ሆሳዕና በአርያም – በሰማይ ያለ መድኃኒት!

/አክሊለ ሰማዕት/

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኢያሪኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ፤ በደብረዘይት አቅራቢያ ወደምትገኘው ቤተፋጌ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላካቸው፡፡ አህያ ከነውርንጭላዋ ታስረው እንደሚያገኙ ከነገራቸው በኋላ “ፈታችሁ አምጡልኝ“ (ማቴ.21÷2) አላቸው፡፡

ደቀመዛሙርቱም አህያዋን ከነውርንጭላዋ ፈቷቸው፡፡ ለምን  ትፈታላችሁ? ተብለው ሲጠየቁም ጌታቸው ይፈልጋቸዋል አሉ፡፡ በሥነ-ፍጥረት ንብረቱ ናትና አህያዋን ጌታዋ ይፈልጋታል ተባለ፤ ሊቀመጥባትም መጣችለት፡፡ ልብሳቸውን በአህያዎቹ ላይ ደለደሉለት፡፡ ልብስ መደልደሉ ለምቾት ይጠቅማልና የምትመች የማትቆረቁር የወንጌልን ሕግ ሠራሁላችሁ ሲል ልብሳቸውን ጐዘጐዙለት፡፡ ልብስ በአካል ያለውን ነውር ይሰወራልና አቤቱ አንተ የኃጢአትን ነውር በይቅርታ የምትሸፍን ቸር ነህ ሲሉ ልብሳቸውን ደልድለውለታል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአህዮቹ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ፡፡ አስቀድሞ በነቢዩ ዘካርያስ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፤እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ፡፡ እነሆ ንጉስሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፡፡ ትሁትም ሆኖ በአህያም፤ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡“ (ዘካ 9÷9) ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡

በአህያ የተቀመጠበት ምክንያት አንዱ ይሄንን ትንቢት መፈጸም ሲሆን፤ በተጨማሪም አህያ የትህትና የየዋህነት ምሳሌ ናትና፣ በመሃይምናን በየዋሀን አድሬባቸው እኖራለሁ ሲል ነው፡፡ በተጨማሪም አህያ እንደፈረስ ፈጥና አታመልጥም አሳዳም አትደርስምና ጌታችንም ከፈለጉኝ አያጡኝም፤ ካልፈለጉኝ አያገኙኝም ሲል በአህያ ተቀምጧል፡፡

በእናትና በውርንጫ አህያዎች ላይ በየተራም ቢሉ በተአምራት በሁለቱም ላይ ቢሉ መቀመጡስ ለምንድነው? ቢሉ፤ እናቲቱ አህያ ጭነት የለመደች ናት፡፡ ውርንጫይቱ አህያ ግን ለሸክም አዲስ ናት፡፡ ይኸውም የእስራኤል እና የአህዛብ  ምሳሌ ነው፡፡ እስራኤል በሕገ ኦሪት የኖሩ ሕግ የለመዱ ሲሆኑ፤ አህዛብ ግን ለሕግ አዲስ ናቸው፡፡ ጌታችን ግን ሕዝብ  የተባሉ እስራኤልንም አህዛብንም እኩል እንደሚፈልጋቸው ሲያጠይቅ በአህያይቱና በውርንጭላዋ ተቀመጠ፡፡

በአህዮቹ ፊትም ሕዝቡ ሁሉ ልብሳቸውንና ቅጠል ያነጥፉ ነበር፡፡ ዘንባባም ይዘው ትንሹም ትልቁም ያመሰግኑት ነበር፡፡ ዘንባባ የሚወጋ የእሾህ ዓይነት ጫፍ አለውና አይደፈርም። ጌታችንንም ኃይልና ድል መንሳት ያንተ ነው ሲሉ ዘንባባ ይዘው አመስግነውታል፡፡ የዘንባባ ፍሬው ከመሬት እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ጌታችንን የማትመረመር ልዑል ነህ ሲሉ ዘንባባ ይዘዋል፡፡ ከፊት ከኋላ ከቀኝ ከግራ ብዙ ሺህ ሕዝብ እየተቀባበሉ እያመሰገኑት ተጓዘ፡፡ “ያቺ ዕለት እግዚአብሔር ሥራ የሰራባት ናት፤ በእርሷ ፈጽሞ ደስ ይበለን፡፡“ (መዝ.117÷24) እንደተባለ፤ እግዚአብሔር አጋንንትን አጥፍቶ ነፍሳትን ነጻ አውጥቶ የማዳን ሥራውን የሚሠራበት ዕለተ አርብ ቀርባለችና በእርሷ ደስ ይበለን የሚል ትርጉም እናገኛለን፡፡

ከዕለተ ስቅለት በፊት ባለችው በመጨረሻዋ እሁድ “በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው“ እያሉ አመስግነውታል፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር አብ መስክሮለት የመጣ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነው ማለት ነው፡፡ ከሞት ያስነሳው ዓልአዛርም ከፊት ከፊት እየሄደ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ እያዩት ጌታችንን ያመሰግኑት ነበር፡፡ ዓልአዛር የጌታችን አምላክነት ምሥክር ሆኖ ብዙ ሕዝብ እርሱን እያዩ ፈጣሪ ጌታ መሆኑን አምነው በምሥጋና በውዳሴ ይከተሉት ነበር፡፡

“ከሚጠቡና ከሕጻናት አንደበት ምሥጋናን አዘጋጀህ “(መዝ.8÷2) እንደተባለ አፋቸውን ያልፈቱና በእናታቸው እቅፍ ያሉ ሕጻናት እንኳን ሳይቀሩ አመሰግነውታል፡፡ሆሳዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነውና መድኃኒት መባል ለአንተ ይገባሃል እያሉ አመስግነውታል፡፡ ወደኢየሩሳሌም በቀረቡ ጊዜም ከተማዋ ተጨነቀች፣ታወከች የፊቱ ብርሃን ከፀሐይ ይልቅ ሲያበራ አይታ፤የሕፃናቱን ደማቅ ምስጋና ሰምታ ደስ ሊላት ሲገባ ታወከች፡፡ ይህ በዚህ ያለ ምስጋና የመጣው ማነው? አለች፡፡

አምላክ ወልደ አምላክ፣መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት፣ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል፤ ሆሳዕና በአርያም ማለትም በሕልውናው በሰማያት ያለ መድኃኒት፤ ሥጋን ተዋህዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በገሊላ ናዝሬት ያደገው ኢየሱስ ክርስቶስ (ማቴ 11÷21) እርሱም እግዚአብሔር ነው፡፡

የጉዞውን መጨረሻ ያደረገው ቤተ መቅደስን ነበር፡፡ መገኛው ቤተ መቅደስ፣ አማናዊና ዘለዓለማዊ መሥዋዕትም እርሱ ነውና በኦሪት መሥዋዕት የነበሩትን ርግብ፣ ወይፈን የመሳሰሉትን ከመቅደስ አስወጣቸው፡፡ በሰማያት ዙፉኑ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የሚመሰገን እርሱ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ በምድር በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ በትንሹም በትልቁም ተመሰገነ፡፡ ስለዚህም ፍጥረቱን የሚንቅ ተፈልጐም የሚታጣ አምላክ አይደለምና ፈጥነን እንፈልገው፤ ተሥፋ አንቁረጥ፡፡አህያን ጌታዋ ይፈልጋታል ያለ አምላክ አኛን ከኃጢአት እስራት ሊፈታን የማይፈልግበት ምክንያት የለም፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከፈለግነውና ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በልተን ጠጥተን መክበር ከፈለግንም በቤተ መቅደስ እንፈልገው፡፡ ቤቴ ብሎ በጠራትና የሐዲስ ኪዳን ቤተመቅደስ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሥጋው ሲወራረድ ክቡር ደሙ ሲቀዳ እናገኘዋለን፡፡ (ማቴ.21÷13)

ወስብሀት ለእግዚአብሔር