ትንሣኤ ክርስቶስ

አክሊለ ሰማዕት

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ረቡዕ ይሙት በቃ ተፈርዶበት አርብ ያለ ሕግ በሐሰት በግፍ ተገርፎ ተሰቅሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ።

በገንዘብ ፍቅር የናወዘው ይሁዳ የአስቆሮቱ መምህሩን ወዳጁን ጌታውን አምላኩን አሳልፎ እንደሰጠው እናስታውሳለን። ይሁዳ ከመንግስተ ሰማያት ይልቅ ሠላሳ ብርን መርጦ ነበር። ይህም የጌታን መሞት ለሚፈልጉና እየወደዳቸው ለጠሉት አይሁድ ደስታን ፈጥሮላቸው ነበር።

በዚህም ላይ የፈለጉትን ለመፈጸም ብዙ ግፍና የሐሰት ምሥክር ጨምረውበት ንጹሑን ጌታ ያለ ቅን ፍቅር ሰቅለውታል። ነገር ግን ቀድሞ እንደሚነሳ ይናገር ስለነበር በመቃብሩ ላይ ተጨማሪ ወታደሮችን አሰማርተው ነበር።

ጌታችን በስድስት ሰአት ተሰቅሎ በዘጠኝ ሰዓት በፈቃዱ ከሞተ በኋላ በ11 ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው በማዕረግ በአዲስ መቃብር አኑረውታል።

ጊዜው የማይቀየር መስሏቸው በአምላካችን ላይ ያንን ሁሉ ግፍ ሲፈጽሙና ሲያሰቃዩት የነበሩት ሊቃነ ካህናት (ካህናተ ኦሪት) ገዢዎቹና ሕዝቡ በጌታችን ሞት ምክንያት የታዩት ተአምራት አስደንግጧቸዋል። አንዳንዶቹም በሰማይ ሶስት በምድር አራት ተአምራት ሲደረጉ “በእውነት ይሄ ሰው አምላክ ነበረ” ብለው የተጸጸቱ ነበሩ።

በልቦናቸው አድሮ ያሰቀለው ዲያቢሎስም በመስቀሉ ፊት ቀርቦ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የተቆጣጠራቸውን ነፍሳት በብዙ ቅጣት አስረክቧል። በአይሁድ መካከልም ሁከትና ረብሻ ነግሶባቸዋል።

በመቃብሩ ላይ ትልቅ ድንጋይ አኑረው ያተሙበት ቢሆንም  ይህ ሁሉ የጌታችንን ትንሳኤ አላስቀረውም። በገንዘብና በመሸነጋገል የሰቀሉትን የቅዱሱን የእግዚአብሔርን ልጅ ትንሳኤ ለማስተካከል ተጨማሪ መማለጃ ለወታደሮች በመክፈል በሐሰት ወሬ አስተባበሉ። ክፋትንም በክፋት ላይ ጨመሩ።

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የተኛ ሰው ከእንቅልፍ ፈጥኖ እንደሚነቃ ተነሳ። (መዝ 77፥66) ይህም ለእኛ ለክርስቲያኖች ፍጹም ሐሴት ፍጹም ደስታ ሆነልን። ለዲያብሎስና ትንሳኤውን ለሚክዱ ግን ጭንቀትና መከራ ሆነባቸው።

የጌታችን ትንሳኤ ዕለት በእርሷ ደስ እንድንሰኝባት እግዚአብሔር የሠራልን ቀን ናት።(መዝ 117፥24) ማለትም በሞቱ ሞትን አጥፎቶ በትንሳኤው ሕይወትን ለእኛ የሰጠባት ዕለት ናት። አጋንንትን አጥፍቶ አዳምንና ሔዋንን ከነዘሮቻቸው ከጥፋት ከኃጢአት ያዳነባት ዕለት ናትና በእርሷ ደስ ይበለን እንዳለ። በደስታ በሐሴት የምናከብራት ዕለት ናት።

“ጠላቶቹን በኋላው ገደለ” (መዝ 77፥6) እንዳለ ጠላት ዲያቢሎስን ተሰቅሎበት ከጀርባው ባደረገው ቅዱስ መስቀሉ ቀጥቅጦ ከመንገድ አስወግዶልናል። ጠላታችንም ሥጋን ተቆራኝቶ ወደ መቃብር ነፍስን ተቆራኝቶ ወደ ሲዖል የማውረድ ሥልጣኑ ተሽሮበታል።

‘አፈር ነህና ወደአፈር ትመለሳለህ” ብሎ ቀድሞ በአዳም የፈረደ አምላክ ሙስና መቃብርን (በመቃብር ፈርሶ በስብሶ) መቅረትን ሊያስወግድ በሶስተኛው ቀን ተነስቷል ። በዚህም የሰው ልጅ ተሥፋ ትንሳኤንና ተሥፋ መንግስተ ሰማያትን አግኝቷል።

ይህን የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ አምነን እኛም የሙታንንም መነሳት በእምነት በተሥፋ እንጠብቃለን። ‘’ሙታን የማይነሱ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሳም’’ እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡

መለኮትን የተዋሀደው ቅዱስ  ሥጋው ወደ መቃብር ሲወርድ መለኮት ያልተለያት ቅድስት ነፍሱም በሲኦል ተገኝታ ድህነትን ለነፍሳት ስታድል፤ የነበረባት ዕለት እግዚአብሔር የሠራት ማለትም ሥራን የሰራባት እለት ይህች ናት። የገነት በር ተክፍቶልን ተሥፋ ትንሳኤ ተሰጥቶን ‘ሞት ሆይ መውጊያህ የት አል’’ እያልን ደስ እንሰኝባት ሐሴትም እናድርግባት የትንሳኤውን ጌታም እናመስግንባት፡ የመስቀሉ መከራ ተካፋይ የሆነችውን የድህነታችን ምክንያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንም ከፍ ከፍ እናድርግባት። በመከራ ውስጥ ስለኛ በፍቅር የነገሰበትን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሰጠበትን ክቡር መስቀሉን እናክብርባት።

ወስብሀት ለእግዚአብሔር