ሐዊረ ሕይወት

በካናዳ ማዕከል ማኅበረ ቅዱሳን የቶሮንቶና የሳውዝ ዌስት ኦንታርዮ ንዑሳን ማዕከላት አስተባባሪነት በጓልፍ ክፍለ ከተማ ወደሚገኘው የሊቀ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ መጋቢት 10, 2015 ዓ.ም.  የተካሄደው የሐዊረ ሕይወት መንፈሳዊ መርኃ ግብር እጅግ በጣም ጥሩ በሆነ መልኩ ተከናውኗል::

ከቶሮንቶ አቡነ ተክለሃማኖት ቤተ ክርስቲያን በተዘጋጀው አውቶቡስ የመጡት አባቶች ካህናትና ምዕመናን፣ በዝማሬና በቃለ እግዚአብሔር እያመሰገኑ በጓልፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በመድረስ ያስቀደሱ ሲሆን፣ ከኪችነር ሐመረ ኖኅ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያንም ካህናት፣ ዲያቆናት እና ምዕመናን ተገኝተዋል:: በተጨማሪ በየግል መኪናቸው የመጡትን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን በመገኘት መርኃግብሩን ተሳትፈዋል:: ከዕለቱ የደብረዘይት በዓል እና የሰንበተ ክርስቲያን የቅዳሴ አገልግሎት በኃላ በአዘጋጆች የቀረበውን የፍቅር ማዕድ(ምግበ ስጋ) ተመግቦ በቀጥታ ወደ ዋናው ዝግጅት በመሄድ ሙሉ መርኃ ግብሩ በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ አልዓዛር አድነው የኪችነር ሐመረ ኖኅ ኪዳነምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ተመርቷል::

የመክፈቻው መዝሙር ተተኪ ትውልድ በሆኑ ህፃናት መዘምራን የበገና ዝማሬ ከቀረበ በኃላ በቀሲስ መምህር ቤዛ የዕለቱ የስብከተ ወንጌል ትምህርት በሚገባ ተሰጥቷል:: በመቀጠልም በሊቀ ጠበብት ማኅቶት የሻውና በቀሲስ ፍስሃ በኩል የምክረ አበው ዝግጅት የቀረበ ሲሆን፣ በዚህም የተለያዩ ቤተሰባዊና መንፈሳዊ እንዲሁም ወቅታዊ ጥያቄዎችን በመመለስ ድንቅ መንፈሳዊ መልዕክት ተላልፎበታል:: የማኅበሩ አባላት ዘማርያንም ጥዑም መንፈሳዊ ዝማሬን አቅርበዋል::

ስዕለ አድህኖ ለጉባኤው በእጣ ቀርቦ በመሸጥና፣ በወንድም ቴዎድሮስ ደስዬ መሪነት የመንፈሳዊ ጥያቄና መልስ ዝግጅት በማቅረብ ጥያቄዎቹን ለመለሱ ምዕመናን የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል:: በመጨረሻም ወንድም ሳሙኤል ስለ ማኅበረ ቅዱሳን እንቅስቃሴና እና ወቀታዊ የአገልግሎት መረጃዎችን በተመለከተ ለጉባኤው መልዕክቱን አስተላልፏል::

በዚህ የሐዊረ ሕይወት መርኃ ግብር ላይ ወሳኝ የነበረው የህፃናት እና የወጣቶች አገልግሎት ልጆቹን በሁለት ጉሩፕ በመክፈል የስብከት፣ የጥያቄና መልስ እንዲሁም የተለያዩ መንፈሳዊ ውድድሮችን በማካሄድና ሽልማቶችን በመስጠት እጅግ መልካም መንፈሳዊ ግዜን ማሳለፍ ተችሏል:: በጠቅላላው የማኅበሩ አባላት እና ምዕመናን በሙሉ በሁሉም የአገልግሎት ዘርፍ ከመቼውም በላይ በፍቅር እና በትጋት በመሳተፍ እንዲሁም የጎደለቦታን በመሙላት እና በማስተባበር እጅግ ከፍተኛ የበረከት አገልግሎትን ያሳዩ ሲሆን መርኃግብሩ በአባቶች ቡራኬ ከተዘጋ በኃላም አባላቱ እና ምዕመናን የማስታወሻ ፎቶ በመነሳት በኅብረት ጥሩ ጊዜ አሳልፈዋል:: ስለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን ::