ሥርዓተ ጾም

ጾም ማለት መተው መከልከል ማለት ሲሆን፤ ለጊዜው ለተወሰነ ሰዓት ከማንኛውም ምግብና መጠጥ መከልከል በተጨማሪም የጾም ወቅት እስከሚፈጸም ከጥሉላት መከልከል ማለት ነው፡፡( ፍትሐ ነገስት አንቀጽ 15)፡፡

ጾም የሚያምረንን የሚያስጐመጀንን ሁሉ በመተው ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ የምናስገዛበት መሣሪያ ነው፡፡

ጾም ከእግዚአብሔር ጋር ያገናኛል፡፡ቅዱሳን ነቢያት ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ዋናው መሣሪያቸው ጾም ነበር (ዘì.34÷28) ፡፡ ጾም ከእግዚአብሔር ይቅርታን አግኝቶ መዓቱን በምህረት ቁጣውን በትዕግስት ለመለወጥ ይጠቅማል (ዮናስ.3÷7) (ኢዮ. 2÷12)

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ጾሞየጾምን አስፈላጊነት አሳይቶናል፡፡ ጾምን በሐዲስ ኪዳንም ጭምር እንደሚጠቅም ሲያመለክተን ወደ ምድር የመጣበትን ዓላማ በጾም ሲጀምር እናያለን (ማቴ. 4÷2)፡፡ ይሄንኑ አርአያ ተከትሎ ትእዛዘ እግዚአብሔርን ለመቀበል፤ እንዲሁም ዲያቆናትና ቀሳውስትን ሲሾሙ፤ ለመሳሰሉት አገልግሎቶች ቅዱሳን ሐዋርያትም ጾምን እንደ መሣሪያ ተጠቅመዋል (ሐዋ.13÷2)፡፡

ጾም ረቂቃን ክፉ መናፍስትን የምንዋጋበት ረቂቅ መሣሪያችን ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ርኩስ መንፈስ ካለጾምና ካለጸሎት ከሰው አይወጣም“ ብሎ በወንጌል ያስተማረው (ማር. 9÷2)፡፡

ጾም ይህን ሁሉ ጥቅም የሚያስገኝ ከሆነ፤ ጾማችን ትርጉም ያለውና ዋጋ የምናገኝበት እንዲሆን፣ ለሥጋዊ ፍትወት የሚያጋልጡ አመጋገቦችን ሥጋ፣ወተት፣ ቅቤ አልኮል ጨምሮ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡(ዳን. 10÷2)፡፡

እንዲሁም ለጾም ስንል የምንተዋቸውን ቁርስና ምሣ ለነዳያን ማካፈል ጾማችንን ፍጹም ያደርገዋል (ኢሳ. 58÷6)፡፡

በተጨማሪም ለሆዳችን መብልን እንደምንከለክል ዓይናችንን፣ ጆሮአችንን፣ ክፉ ከማየትና ከመስማት፣ እንዲሁም እጅና እግራችንን ወደ ክፉ ከመውሰድ አንደበታችንንም ክፉ ከመናገር መከልከል እንደሚገባ ታዟል (ማቴ. 5÷21)፡፡

እነሆ የጀመርነው ዓቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት ያሉት ሲሆን፤እንደ ቅዱስ ያሬድ ጾመድጓ የየራሳቸው ስም ተሰጥቷቸዋል ፡፡ እነሱም ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መጻጉዕ፣ ደብረዘይት፣ ገብርኄር ፣ ኒቆዲሞስ፣ ሆሳዕና ናቸው፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ጾሙን በሰላም እንዳስጀመረን፣ 

እርሱ እንደሚወደው እንደሚፈቅደው ጾመን እንድንፈጽም ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር