። ሲከተሉት ተከታዮቹን ወስዶ በመልካም መሰማሪያ ላይ የሚያደርስ ማለት ነው። መልካም መሰማሪያ የተባለች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም መንግሥተ ሰማያት ናት። ስለዚህ መልካም ሥራ ሠርቶ እርሱም የሚጸድቅ መንጋውንም ወደ መልካም ነገር እየመራ የሚያጸድቅ መሆን አለበት።

ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠውና በቅዱስ ወንጌል የተጻፈው የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ኀላፊነት “ጠቦቶቼን አሰማራ” የሚል ትእዛዝ ነበረበት። አሰማራ የሚለው ትእዛዝ ከመጠበቅ ባለፈ አቅጣጫ ማሳየትን፣ መምራትን፣ መዋያቸውን፣ ማደሪያቸውን፣ ምግባቸውን፣ አጠቃላይ ለሕይወታቸው አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሙሉ ከማሰብና ከማዘጋጀት ጋር የተያያዘ ነው። ካህኑ መሪ ነው ሲባል ክርስቲያናዊ ሕይወትን በተግባር እየኖረ የሚያሳይ መሆን አለበት። እንዲህ ከሆነ ሕዝቡም የእርሱን ፈለግ የሚከተል ይሆናል። ይህን አስመልክቶ በፍትሕ መንፈሳዊ “በከመ ይቤ ሆሴዕ ነቢይ እስመ ከመ ይከውን ካህን ከማሁ ካዕበ ሕዝብኒ፤ ነቢዩ ሆሴዕ መምህሩ ደግ ቢሆን ሕዝቡም እንደርሱ ደጋግ ይሆናሉ ብሎ እንደተናገረ ደግ መሆን አለበት” የሚል ኀይለ ቃል እናገኛለን። ይህንም ሲያጠነክር “ ወዓዲ መምህርነ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነ ወጠነ ቅድመ ከመ ይግበር ወይምሀር፤ ዳግመኛም ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ሠርቶ ያስተምር ዘንድ ጀመረ። ወይቤ እስመ ዘይገብር ወይሜህር ዐቢየ ይሰመይ በመንግሥተ ሰማያት፤ ሠርቶ የሚያስተምህር መምህር በመንግሥተ ሰማያት ደገኛ እንዲሆን ተናገረ” ተብሎ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተግባራዊ አስተምህሮ በማስረጃነት ተጠቅሶ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ካህኑ በተግባር እያሳየ መንጋውም እርሱን እንዲከተል ማድረግ እንደአለበት ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃልም በተግባርም አስተምሯል። የቅደም ተከተል ጉዳይ ካልሆነ በቀር በተግባር ያልፈጸመውን እኛ እንድንፈጽመው አላዘዘንም። ለዚህም ነው ከላይ በጠቀስነው በፍትሕ መንፈሳዊ “ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ሠርቶ ያስተምር ዘንድ ጀመረ።” የተባለው። ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የሾማቸው ካህናትም እንዲሁ ምእመናንን ሲመሩ እነርሱ በተግባር እያከናወኑ መሆን አለበት።

ካህናት መጋቢ ናቸው

በክህነት አገልግሎት መኖር የክርስቶስ እንደራሴ ሁኖ የክርስቶስን ጸጋ ለምእመናን ማድረስ ነው። በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፬ ቍጥር ፵፯ “ሊቀ ጵጵስና ህየንተ ክርስቶስ ውስተ ዓለም፤ በዚህ ዓለም ሊቀ ጵጵስና መሾም እንደ ክርስቶስ መሆን ወይም የክርስቶስ ምስለኔ መሆን ነው። በእንተ ዐቂበ ሃይማኖት፤ ሃይማኖትን ለማጽናት፣ ወመግቦተ መሃይምናን፤ ምእመናንንም ለመመገብ” ተብሎ ተገልጾ እናገኘዋለን። ስለዚህ ሃይማኖትን አጽንቶ ምእመናንን ከነጣቂ ተኵላ ጠብቆ፣ የሚያሻቸውን ምግብ እየመገበ ይኖራል። ካህኑ የሚጠብቃቸውን መንጋዎቹን መመገብ የግድ ይለዋል። ጠባቂነቱ፣ አባትነቱ መንፈሳዊ ነውና መንፈሳዊውን ምግብ የእግዚአብሔርን ቃል ዕለት ዕለት እየመገበ ማኖር አለበት። በቅዱስ ወንጌል “ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰቡ ላይ የሚሾመው ደግ፣ ታማኝና ብልህ መጋቢ ማን ይሆን? ጌታው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው አገልጋይ ብፁዕ ነው” (ሉቃ.፲፪፥፵፪-፵፫) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ካህኑ እግዚአብሔር በምእመናኑ ላይ የሾመው መጋቢ ነው። በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው ተግቶ የሚመግብ ደግሞ እጅግ የላቀ ዋጋ ያገኛል።

የሰው ልጅ በባሕርዩ ምግበ ሥጋም ምግበ ነፍስም የሚያሻው ሆኖ ተፈጥሯል። የተለየ ጸጋ ኖሮት ያለ ምግበ ሥጋ መኖር ቢችል ያለምግበ ነፍስ መኖር አይችልም። ካህኑ እንዲጠብቃቸው በአደራ የተሰጠውን መንጋዎቹን ምግበ ሥጋቸውንም ምግበ ነፍሳቸውንም ማዘጋጀትና መመገብ ግዴታው ነው። ምን አልባት ምግበ ሥቻውን በተመለከተ እርሱ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ማገዝ ባይችል እንኳን ልጆቹን እያስተባበረ በማኅበራዊ ኑሯቸው እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ እያደረገ ችግራቸውን እንዲፈቱ ማድረግ አለበት።

ምክንያቱም በሥጋዊ ችግራቸውም አቅሙ በፈቀደ መጠን መሳተፍ አለበት። ይህን በተመለከተ በመጽሐፈ ዲድስቅልያ “ሰውን ወዳጅ፣ እንግዳን የሚቀበል፣ ፊት አይቶ የማያዳላ፣ ለባለጸጋና ደሃ የማያዳላ፣ ፈራጅ፣ ጥበብ ያለው፣ ለመስጠት እጁን የሚዘረጋ፣ ረዳት የሌለውን የሚቀበል፣ ድሆችን፣ ድሀ አደጎችንና ባልቴቶችን የሚወድ ይሁን፤ ዳግመኛም ልጆች ያሏቸውን ይመግብ” (ዲድስቅልያ አንቀጽ ፬ ቍጥር ፲፬) የሚል የሐዋርያትን ትእዛዝ እናገኛለን። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም በመልክቱ “ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቀቡት” (ያዕ.፭፥፲፬) በማለት የገለጸው በደዌ ነፍሳቸው ብቻ ሳይሆን በደዌ ሥጋቸውም መጨነቅ እንዳለባቸው፣ በነፍስ ረኀባቸው ብቻ ሳይሆን በሥጋዊ ረኀባቸውም እንዲጨነቅ ሲያስረዳን ነው። መሪ ነው ሲባልም እንዲህ ያለውን ሁሉ እያስተባበረ የመፍትሔ አካል መሆን እንዲችል ነው። ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ ካህኑ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ግን የመንፈስ ልጆቹ ናቸውና ለመንፈሳዊ ምግባቸው ነው። ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ምግባቸው ምንድን ነው? ከተባለ ተፈጥሯቸው በአንድ በኩል ከባሕርየ እንስሳ ነውና ምግበ ሥጋ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ በሌላ በኩል ደግሞ በባሕርየ መላእክት ነውና እንደ መላእክት ምግባቸውም ቃለ እግዚአብሔር ነው። የመላእክትን ምግብ በተመለከተ ሊቁ ኤጲፋንዮስ በመጽሐፈ አክሲማሮስ “ወሲሳዮሙ ለመላእክት ቅዳሴ ወስብሐት ወስቴሆሙ ፍቅረ መለኮት፤ የመላእክት ምግባቸው የእግዚአብሔር ቃል መጠጣቸውም የመለኮት ፍቅር ነው” (አክሲማሮስ ዘዕለተ እሑድ ክፍል ፬ ቍጥር ፲፮) በማለት ያስረዳናል። እንደ መላእክት የእግዚአብሔርን ቃል የሚመገቡ መሆናቸውን ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወኅብስተ መላእክት በልዑ እጓለ እመሕያው፤ የመላእክትንም እንጀራ የሰው ልጆች በሉ” (መዝ.፸፯፥፳፭) በማለት ያስረዳናል።

ስለዚህ ካህኑ የመንጋዎቹ መጋቢ ነው። ሲባል ሊመግባቸው የሚገባው የእግዚአብሔርን ቃል ነው። በእግዚአብሔር ቃል ኮትኩቶ ማሳደግ ቃለ እግዚአብሔር የዕለት ተዕለት ምግባቸው እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅበታል። በቅዱስ ወንጌልም “ ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንዳይደለ ተጽፏል” (ማቴ.፬፥፬) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ካህኑ ለምእመናን የእግዚአብሔርን ቃል እየመገበ ከቤቱ እንዲኖሩ ማድረግ፣ በንስሓ ሕይወት እንዲመላለሱም ማስቻል፣ መንግሥተ ሰማያትን የሚያወርሰውን፣ የተዘጋችውን የገነትን በር የከፈተውን ሥጋ ወደሙ ማቀበል ዋነኛ ድርሻውና ኃላፊነቱ መሆኑን ነው።

የጠፉትን የሚፈልጉ ናቸው፡- በቅዱስ ወንጌል የዐመፅ ጥያቄን ያዥጎደጉዱት ለነበሩት ጸሐፍት ፈሪሳውያን ኃጢኣተኞችን ይቀበላል ከኃጢኣተኞችም ጋር ይበላል ብለው ላቀረቡለት ጥያቄ የሚሆን መልስ “ከእናንተ መካከል መቶ በጎች ያሉት ሰው ቢኖር ከእነርሱ አንዲቱ ብትጠፋው ዘጠና ዘጠኙን በምድረ በዳ ትቶ እስኪያገኛት ድረስ ይፈልጋት ዘንድ ወደጠፋችው በግ ይሄድ የለምን? በአገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በትከሻው ይሸከማታል” (ሉቃ.፲፭፥፬) ተብሎ እንደተጻፈ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጠፋውን አዳምን ይፈልግ ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣ። የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ የጠፋውን አዳምን እንደፈለገ ሁሉ እርሱ የሾማቸው ካህናትም ዋነኛ ተግባራቸው የጠፋውን የአዳምን ልጅ መፈለግ ነው።

መጥፋት በአካል ብቻ ላይሆን ይችላል። በመንፈስም መጥፋት አለ። ካህናት መንፈሳዊ ጠባቂዎች ናቸውና በመንፈስ የጠፋውን ፈልጎ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። ጌታችን ጠፍተው ስለተገኙ ሦስት ነገሮች እና ጠፍተው በመገኘታቸው በባለቤቶቹ ዘንድ ምን ያህል ደስታ እንደሚደረግ ሲያስተምር ጠፍተው ከተገኙት ከሦስቱ ነገሮች መካከል አንዱ በቤት ውስጥ የጠፋ ነበር። ጠፍታ የተገኘችው በግ በጠባቂው ግዴለሽነት የጠፋች ናት፤ የጠፋው ልጅ ደግሞ በጥጋቡ ከቤት ኮብልሎ የወጣና ከአባቱ ቤት መለየቱ አላዋጣህ ሲለው በራሱ ጊዜ ተመልሶ የመጣ ነው። ጠፍቶ የተገኘው ድሪም ግን በቤት ውስጥ ከቆሻሻ ጋር ተቀላቅሎ የነበርና ባለድሪሟ በመብራት ፈልጋ ያገኘችው ነው። (ሉቃ.፲፭፥፩-፳፬)

ካህናት እረኞች ናቸውና ቢቻል አስቀድመው መንጋቸው እንዳይጠፋ ተግቶ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ካልተቻለ የጠፋበትን ምክንያት፣ የት እንደጠፋ ማለት እንደበጊቱ በእረኛው ግዴለሽነት ነው? ወይስ እንደጠፋው ልጅ በራሱ ጥጋብ ነው? ወይስ ደግሞ በቤት ውስጥ ከጥራጊ ወይም ቆሻሻ ጋር የተደበቀ ነው? በማለት መለየትና ፈልጎ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

እንደ ዲናሩ ከቤቱ እያለ ግን በዓለም ቆሻሻ ተውጦ ይሆን፣ በቤተ ክርስቲያን እየተመላለሰ፣ በሚገባ የማይጸልይ ከሆነ፣ የማይጾም ከሆነ፣ ንስሓ የማይገባ ከሆነ፣ ሥጋ ወደሙ የማይቀበል ከሆነ በቤቱ አለ ግን በኃጢያት ቆሻሻ ተውጦ መገኘት አልቻለም ማለት ነው። ስለዚህ  እንደባለዲናሯ መብራት ማብራትና መፈለግ የካህኑ ድርሻ ይሆናል። ካህናት እነዚህንና የመሳሰሉትን ኃላፊነቶች ለመቀበል በቅድሚያ ኃላፊነታቸውን በሚገባ መረዳት፣ ለዚህ ኃላፊነት የሚያበቃ ዝግጅት ማድረግ፣ ማለትም በትምህርትም፣ በምግባርም፣ በቁርጠኝነትም ወዘተ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል። እንዲሁ የክርስቶስ ወዳጅ መሆን አለባቸው። ምክንያቱም በኃላፊነት የሚቀበሏቸው መንጋዎች በምድራዊ ወርቅና ብር የተገዙ ሳይሆኑ በደም የተገዙ ናቸው። ይህን በተመለከተ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ። ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ” (፩ጴጥ. ፩፥፲፰-፲፱)

በማለት ያስረዳናል። ስለዚህ እንደዚህ የከበረ ዋጋ የተከፈለላቸውን ምእመናን ለመጠበቅ የሚያበቃ ትጋት ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ በክህነት አገልግሎት የሚኖሩ ካህናት ኃላፊነታቸው እጅግ ከባድና በአግባቡ ከተወጡት ግን ሰማያዊ ክብርን የሚያጎናጽፍ መሆኑን መረዳት ይጠበቅባቸዋል። ስለሆነም መንጋውን በአግባቡ ሊጠብቁት፣ ወደሚፈለገው ቦታ ሊመሩት፣ የሚያስፈልገውን ምግብ ሊመግቡትና ቢጠፋ እንኳን ፈልገው ከጠፋበት ሊመልሱት እንደሚገባቸው ራሳቸው ካህናቱም መረዳት አለባቸው ምእመናንም እንዲሁ ይህን ጥብቅ አደራ ተረድተው በተቻለ መጠን የካህናት ትእዛዝ ሊቀበሏቸው ይገባል። እግዚአብሔር አምላክ ኀላፊነቱን በሚገባ የሚወጣ ጠንካራ አባት እንዲያድለን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኀበረ ቅዱሳን፣ የካናዳ ማዕከል ትምህርትና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል፡፡

ወስብሃት ለእግዚአብሔር፡፡

ስለምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? /ኢሳ. ፶፰፥፫/

በቀሲስ ስንታየሁ አባተ

በኢሳያስ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን የተናገሩት ቃል ነው። እስራኤላውያን የሚጾሟቸው ብዙ አጽዋማት ነበሯቸው። ለምሳሌ ያህልም ብናይ በሳምንት ሁለት ጊዜ በሳምንት ሁለት ቀን ይጾሙ እንደነበር በሉቃ. ፲፰፥፲፪ ላይ ያለው ቃል ያስረዳል። ማክሰኞና ሐሙስ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ወደ ደብረ ሲና የወጣበትና ከዚያ የወረደበት ዕለት ለማሰብ እስራኤላውያን በሳምንት ሁለት ቀኖች ይጾሙ ነበር። በነቢዩ በዘካርያስ ትንቢትም ላይ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን እንዲህ ብሎ አዝዟቸዋል «የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሀሤትም በዓላት ይሆናል ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ወደዱ።» ተብሎ ለእስራኤላውያንከእግዚአብሔር ዘንድ በነብዩ በኩል በተነገራቸው መሠረት የተጠቀሱትን ይጾሙ ነበር። /ዘካ. ፰፥፲፰-፲፱/።

በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን የእስራኤል ዘስጋ ታሪክ በምናይበት ሰዓት ብዙውን ጊዜ ሲጾሙ ብዙውን ጊዜ ሲጸልዩ በጾም ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ፣ በጾም ችግራቸውንና ሐዘናቸውን ለእግዚአብሔር ለመግለጽ፣ በጾም የልቡናቸውን መሻት ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመቀበል ነበር።

እኒህን ሁሉ አጽዋማት ጊዜያቱን ጠብቀው ቢጾሙም እግዚአብሔር በምህረት አይኖቹ አላያቸውም መራቡ መጠማታቸውንም አልቆጠረላቸውም ስለዚህ በርዕሳችን እንደጠቀስነው «ስለምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም» በማለት እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ዘንድ ምሬታቸውን ሲያቀርቡ እንመለከታለን። እስራኤል ጾመዋል ፣ደክመዋል፣ ራሳቸውንም አዋርደዋል፣ ሰውነታቸውንም አጎሳቁለዋል። ይሁን እንጂ የልቡናቸው መሻት ሰላልተፈጸመላቸው የጾማቸው ዓላማ ግቡን ስላልመታ ፍሬም ስላላፈራላቸው ወደ አባታቸው ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው «ስለምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም?» ብለው እንደጠየቁት እናያለን።

ስለምን እግዚአብሔር አልተመለከታቸውም? በእውነት የዋሀን እንደሚያስቡት ጾም ፈቃደ እግዚአብሔር ሳይሆን ቀርቶ ነውን? እግዚአብሔር ጾምን የማይቀበል ሆኖ ነውን? አይደለም።

በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጠቀሰው ጾም ፈቃደ እግዚአብሔር ነው። የሰው ልጆች እንዲጾሙ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር እነዲቀርቡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ጾም ፈቃደ እግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ዘንድ ከተሰጡት ትእዛዛትና ሕግጋት መካከል የመጀመሪያውና ቀዳሚ ትእዛዝ መሆኑን መጽሐፍ ቀዱስ ይነግረናል። /ዘፍ. ፪፥፲፮-፲፯/።

እግዚአብሔር ለአዳም ሁሉን ይገዛ ዘንድ በሁሉ ላይ ባለሥልጣን ገዥ ንጉሥ እንዲሆን አድርጎታል። ነገር ግን አዳምን ዓይኑ የተመለከተዉን ሰውነቱ የፈቀደውን ሁሉ ያደርግ ዘንድ አላሰናበተውም። ለዚህ ነው ሥርዓተ ጾምን /ሕገ ጾምን/ የሠራለት። እግዚአብሔር አዳም እንዳይበላ የከለከለውን ዕፀ በለስን በምናይበት ሰዓት ለአዳም እንዲበላ ከተሰጡት ዕፅዋት መካከል ተለይታ ለዓይን የምታስጎመጅ ለጥበብም መልካም ሆና የተገኘች ነበረች። ጾም አብልጠን የምንወደውን የሚያምረንና ለሰውነታችን እርካታና ምቾት የሚያስገኘውን ሁሉ ለተወሰኑ ጊዜያት ወይም በዘላቂነት መተውን የሚመለከት መልካምና ደገኛ የሆነ የሃይማኖት ሥርዓት ነው።

ጾም ከጥሉላት ምግቦች ወይም ከእንስሳት ተዋጽኦ ራስን ገትቶ መቆየት ብቻ አይደለም። ይልቁንም ጾም የመላ ሕዋሳት ተግባር ነው። ጾም በዚህ ምክንያት መላ ሰውነትን ለእግዚአብሔር ማደርያነት ቀድሶ ማቅረቢያ ነው። እስራኤል ከዚህ ስለጎድሉ ነው እግዚአብሔር በነብዩ በኢሳያስ አድሮ «በውኑ እኔ የመረጥሁት ጾም ይኸ ነውን?» በማለት ለእስራኤል ጥያቄ መልስ የሰጣቸው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ያለዘርዓ ብእሲ በፍጹም ድንግልና ከተወለደ በውኃላ ብርሃነ ክብሩን በገለጠበት በደብረ ታቦር ተራራ ከቀዱሳን አበው መካከል የተመረጡ ሰዎች በዚያ ተገኝተው ነበር። ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንዲሁም ነብዩ ኤልያስ በዚያ የክርስቶስ ክብር ብርሃነ መለኮቱ በተገለጠበት ተራራ ላይ ቆመው እናያቸዋለን። ይህን ሰማያዊ ክብር ለማየት የታደሉት እኒህ አበው በዘመናቸው 40 ቀንና ሌሊት ጾመዋል። በጾማቸውም በረከትን ተቀብለዋል። ሊቀ ነቢያት ሙሴ በመጾሙ እስራኤል የሚመሩበት ሕገ ኦሪት ሠርቶላቸዋል ሕዝበ እስራኤል የሚባረኩበትን ጽላት ተቀብሏል። ነብየ እግዚአብሔር ኤልያስም ፈራሽ ሆኖ ሳለ በመጾሙ በመጸለዩ ለእግዚአብሔርም ክብር በመቅናቱ ሰማየ ሰማያት እንዳረገ ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል።/፪ ነገስ. ፪፥፲፩/። ቅዱሳኑ በዘመናቸው በፈጸሙት መልካም ጾም የጌታችንን መለኮታዊ ክብር ለማየት በቅተዋል። ጾም በአግባቡ ቢጾሙት እግዚአብሔር እንደሚፈቅደው ሆነው ከተገኙ እግዚአብሔር ጾምን የሚቀበለው ሐዘንን ከልቡና የሚያርቅ እንባን ከዐይን የሚያብስ መሆኑን እናያለን።

ጾም እንዲህ ያለ ታላቅ ዋጋ የሚያሰጥ ቢሆንም እስራኤል ግን ጾመው ያገኙት ጥቅም አልነበረምና «ስለምን ጾምን» በማለት እግዚአብሔርን ይጠይቁታል።

ምክንያቱም ጾማቸው የጎደለው ኖሮ ነው ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርባቸው፣ ከእግዚአብሔር ሊያስታርቃቸው፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት ቸርነትን ሊያመጣላቸው ያልቻለውና «ስለምን ጾምን» ብለው መጠየቃቸው አግባብ ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርአት መሠረት ከዓመቱ ቀናት መካከል ከ235 ቀናት በላይ እንጾማለን። ይሁን እንጂ እንደ እስራኤል ዘሥጋ ሁሉ «ስለምን ጾምን?» የሚያሰኙ ሁኔታዎች አሉን። የበዛውን የዓመቱን ጊዜ በጾም አሳልፈናል በውኑ እግዚአብሔር ጾማችንን ተቀብሎአልን? ተመልክቶስ ቤታችንንና ሥራችንን፣ ልጆቻችንንና ሀብታችንን ባርኮአልን? ካልሆነስ ለምን? የጾምንበት ዓላማ ግቡን መምታቱንና አለመምታቱን ካየን በኋላ ለምን በሚል ጥያቄ አምላካችንን እንድናማርር አድርጎናል። መልካም ደገኛ የሆነውን ሥርአተ ጾም ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ራሱን የሚያዋርድ ሰው ሁሉ አጽዋጿሙ በእግዚአብሔር ፊት ምን እንደሚመስል ራሱን ሊጠይቅ፣ ሕይወቱንና ልቡናውን ሊመረምር ይገባል።

በሀገራችን፣ በቤተ ክርስቲያንና በቤታችን ውስጥ ዛሬ እንደምናየው መከፋፈልና መለያየት፣ ረሃብና ደርቅ፣ በሽታና ስደት ነግሰው ዕለት ዕለት የምእመናንን ልቡና በትካዜ ተውጠው እናያቸዋለን። በየቀኑ ከምትወጣዋ ፀሐይ ጀርባ መልካም ዕለትን ከመናፈቅ ይልቅ እያንዳንዱ ዕለት መከራ ያመጣብን ይሆን? እያሉ የሚሰጉ ወገኖቻችን ብዙ ናቸው። የዚህ ሁሉ መንስኤው እንደ እስራኤል ሁሉ መንፈሳዊነት የጎደለው ጾም ስለሆነ ነው። የቡዙዎቻችን ጾም እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ሆኖ አለመገኘቱ ነው።

ከላይ እንዳየነው እስራኤላውያን በዓመት ውስጥ አራት ወራትን በሳምንት ሁለት ቀናትን ቢጾሙም ጾማቸው መንፈሳዊነት የጎደለው ነበር። እስራኤል ቢጾሙ የሰዓቱን እርዝማኔ እንጂ በዚያ በረዘመው ሰዓት ወስጥ ምን እያደረጉ እንደሆነ አያውቁም ምን ማድረግ እነደነበረባቸውም አያስተውሉም ነበር። ይህ ሁኔታ ዛሬ በምንጾመው ጾም ውስጥ የሚታይ ነው።

እስከ ስድስት እስከ ዘጠኝ እስከ አስራ ሁለት ሰዓት እየቆየን እንጾማለን እንጂ በዓመቱ ያሉትን ሰባት አበይት የዐዋጅ አጽዋማት ዛሬ ደግሞ በግልና በፈቃድ የምንጾማቸውን የጳጉሜንና የጽጌን ጾም ጨምሮ መጾማችንን እንጂ በአጽዋማቱ ወራት ወቅትና ዕለት እንደ ምእመን አንድ የእግዚአብሔር ሰው ሊያድርገው የሚገባውን ነገር እያደረግን ነው ወይ? የሚለውን ነገር አናስተውለውም። የሚታየን መዋላችን ከምግብ መከልከላችንና ራሳችንን ማድከማችን እንጂ በነዚያ ሰዓታት ውስጥ በትሕትና ከወገኖቻችን ጋር በሰላምና በፍቅር መሄድ አለመሄዳችንን ስለማናስተውለው መንፈሳዊነት ይጎድለናል።

ከዚህ በተጨማሪ እስራኤላውያን ሲጾሙ ጥል ክርክና ግፍ ማድረግን ከልቡናቸው አላራቁትም ነበር። ይጾማሉ በሚጾሙበት ሰዓት ግን ይጣሉ ነበር። ይጾማሉ በሚጾሙበት ሰዓት እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ነበር። ይጾማሉ በተለይ በሚጾሙበት ወቅት በሠራተኞቻቸው ላየ ግፍ ያደርጉ፣ የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ ያስቀሩ፣ በግፍ ይበዘብዟቸው፣ ያስጨቋቸው፣ ያስመርሯቸው ስለነበር ይሄ ጾማቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ያቀርባቸው ዘንድ አልቻለም። እስራኤል «ለምን አልሰማኸንም» በማለት ከእግዚአብሔር ጋር በተዋቀሱ ጊዜ እግዚአብሔር በነብዩ በኢሳያስ አድሮ እንዲህ ይመልስላቸዋል «በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁን ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እነደምትጾሙት አትጾሙም» በማለት እግዚአብሔር ወቅሷቸዋል።/ኢሳ. ፶፰፥፫-፬/።

ጾም የምንጣላበት ሳይሆን ሰላምን የምናደርግበት ነው። ጾም የምንከራከርበት ጊዜ ሳይሆን አንድ የምንሆንበት ጊዜ ነው። ጾም ግፍን የምናደርግበት ሳይሆን የግፍን ማሰርያ የምንበጥስበትና ከክፉ አድራጊነት ወደ በጎነት የምንሸጋገርበት ጊዜ ነው።ይሄን ሳያገናዝቡ መጾም ጾማችንን መንፈሳዊነት የጎደለው ያደርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪ እስራኤላውያን ሲጾሙ ለወገኖቻቸው ምሕረትን አላደረጉም ነበር። ጾም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን የምንለምንበትና የምንጠይቀበት ጊዜ ነው። እግዚአብሔር ዓይነ ምሕረቱን እነዲመልስ እዝነ ልቡናውን ወደ እኛ ንዲያዘነብል የማያልቀውን የቸርነቱን ሥራ እንዲሠራልን የምንጠይቅበት ጊዜ ነው።

ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትንና ይቅርታን እንደምንፈልግ ሁሉ እኛም በጾማችን ወቅት ከሌላው ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ለወገኖቻችን ምሕረትን ልናደርግ ይገባል። ምሕረት ማድረግ ስንል ሁለት ነገሮችን ያጠቃልላል። እነዚህም ምሕረት ሥጋዊና ምሕረት መንፈሳዊ ናቸው።

ምሕረት ሥጋዊ ፤ለአንድ ሰው በሥጋ የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት ነው። ቀዶ ማልበስ ቆርሶ ማጉረስ ወዘተ ነው። የጎደለውን አይቶ መሙላት በተለይ በጾማችን ወቅት ከሌላው ወቅት በተለየ ሁኔታ ለሌሎች ምሕረት ማድረግ ይገባናል።

ምሕረት መንፈሳዊ ፤ ማለትም አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብበትን ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻችት ነው። በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል የአባትና የልጅ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ፣ ኃጢአት ሠርቶ ከእግዚአብሔር የራቀውን በትምህርት በምክር በተግሳጽ ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ነው። ከባልጀራው ጋር ተጣልቶ እግዚአብሔርን ያስቀየመውን በመካከላቸው እርቅ እንዲኖር ማድረግ በአጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወቱ እንዳይጎሰቁል እንዳይደክምና ከጽድቅ እንዳይጎድል መርዳት ነው።

እንደ እስራኤል ሁሉ ከምሕረት የራቀ ጾም ይዘን እንደሆነ መልስ የማያስገኝ በመሆኑ በምንጾምበት ሰዓት ለወገኖቻችን ምሕረት ማድረግን የጾማችን ክፍል ልናደርግ ይገባል።

«እኔስ የመረጥሁት ጻም ይህ አይደለምን? የበደልን አስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቆርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ደሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቆቱትንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል፥ የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሀል።» /ኢሳ. ፶፰፥፮-፱/ ተብሎ የተነገረው ቃል በጾማችን ወቅት ምሕረት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ያሳየናል።

እስራኤል ሲጾሙ ሥጋቸውን ከማስራብ በስተቀር ነፍሳቸውን በንስሐና በቃለ እግዚአብሔር አይመግቧትም ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና እንደ እግዚአብሔር ቃል የጾም ትልቁ ዓላማ ሥጋን ማስራብ ሳይሆነ ነፍስን በበጎ ነገር ማርካትና በበጎ ነገር ማጥገብን የግድ የሚመለከት ነገር ነው።

ጌታችን አርአያና ምሳሌ የሆነበት ዐቢይ ጾም ፈታኝ ወደእርሱ ቀርቦ እንዲመገብ ባዘዘው ጊዜ «ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ጭምር እንጂ» በማለት እንደመለሰ በማቴ. ፬፥፬ ተጠቅሶ እናገኛለን።

በጾማችን ወቅት ምግበ ሥጋ በማጣት የደከመ ሥጋ ብቻ ሳይሆን ቃለ እግዚአብሔርን የጠገበች ነፍስም ልትኖረን ያስፈልጋል። ያለዚያ ግን ምንም እንኳ ሥጋ ቢደክምም ነፍስ ከተራበች ኃጢአት ይሰለጥንባታል። በዚህ ምክንያት ጾማችን ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርበን ምሕረትና ቸርነትንም ሊያስገኝልን አይችልም። «የጠገበች ነፍስ የማር ወለላን ትረግጣለች፤ የተራበች ነፍስ ግን የመረረ ነገር ሁሉ ይጣፍጣታል።»/ምሳ. ፳፯:፯ /። ጽድቅን፣ ቃለ እግዚአብሔርን፣ ንስሐን የተራበች ነፍስ በሁሉም በጎ የሆነውን ፈቃደ እግዚአብሔር በመማር ያላወቀችና ከፈቃደ እግዚአብሔር የራቀች ነፍስ የመረረ ነገር፣ ኋጢአት፣ በደል፣ ክፋት ይጣፍጣታ። በኋጢአት በበደል በክፉ ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ባልሆነ ነገር ሁሉ ታስራ መከራዋን ታያለች። በቃለ እግዚአብሔር፣ በፍቅረ እግዚአብሔር፣ በንስሐ ፣በሥጋውደሙ የጠገበች ነፍስ ግን የዚህን ዓለም ተድላ ደስታ ምኞት ንቃ ትጠየፈዋለችና ከእግዚአብሔር ጋር አንድነቷን ታጠናክራለች።

በቅዱሳት መጻሕፍት ዜና ሕይወታቸው ተዘግቦ የምናገኘው ቅዱሳን ራሳቸውን አሳልፈው ለሞት እስከ መስጠት ዓለምን ንቀው ወደ በረሓ እስከ መመነን የሚደርሱት ነፍሳቸው በቃለ እግዚአብሔር የጠገበች በመሆኗ ነው።

ሊቀ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ በዱድያኖስና በሰብአ ነገሥታት ፊት በተጋደለበት ዘመን ዱድያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሊያታልለው ሞክሮ ነበር። በዚህ ዓለም የብዙዎች ስዎችን ልቡና የሚያነሆልሉና የሚያታልሉ ታላላቅ ገፀ በረከቶችን አቅርቦለት ነበር። ከነዚህም መካከል መኳንንቱና መሳፍንቱ የሚመኟት አንዲት ሴት ልጁን ሊድርለት ቃል መግባቱ ነበር። የመንግሥቱን እኩሌታም እንደሚሰጠው፣ ከእርሱ በታች ታላቅ ባለሥልጣን እንደሚያደርገው፣ በሰባ ሀገሮች ላይም እንደሚሾመው ቃል ገብቶለት ነበር። ይሁን እንጂ ነፍሱን በእግዚአብሔር ቃል ያጠገበ አባት ነበርና ዱድያኖስ ያቀረበለትን ማባበያ ንቆ በሃይማኖት ጸንቶ ተገኝቷል።

እስራኤላውያን በጾማቸው ወቅት ሥጋቸውን ከማስራብ በስተቀር ነፍሳቸውን ያጠገቡበት ሁኔታ አልነበረም። ነፍሳቸውም ሥጋቸውም የተራበች ነበረች። ከዚህ የተነሳ ነው እግዚአብሔር ሊጎበኛቸውና ሊመለከታቸው ያልቻለው። ስለዚህ የእኛም ጾም እንዲህ እንዳይሆን በምንጾምበት ጊዜ ጾማችን የግድ ከንስሐ፣ ከሥጋ ወደሙ፣ ከቃለ እግዚአብሔር ጋር አንድነት ሕብረት ያለው ሊሆን ይገባዋል። ሥጋን ብቻ አስርቦ ነፍስን የማያጠግባት ጾም መልስ የማያስገኝና የምሬተ ጾም ይሆንብናል።

በነብዩ በኤርምያስ ዘመን የነበሩ እስራኤላዉያን የተወቀሱበትን ሁኔታ ስንመለከት አንድ ነገር እንድናስተዉል ያደርገናል። «እንዲህ ትላቸዋለህ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የወደቁ አይነሰሡምን? የሳተስ አይመለስምን? እንግዲህ ይህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዘወትር ስለ ምን ወደ ኋላው ይመለሳል? ተንኰልን ይዞአል ሊመለስም ዕንቢ ብሎአል። አደመጥሁ ሰማሁም ቅንን ነገር አልተናገሩም፤ ማናቸዉም፦ ምን አድርጌአለሁ? ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፤ ወደ ሰልፍም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል። ሽመላ በሰማይ ጊዜዋን አዉቃለች ዋኖስና ጨረባ ዋልያም የመውጣታቸዉን ጊዜ ይጠብቃሉ፤ ሕዝቤ ግን የእግዚአብሔርን ፍርድ አላወቁም»።/ኤር. ፰፥፬-፯/።

እስራኤል በጾማቸው ወራት ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሳቸውን ንስሐ አልተጠቀሙበትም ነበርና ነዉ እግዚአብሔር ያልሰማቸው። ስለዚህ በጾማችን ወቅት ከመብል መከልከል ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነት ወደ እኛ እንዳይመጣ ያገደዉን ኃጢአት በንስሐ ልናስወግድ ይገባል።

የእስራኤል ጾም በልማድና በግብዝነት የተሞላ ነበር። ይህ ነዉ የልቡናቸው መሻት እንዳይፈጸም አንቆ የያዘው። ጾም ዓላማ ሊኖረው የሚገባ ድርጊት ነው። የሚጾም ሰው በጾሙ አማካኝነት ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ፤ የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነት እንዲደረግለትና ለልዩ ልዩ ዓላማ ሲጾም የጾሙ ማዕከላዊ ዓላማ ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር ሊጣጣም ይገባል።

ሥርዓቱ ስለተደነገገ ብቻ የሚጾም ጾም አላማዉን ግብ ማድረግ አይችልም። ልማዳዊ ብቻ ስለሚሆንም ዋጋ አያስገኝም። በመጽሐፍ ቅዱስ የጾሙ ሕዝቦችንና ግለሰቦችን ታሪክ በምናይበት ጊዜ ለጾማቸው ዓላማ ነበራቸው።

በዘመነ አስቴር የነበሩ አይሁድ ከክፉ ሀማ ምክር ይድኑ ዘንድ /አስቴ. ፬፥፲፮/ ፣ የነነዌ ሕዝቦች ከቁጣ እግዚአብሔር ያመልጡ ዘንድ /ዮና. ፫፥፭/፣ እነ ዳንኤል ምስጢር እንዲገለጥላቸው /ዳን. ፲፥፫/ ጾመዋል። ስለዚህ እኛም በምንጾምበት ወቅት እግዚአብሔር በእኛና በእርሱ መካከል ያለውን የአባትነትና የልጅነት መንፈስ እንዲያጠናክርልን፣ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን፣ ቀሪው የሕይወት ዘመናችንን እንዲባርክልን፣ በጾማችን ወቅት ሀገራችንን እንዲጎበኝልን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን እንዲጠብቅልን፣ ለቤት ክርስቲያን መሪዎች ሰላም ፍቅርና አንድነትን አድሎ ሕዝቡን በአንድ ልቡና እንዲመሩልን የመሳሰሉ ዓላማዎች ሊኖሩን ይገባል።

ከዚህ ዉጪ በልማድ ብቻ የሚደረግ ጾም ዋጋ የማያስገኝ ከንቱ ነው። ቀዱስ ጳዉሎስ የምታደርጉትን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድርጉ በማለት እንዳሳሰበን ጾማችንን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መሰረት ባደረገ ሁኔታ ብንጾም ይህ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛል። ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት ቸርነትና በረከትን ያሰጠናል በማለት ሊሆን ይገባል።

እስራኤል ከሌላው ጊዜ የጾማቸውን ወቅት የሚገልጠውና የሚያሳየው አስቀድመው በፍስክ ወቅት ይበሉት የነበራውን ነገር ትተው የምግብ ለውጥ ማድረጋቸው ብቻ ነው። ሌላ የሕይወት ለውጥ አይታይበትም። በቤተ ክርስቲያን ያለን ምእመናንም ጾማችንን በምናይበት ሰዓት ከዚህ የተለየ ሆኖ አናገኘውም። ከፍስኩ ወቅት ሥጋና የሥጋ ተዋጽኦዎችን እንመገብ የነበርን ሰዎች በጾማችን ትተነዋል ይሁን እንጂ በእርሱ ፈንታ ሥጋችንን ሊያዳብሩ የሚችሉ ምትክ ምግቦችን ምናልባትም በፍስኩ ወቅት በተሻለ ሁኔታ እንመገባለን። ያም ሆኖ ከምግብ ከመከልከል ዉጪ ሌላ ለዉጥ በሕይወታችን አይታይም። የጾም ወቅት ግን የአስተሳሰብ ለውጥ ልናሳይ የሚገባበት ወቅት ነው።

የጾም ወቅት ከሌሎች ጊዜያት ይልቅ ለአንደበታችን ልጓም የምናበጅበት ወቅት ነው። ባልንጀራን የሚያሳዝን ሰዎችን የሚያስከብር ዓላማዊ ሕይወትን የሚያደፈርስ በእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአት ሊሆን የሚችል ንግግርን ከአንደበታችን ልናርቅ የሚገባበት ወቅት ነው። የጾም ወቅት ንግግርን ብቻ ሳይሆን የአሠራርም ጭምር ለውጥ የምናመጣበት ነው። አስቀድመን እንሠራቸው የነበሩ የኃጢአት ሥራዎችን ትተን አባቶቻችን ቅዱሳን አበውንና እናቶቻችንን ቅዱሳን አንስትን በቅድስና የምንመስልበት ነው። የጾማችን ወቅት ፈቃድ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን የምናስገዛበት መልካዊ ባሕርያችን የሚያይልበት ወቅት ነው።/፩ ቆሮ. ፱፥፳፮-፳፯/።

በአጠቃላይ እንደ እስራኤል ዘሥጋ ዓይነት ጾም ጾመን «ስለምን ጾምን አንተም አልተመለከትኸንም» በማለት እንዳናማርር ጾማችን የምሕረትና የቸርነት ፍሬያት የሚገኙበት እንዲሆን የአጿጿማችንን ሁኔታ ልናየውና ልንመረምረው ይገባል።

እግዚአብሔር አምላካችን በነብዩ በኤዪኤል አድሮ «ጾምን ቀድሱ» ብሎ እንደነገረን ጾማችንን ከአሕዛብ ልማድና ከግብዝነት አካሄድ ለይተን እግዚአብሔር የሚገኝበትና ወድዶ ፈቅዶ የሚቀበለው ጾም ልናደርገው ይገባናል።/ኢዮ. ፪፥፲፭/። ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የድግል ማርያም አማላጅነት አይለየን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር