ሐዋርያዊ ጉዞ

በቶሮንቶ የማኅበረ ቅዱሳን ንዑስ ማዕከል አስተባባሪነት ልዩ ልዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብሮች የተካተቱበትና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት የሐዊረ ሕይወት መንፈሳዊ ጉዞ  በደማቅ ሁኔታ ተከናውኗል:: ላለፉት ሁለት ዓመታት በተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በአካል ሳይደረግ የቆየው ጉዞ፣ መነሻውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደብረ ገነት አቡነ ተክለሃይማኖት ደብር  በማድረግ ፣ ከቶሮንቶ ከተማ በ 128 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ኪችነር ከተማ  ወደምትገኘው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሐመረ ኖህ ኪዳነምህረት እሁድ ሰኔ 26,2014ዓ.ም.  /ጁላይ 3, 2022/ በቶሮንቶ እና አካባቢው የሚገኙ በርካታ ምዕመናን ያሳተፈ መንፈሳዊ ጉዞ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል። በካናዳ የሰዓት አቆጣጠር ከንጋቱ 5:00 ሰዓት ከቶሮንቶ የአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የተነሱት አውቶቡሶችና እጅግ ብዛት ያላቸው የግል መኪናዎች: ካህናት አባቶችንና ምዕመናን  ይዘው ወደ ኪችነር ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በዝማሬ ፣ በቃለ እግዚአብሔር በመታጀብ ወደዝግጅቱ ቦታ ሲደርሱም በደብሩ ካህናት አባቶች እንዲሁም ምዕመናን ደማቅ መንፈሳዊ አቀባበል ተደርጎላቸዋል::

በመቀጠልም የቅዳሴ አገልግሎቱ እንዳበቃ የደብሩ መዝምራን ጥዑም ዝማሬ ካቀረቡ በኋላ  ደብሩ አስተዳዳሪ የሆኑት ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ አላዓዛር አድነው መርኃግብሩን በመክፈት፣  በቀጥታ ከአዲስ አበባ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ተጋባዥ መምህር ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ  በመካነ ድር አማካኝነት “የእግዚአብሔር ስጦታ” በሚል ኃይለ ቃል መነሻነት ሰፋ ያለ የዕለቱን ትምህርት በሚገባ ሰጥተዋል። በተመሳሳይ ሰዓትም  በኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ቀሲስ ሔርሞን ተክለ በጉባኤው ተገኝተው ለታዳጊ ህፃናት እና ወጣቶች መንፈሳዊ ትምህርት እና ምክሮችን በመስጠት ያገለገሉ ሲሆን ፣ እንዲሁም ለህፃናት በዲያቆን ኖላዊ አሸናፊ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት ተሰጥቷል።

የምሳ መስተንግዶው እንዳበቃም መርሐ ግብሩ በመቀጠል የማኅበረቅዱሳን አባላት የሆኑ መዘምራን: እንዲሁም የሁለቱም ደብራት ታዳጊዎች በክራር እና በመሰንቆ ዝማሪዎችን አቅርበዋል። በማስከተልም የቶሮንቶ ንዑስ ማዕከል በወቅታዊ የቤተክርስትያን ጉዳይ እና ማኅበረ ቅዱሳን በሀገራችን ኢትዮጵያ እየሰራቸው ያሉትን  መንፈሳዊ አገልግሎቶች ገለፃ ካቀረበ በኋላ ምዕናንና እንደ እምነቱ ተከታዮች ምን እናድርግ በሚል ሰፋ ያለና ብዙ ጥያቄዎችን ያስተናገደ  ውይይት ተካሂዷል። ተሳታፊዎችም በቀረበው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በታላቅ ቁጭት አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ አንዳንድ የማኅበሩ አባላት እና ምዕመናንም ማኅበረ ቅዱሳን በሚያሳያቸው አቅጣጫ ድጋፍ ለማድረግም ቃል ገብተዋል።

ከውይይቱ በማስከተልም በዕለቱ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የመርኃግብሩ አስኳል፣  ምዕመናን በመንፈሳዊ ሕይወታችው እንዲበረቱ ለጥያቄዎቻቸው መልስ እንዲያገኙበት  የተዘጋጀው የምከረ አበው መረሐ ግብር ነበር። ከምዕመናን የተሰበሰቡትን ጥያቄዎች በዕለቱ ለተጋበዙት ለመልአከ ሕይወት ሃረገወይን ብርሃኑ የቶሮንቶ  ደብረ ገነት አቡነ ተክለሃይማኖት የኢ/ኦ/ተ/ ቤተክርስትያን ደብር አስተዳዳሪ እና ሊቀጠበብት ማህቶት የሻው  ከኪችነር ሐመረ ኖህ ኪዳነምህርት የኢ/ኦ/ተ/ ቤተክርስትያን የቀረቡ ሲሆን አባቶቻችንም ጥያቄዎችን ከብሉይና ከሀዲስ መፅሀፍት፡ ከስርዓተ ቤ/ክርስትያንና ከቤተክርስትያናችን አስተምህሮ ጋር በማያያዝ ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

የዕለቱ የመጨረሻ መርሐ ግብር የነበረው የመንፈሳዊ ጥያቄና መልስ ውድድር ሲሆን፣በውድድሩም ለአሸነፉት ምዕመናን የተለያዩ መንፈሳዊ መፅሐፍትን የማበረታቻ ሽልማት  በመስጠት:  የዕለቱን መርሐ  ግብር በአባቶች ፀሎትና ቡራኬ በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ የአጥቢያው ምዕመናንና በማኅበረ ቅዱሳን የካናዳ ማዕከል የደቡብ ምዕራብ ንዑስ ማዕከል አባላት ከቶሮንቶ ንዑስ ማዕከል ለመጡት ምዕመናን ደማቅ አሸኛኝት አድርገዋል። በጉዞው የተሳተፉት ምዕመናንም  የሐዊረ ሕይወት መንፈሳዊ ጉዞ በጣም እንዳስደስተቻው ገልጸዋል።

ለዝግጅቱ መሳካት የቶሮንቶ ደብረ ገነት አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስትያን ምዕመናን በመቀስቀስ፣ የኪችነር ሐመረ ኖህ ኪዳነምህርት ቤተክርስትያን ምዕመናን ሰንበት ትምህርት ቤት እና በማኅበረ ቅዱሳን የካናዳ ማዕከል የደቡብ ምስራቅ ንዑስ ማዕከል ለተጓዦቹ አቀባበልና መስተንግዶ በማቅረብ፣  ቲሸርት በማዘጋጀት ለጉዞው መሳካት ትልቅ አስተዋጾ አድርገዋል። ከቶሮንቶ የተነሱት ምዕመናንም እግዚአብሔርን በዝማሬ እያመሰገኑ ወደ ቶሮንቶ በሰላም ተመልሰዋል።