“ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ”

(ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ)

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር እጅግ የሚረቅ፣ የሚደንቅ፣ ከኅሊና በላይ የሆነ ነው። ሊቃውንቱንም እጅግ እያስደነቃቸው በተቻላቸው መጠን ለመግለጽ ይሞክሩና ከኅሊናቸው በላይ ሲሆን ዕፁብ ድንቅ እያሉት ያልፋሉ። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ውዳሴው “ኦ ዝ መንክር ልደተ  አምላክ እማርያም ቅድስት ድንግል አግመረቶ ለቃል ኢቀደሞ ዘርዕ ለልደቱ፤ ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ፣ ቃልን ወሰነችው ልደቱንም ዘር አልቀደመውም” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት በኅሊናው ላይ የተፈጠረውን አግራሞት ይገልጻል። እንዲህ ያለው ልዩ ምሥጢር የተገለጸለትና በአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ የኖረው ሊቁ ቅዱስ ሳዊሮስም “ወኮነ ሰማይ ዓለመ ወዓለምሂ ሰማየ፤ ሰማይ ዓለምን ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ” በማለት ተናገረ። እስኪ ምን ማለት እንደሆነ የተወሰነውን ምንባብ ጠቅሰን ዘርዘር አድርገን እንመልከተው።

…

“ወኮነ ሰማይ ዓለመ ወዓለምሂ ሰማየ፤ ወኮነ እግዚአብሔር ሰብአ በታሕቱ፤ ወረሰዮ ለሰብእ ውስተ አርያም በላዕሉ። ወስብሐተኒ ዘውስተ ሰማይ ኮነ ዲበ ምድር፤ ዘሀሎ በሕጽነ አቡሁ ኮነ በሕፅነ ማርያም፤ ወለዘወለዶ እግዚአብሔር አብ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ መንጸፈ አንስት፤ ወለደቶ ማርያም በሥጋ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ ሩካቤ ተባዕት፤ ሰማይ ዓለም ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ተገኘ ሰውንም በላይ በአርያም አደረገው፤ በሰማይ የሚቀርበው ምስጋና በዚህ ዓለም ተደረገ (መላእክትና ደቂቀ አዳም በአንድ ቦታ ተገልጠው አመሰገኑ) ። በአብ ኅሊና ያለ እርሱ በእመቤታችን ክንድ ተይዞ ታየ። እግዚአብሔር አብ በማይመረመር ምሥጢር ያለ እናት የወለደውን ማርያም በማይመረመር ምሥጢር ያለ ዘርዐ ብእሲ በሥጋ ወለደችው።” (ሃ.አበ. ዘሳዊሮስ ፹፭፥፴፯) ከዚህ ምንባብ በርከት ያሉ  ነጥቦችን ማንሣት ቢቻልም። ጉዳዩ ሰፊ በመሆኑ በዚህ ጽሑፍ የተወሰኑትን ብቻ እንደሚከተለው እንመለከታለን።

.

 ፩. አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ

Pin on Icônes Ethiopiennes - Ethiopian Icons

 ሊቁ የአምላክን ሰው መሆን የሰውን አምላክ መሆን “ወኮነ እግዚአብሔር ሰብአ በታሕቱ፤ ወረሰዮ ለሰብእ ውስተ አርያም በላዕሉ፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ተገኘ ሰውንም በላይ በአርያም አደረገው” በማለት ገለጸልን። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ለማዳን ሰው ሆነ፤ አምላክ ሰው በሆነ ጊዜ ሰውም አምላክ ሆነ። ጥንት እግዚአብሔር የእርሱን የባሕርይ አምላክነት፣ ገዢነት፤ ልጅነት ወዘተ በጸጋ አድሎት፣ ፍጥረቱን ሁሉ እንዲገዛ ፈቀደለት። ግን አታድርግ የተባለውን ሲያደርግ የተሰጠውን ጸጋ ሁሉ ተነጠቀ። ይህ የተነጠቀው ጸጋ ይመለስለት ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ።  የሰው ልጅ ይድን ዘንድ አምላክ ሰው መሆኑን አስመልክቶ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ መጽሐፈ ምሥጢር በተሰኘ መጽሐፉ የሚከተለውን ይነግረናል። “ባለመድኃኒቱ በድውዮች ሴት ልጅ አደረ ከእርሷም ምድራዊት ሥጋን ተዋሐደ ለድውዮችም ፈውስ በሚሆን ገንዘብ ከመለኮቱ ጋር ገንዘብ አደረገው። ባለመድኃኒት ከሰማየ ሰማያት መጥቷልና የፈውስ እንጨትም በዳዊት ቤት ተገኘ። መለኮት ከሥጋ ጋር ሳይዋሐድ ፈውስ እንደማይሆን ባለመድኃኒቱ አወቀ።  ስለዚህ ራሱን ሰው ለመሆን ሰጠ።” (መጽሐፈ ምሥጢር ፳፥፯) ሁሉን የሚያድን አምላክ ለሰው ልጅ መድኃኒት ያደረገው ራሱ ሰው መሆንን ነበር። በመሆኑም አምላክ ሰው ሲሆን ሰውም አምላክ ሆነ። ሊቁም የነገረን ይህን ነው።

 ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ቅድስት ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ውዳሴ ማርያም “ወኮነ ሰብአ ከማነ ዘእንበለ ኀጢአት ባሕቲታ፤ ከኀጢአት ብቻ በቀር እንደኛ ሰው ሆነ።” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት የተናገረውን መተርጕማኑ “ባሕርያችንን እንደተዋሐደ ሲናገር እንደኛ ሰው ሆነ አለ። ከግብራችን እንደለየው ሲናገር ደግሞ ከኀጢአት ብቻ በቀር አለ” በማለት አብራርተውታል። ሰው የሚባለው አራቱ ባሕርያተ ሥጋና ሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ በተዋሕዶ አንድ ሆነው ነውና። አምላክ ሰው ሲሆን ሰው አምላክ ሲሆን ባሕርየ ሥጋን ባሕርየ ነፍስን ሲነሣ ሥጋም ባሕርየ መለኮትን ገንዘብ ሲያደርግ ረቂቁ መለኮት ገዘፈ ግዙፉ ሥጋ ረቀቀ፤ ውሱኑ ሥጋ መላ ምሉእ መለኮት ተወሰነ። አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ ማለት ይህ ነው። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ይህን ልዩ ምሥጢር “ኑ ይህን ድንቅ ምሥጢር እዩ ሰው የማይሆን ሰው ሆነ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ተቆጠረለት የማይታይ ታየ የማይታወቅ ታወቀ።” (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ) በማለት ከአድናቆት ጋር ያስረዳል።

…

ስለዚህ ሰማይ ዓለምን ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ” ማለት ልዑለ ባሕርይ ሰማያዊ አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሰው ሆነ፤ በዚህ ዓለም ተገለጠና ለሰው ሁሉ ታየ፤ ምድራዊው ሰው በተዋሕዶ የመለኮትን ገንዘብ ገንዘብ አድርጎ ሰማያዊ አምላክ ሆነ ማለት ነው። ይህ ምሥጢር በተዋሕዶ የተፈጸመ መሆኑን ሲያስረዳ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “በእንተ ሥጋ ወነፍስ ዐፅም ወደም ፀጕር ወአሥራው ዘነሣእከ እምኔሃ ወረሰይኮን አሐደ ምስለ መለኮትከ ዘእንበለ ፍልጠት ወኢውላጤ ዘእንበለ ቱስሕት ወኢቡአዴ በከመ መሐሩነ አበው፤ ከእርሷ የነሣሃቸውን ሥጋና ነፍስ፣ አጥንትና ደም፣ የሰውነት ክፍሎችም አባቶቻችን እንዳስተማሩን ያለመለየት፣ ያለመለወጥ፣ ያለመጨመር፣ በተዋሕዶ ከመለኮትህ ጋር አንድ አደረግሃቸው። (መጽሐፈ ሰዓታት) በማለት ያስረዳል። ፪. አብ የወለደውን ድንግል ማርያም ወለደችው  ሊቁ ከላይ በገለጽነው ምንባብ ከሚናገራቸው ነጥቦች መካከል አንዱ አብ የወለደውን ድንግል ማርያም ወለደችው የሚለው ነው። ይህን ሲገልጽ “ወለዘወለዶ እግዚአብሔር አብ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ መንጸፈ አንስት፤  ወለደቶ ማርያም በሥጋ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ ሩካቤ ተባዕት፤ በማይመረመር ግብር አብ ያለ እናት የወለደው እርሱን፤  በማይመረመር ተዋሕዶ እመቤታችን ያለ አባት ወለደችው” በማለት ልደቱን ብቻ ሳይሆን  ልደቱ የማይመረመር እና ረቂቅ ምሥጢር እንደሆነም ይነግረናል። የሰውን ልጅ ለማዳን ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደው ወልድ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው ነው።

…

ይህን በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ፤ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ” (መዝ.፻፱፥፫) በማለት ነገረን። መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞንም “ተራሮች ሳይመሠረቱ ከኮረብቶች በፊት ወለደኝ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ በታች የሚታደርባቸውን ሀገሮችንና ዳርቻዎችን ሳይፈጥር ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬው ነበርሁ። ዙፋኑን በነፋሳት ላይ ባጸና ጊዜ፣ የቀላያትን ምንጮች ባጸና ጊዜ፣ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ የምድርን መሠረት ባጸና ጊዜ እኔ ከእርሱ ጋር እሠራ ነበር” (ምሳ.፰፥፳፭-፴) በማለት ቅድመ ዓለም መወለዱን፣ እንዲሁም በአንዲት ሥልጣን ከባሕርይ አባቱ ጋር ዓለምን የፈጠረ መሆኑን ያስረዳናል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ” (ዕብ.፩፥፩) በማለት እንደነገረን ጥንት በአበው ምሳሌ ሲያስተምር በነቢያት ትንቢት ሲያናግር የነበረው አምላክ በኋላም በሐዋርያት እንደተመሰከረለት ሊቃውንቱም አምልተውና አስፍተው አስረዱን። ረቂቁን ምሥጢር እግዚአብሔር በገለጸላቸው መጠን ገለጹልን። ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት የተወለደው ድኅረ ዓለም ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት መወለዱን ወልደ አብ ወልደ ማርያም መሆኑን አባቶቻችን ሊቃውንት በስፋት ገልጸው ነገሩን።

…

የተዋሕዶ መዶሻ እየተባለ የሚጠራው ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ “ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይመረመር ተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነውና ቀዳማዊ ሲሆን ከዘመናት አስቀድሞ ከአብ የተወለደ ነው፤ ዳግመኛም ከድንግል በሥጋ የተወለደ ነው ተብሎ ስለ እርሱ እንዲህ ይነገራል።” (ሃ.አበ.ምዕ ፸፫ ክፍል ፲፩ ቁ. ፬) በማለት ያስረዳል።  ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ “በምድራዊ ልደቱ አባት አለው አትበሉ፤ በሰማያዊ ልደቱም እናት አለችው አትበሉ፤ እርሱ በምድር አባት የሌለው ነው፤ በሰማይም እናት የሌለችው ነው።” በማለት ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት መወለዱን አስረዳን። ሊቁ እንዲሁ ተወለደ በሚል ቃል ብቻ አይደለም የገለጸው በሰማይ እናት አትፈልጉለት፣  በምድር ደግሞ አባት አትፈልጉለት በማለት በውስጣችንም ሊነሣ የሚችለውን ጥያቄ ግሩም የሆነ መልስ በመስጠት መጨነቅም እንደሌለብን ያስረዳል። አንድ ሰው ተወልዶ እስኪያድግ ድረስ ጡት እያጠባች የምታሳድገው እናት፣ ከእናቱ ጋር እየተንከባከበ የአባት ፍቅር ሰጥቶ የሚለብሰውንና  የሚጎርሰውን እያዘጋጀ የሚያሳድገው አባት ይፈልጋል። ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለሰማያዊ ልደቱ እናት ለምድራዊ ልደቱ አባት እንደማያስፈልገው ሊቁ ጎርጎርዮስ “በሰማያዊ ልደቱ ጡት አጥብታ በወተት የምታሳድገው እናት አትሹለት፤ በሰማያዊ ልደቱ እናት የለችውምና መለኮቱን ከትስብእቱ ልዩ ነው አትበሉ፤ መለየት በሌለበት በእርሱ ክፉ መለየት እንዳይመጣ። (ሃ.አበ ምዕ.፴፭ ክፍል ፪ ከ፲፮-፲፰)  በማለት ምሥጢረ ሥጋዌን በአግባቡ እንድንረዳ አምልቶና አስፍቶ ይነግረናል። ከበረከተ ልደቱ ያሳትፈን አሜን።

ምንጭ: ሐመር መጽሔት (ፀሀፊ: ዲ/ን ዐቢይ ሙሉቀን)

በጣም ጥቂት ማስተካከያ ተደርጎበታል።