በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን

መጻጉዕ እና ልግሥና

እንደ ቅዱስ ያሬድ ጾመድጓ የአቢይ ጾማችን አራተኛ ሳምንት መጻጉዕ ሲሆን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሠላሳ ስምንት ዓመት በአልጋ ላይ የዋለውን ሕመምተኛ የፈወሰበት መታሰቢያ ነው፡፡(ዮሐ 5÷1-25)

ቤተሳይዳ የምህረት በር ማለት ሲሆን በኢየሩሳሌም አቅራቢያ የምትገኝ መጠመቂያ ነበረች፡፡ በዚያች ሥፍራ በየዓይነቱ ደዌ የወደቀባቸው ሰዎች ለመፈወስ የተኙባት  ሲሆን፤ ከሁሉ የባሰው ከአልጋው ወርዶ መነከር ተስኖት ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በዚያ የቆየው ሰው ነው፡፡ በአይሁድ በዓል ቀን ይኸውም በቀዳሚት ሰንበት ወደ መጠመቂያዋ የወጣው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ሰው ቀርቦ ከጠየቀው በኋላ ከብዙ ዓመታት የበሽታ ቀንበር ፈቶ አልጋውን ተሸክሞ እንዲሄድ አድርጐ ፍጹም ፈውስ አድሎታል፡፡

ጌታችን አምላካችን ይህንን ሰው የጐበኘው በበዓል በሰንበት ነበር፡፡ እኛም የተጨነቁ፣የተቸገሩ፣ የታመሙ፣ ያዘኑ፣ የተራቡ፣የተጠሙ፣ የታሰሩ… ወዘተ ሰዎችን በተለይም በዓላትና በሰንበት ልንጐበኛቸው ይገባናል፡፡ ቤተሳይዳ አምስት መግቢያዎች እንደነበራት፣ እኛም አምስቱ አእማደ ምሥጢርን አውቀንና አምነን በሃይማኖትም ጸንተን፣ለሌሎች መልካም ማድረግን ከዚሁ ታሪክ እንማራለን፡፡

የጐደለባቸውን ሰዎች ካለን ላይ አካፍለን፣ከሌለንም ደግሞ ጐብኝተን የማጽናናት ቃላትን በእግዚአብሔር ስም አድለን መመለስ እንችላለን፡፡ ካለን ላይ በመለገስም ሰውን በሰውነቱ አይተን እንጂ አውቀዋለሁ ወገኔ ነው፣ በማለት አዳልተን ሳይሆን ለባሰበት ትኩረት እየሰጠን እንዲሆን ሊቃውንት ያስተምሩናል፡፡ በቅዱሳን ስም የምንዘክረውም ቢሆን ምስኪኖች እንዲለብሱ እንዲበሉ እንዲጠጡ እና ከረሃብ ከቁር እንዲድኑ እንጂ እኛው እርስ በርስ ለመቋደስ አይደለም።

ነዳያን ጠግበው እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ እኛንም እንዲመርቁን መሆን ነው ያለበት፡፡

በምድር ብድራትን መመለስ ለማይችሉ በሰማይ ግን የማያልፍ ዋጋን ለሚያሰጡ  የመንግስት ሰማያት በሮች ለተባሉ ነዳያን መራራት ይገባል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሰ የተቸገረውን መጻጉን አውቆ እንደጐበኘው፤ እኛም ከብዙሃኑ ተለይተው የተቸገሩትን ማየት ይገባናል፡፡ ሰው ሁሉ ቆሞ እየሄደ ተለይተው የወደቁትን፤ሌላው በቤቱ እየኖረ ደጅ  የተጣሉትን፤ ከወገን ተለይተው የተሰደዱትን አውቀን መጠየቅ ቀና ማድረግ፣ መደገፍ ይጠበቅብናል፡፡ የምናደርገውም በከንቱ የሚቀር ሳይሆን በእግዚአብሔር ሕሊና የሚታሰብ ዘለዓለማዊ ዋጋ የሚያሰጥ ነው፡፡

ለተቸገረ የሚሰጥ ለእግዚአብሔር እንደሚያበድር ነው፡፡ “ስጡ ይሰጣችኋል“ እንደተባለ መስጠታችን በበረከት ያበዛልናል እንጂ አያጐድልብንም ፡፡ ባይኖረንም መልካም ቃላት አናጣምና፤ እግዚአብሔር ይስጥህ፣ እግዚአብሔር ይማርህ፣ እግዚአብሔር ያስፈታህ ማለትን ለሌሎች መጸለይን መልመድ አለብን፡፡

ሌሎችን ለማገዝ ስንል የምናወጣው ድካም ጥቂት ነው፤ ዋጋው ግን ሰማያዊና ዘለዓለማዊ ነው፡፡ “ በጥቂት ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ“ እንደተባለ (ማቴ. 25÷14) በምድር ላይ ባለን ጥቂት እድሜ የምንሰራው ጽድቅ በሃይማኖት ፍጻሜ የሌለውን ዘለዓለማዊ ደስታ የሚያጐናጽፈን ነው፡፡ ሰማያዊ መንግስትንም የሚያወርሰን ነው፡፡ በምድር ላለ ዘመናችንም ቢሆን ለሌሎች የምናስብ ከሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ያስብልናል፡፡ በችግራችንና በሕመማችን ጊዜ የነዳያን አምላክ ይደርስልናል፡፡ ለድሆች የሚያስብ ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር በችግሩ ጊዜ ይደርስለታል፣ ከህመሙ ፈውሶ ከወደቀበት አልጋ ፈጥኖ ያነሳዋል ተብሎ በመዝሙር እንደተጻፈ (መዝ 40÷3)

ወስብሀት ለእግዚአብሔር