(ያለው ማማሩ ) ማቴ. 25፥29
/ሊቀጠበብት ማኅቶት የሻው/

.

ገብር ኄር ተብሎ በቅዱስ ያሬድ ስያሜ አማካኝነት ባገኘነው የዓቢይ ጾም
6ኛው ሳምንት በኩል የሚያስተምረን ትምህርት “ያለው ማማሩ” የሚለውን አባባል አውን ያደርግልናል እኛም ያለው ማማሩ ከሚሉት ሳይሆን ያለው ማማሩ ከሚባልላቸው ያድርገን።

የሀገሬ ሰው ለነገሮች አጽንዖት ሰጥቶ ሲናገር ዝም ብሎ አይደለም : ሰው አዲስ ልብስ በተለይም ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ፋሽን ወይም ጌጠኛ ልብስ ለብሶ ሲታይ ሌላኛው ተመልካች (ያለው ማማሩ) ይላል: በገጠር ትጉህ ገበሬ ዝናቡን ጭቃውን ብርዱን ፀሐዩን ረሀቡን ችግሩን ተቋቁሞ ብዙ አምርቶ ሲያስገባ የኔ ቢጤ ሰነፍ ደግሞ ቁጭ ብሎ በማየት ያለው ” አይ ማማሩ” ይላል: ይሄው ታታሪ ገበሬ ከንሰሐ አባቱ ጋር በመመካከር ዝክር ማኅበር ሰንበቴ ደግሶ ህዝብን ጠርቶ ሲያበላ: ሌላኛው የኔ ቢጤ ሰነፍ ድግሱን በልቶ ሲመለስ “ያለው ማማሩ” እያለ ይኖራል:: ታታሪው ደግሞ በተሰጠው አቅምና ዕውቀት ለፍቶ አጠራቅሞ ቤትና የመሣሰሉት አስፈላጊ የሆኑ ቁሣቁስ ብቻ ሲገዛ: ሌላው ባልባሌ ነገር ገንዘብ ሲያጠፋ የሚውለው ደግሞ ያለው ማማሩ ይላል:: እንደዚሁም ደግሞ ባለጸጋ ሰው በአደባባይ ሲናገር ተቀባይነት ካገኘ ሌላኛው የኔ ቢጤ ያለው ማማሩ ይላል: እንዲሁም አንደኛው ምስኪን ድሃ የነበረው በሆነ አጋጣሚ ሥልጣን ቢያገኝ እና ሰዎችን ለሥራ ሲያዝ ወይም መመሪያ ሲሰጥ ቢታይ ያለው ማማሩ ይባልለታል:: ገንዘብ አለው እሚባል ሰው ሰርግ ደግሶ ህዝብ ከጠራ ሁሉም ከተጋበዘ በኋላ ያለውን ሰጥቶ ሳይሆን ያለው ማማሩ ብሎ ይመለሳል ። እንደ እውነት ከሆነ ካለን ላይ ምስጋና ( ሞራል) እሚጨመርልን ከሆነ የሆነ ነገር ሊኖረን እና ያለንንም ልንጠቀምበት ግድ ይለናል ። ዛፍም እሚያምረው ግንዱ ብቻውን አይደለም ለምለም ቅጠል ካለው ያምራል : ቅርንጫፎች ካሉት በጣም ያምራል : ፍሬ ካለው ደግሞ እጅግ በጣም ያምራል ፈላጊውም ይበዛል ለሌላውም ይተርፋል እንዳይቆረጥም ይጠበቃል:: ያለው ማማሩ አይደል:: በዚህ በገብር ኄር ውስጥ ጌታችን አምላካችን መድኃኔዓለም በምሳሌ ያስተማረን ይሄን ነው:: ” ያለው ማማሩ” ማቴ. 25

የሠራ እንደሚመሠገን ሰነፍ እንደሚቀጣ ግልጽ አድርጎ እራሱን በባለጸጋ: እኛን እንደየሥራችን በሠራተኞች : የሚሠጠውን ጸጋ እንደገንዘብ መስሎ አስተምሮናል:: እሚገርመው አና እሚያሰደነግጠው የመጨረሻው ቃል ነው: ያልሠራውን ወቅሶ ያለችውን ገንዘብ ነጥቆ ያለው ማማሩ ነውና ላለው ጨመረለት ። መንግሥተ ሰማያትን ያህል ርስት ያለ ሥራ አይገኝም:: ለዚህ ነው ብዙ ወገኖቻችን በብዙ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ እያወጡ ቤተ ክርሰቲያንን የሚያሠሩት:: ብዙ ሰዎች ገንዘባቸውን ያለአራጣ የሚያበድሩት :: ሥጋቸውን በመጎሰም በጾም እራሳቸውን የሚያደክሙት ለዚህ ነው:: በየጊዜው ንስሐ እየገቡ ከሥጋ ወደሙ የማይለዩት፣ ብዙ ሰዎች ይቅር ባይና አስታራቂ የሚሆኑት ለዚህ ነው:: አምላካዊ ምስጋናን በመሻት አፋቸውን ለጸሎት እጃቸውን ለምጽዋት ልባቸውን ለቅንነት የሚያስገዙት ። ክብር ምስጋና ይግባውና እግዚአብሔር ሲሰጥ አያዳላም እንደየአቅሙ ይሰጣል:: (1ቆሮ. 12፥4) ችግሩ የተሰጠንን መክሊት ቀብረን ማስወሰዳችን ነው:: ከሠራንባት አንዷ ቅንጣት ሰላሣ ስልሣም ከዛም በላይ ሁና ታፈራለች ።
.
ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጆች የተሰጠንን ሙሉ መክሊት በሙሉ እምነት በሙሉ ትጋት በሙሉ ፍላጎትና አቅም ሠርተን: ሙሉ ደመወዛችንን መንግሥተ ሰማያትን እንድንቀበል አምላከ ቅዱሳን ይፍቀድልን ።

“ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እነጅ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ተጠንቀቁ”
2ዮሐ. 1፥8