ሆሳዕና በአርያም
አክሊለ ሰማዕት
.
ሆሳዕና ማለት መድኃኒት ወይም አቤቱ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ ይህ የዐቢይ ጾም ፋሲካ አንድ ሳምንት ሲቀረው የሚከበረው የጌታ በዓል ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው። በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሃት ጸሎተ አስተስርዮ ስለማይፈጸም ጸሎተ ፍትሃትና አስተስርዮ የሚደረገው በዚሁ ዕለት ነው::
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞት ባስነሳባት የቢታንያ መንደር በተገኘ ጊዜ የአይሁድን ፋሲካ ለማክበር ከየሀገሩ መጥተው የነበሩ ሰዎች ጌታችንንም ከሞት ያስነሳውን አልዓዛርንም ለማየት ተሰብስበው ነበር። ተአምራቱን እያደነቁ ብዙዎችም አምነውበት ነበር፡፡ ጌታችን ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም እስኪደርስ ብዙዎች በምሥጋና አጅበውታል፡፡(ዮሐ. 12÷12) የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው “ሆሳዕና በጌታ ስም የሚመጣ የእሥራኤል ንጉስ የተባረከ ነው።” እያሉ እያመሰገኑት ወደ ቤተፋጌ መንደር ደረሱ፡፡
=> ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ዘንባባ የመነጠፉ ሚስጢር የምን ምሳሌ ነው?
1.ዘንባባ፡- ይስሃቅ በተወለደ ጊዜ ደስ ብሎት አብርሃም ዘንባባ ይዞ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡
2.ዘንባባ ደርቆ እንደገና ህይወት ይዘራል:: የደረቀ የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
3.ዘንባባ የሰላም ምልክት ነው፡- የሰላም አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
4.ዘንባባ የደስታ መግለጫ ነው፡- አንተ ደስ የምታሰኝ ሃዘናችንም የምታርቅልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
5.ዘንባባ እሾሃማ ነው፡- አንተ ህያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
6.ዘንባባ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል እንጂ፡፡ ጌታም አንተ ባህሪህ የማይመረመር ነው ሲሉ ነው፡፡
በነቢያት እንደተነገረው “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ አትፍሪ፤ እነሆ ንጉስሽ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል።” (ዘካ.9÷9) የተባለው ትንቢት እንዲፈጸም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላካቸው፡፡ ሄደው አህያዋን ከነውርንጫዋ ታሥራ እንደሚያገኙ፣ ፈተው እንዲያመጡለት፣ ለምን ብለው ከጠየቋቸውም ጌታዋ ይፈልጋታል በማለት መልስ እንዲሰጡ አዘዛቸው፡፡ እነሱም እንደተባሉት አደረጉና ልብሳቸውን አነጥፈውለት በአህያዋ ላይ ተቀመጠ፡፡ (ማቴ.21÷1)
ትንሹም ትልቁም “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፤ ሆሳዕና በአርያም” እያሉ ያመሰግኑት ነበር፡፡ ዘንባባ ይዘው ልብሳቸውንና የዛፍ ቅጠሎችን በመንገዱ ላይ ያነጥፋ ነበር። ልብሳቸውን ማንጠፋቸውም ለክብሩ መግለጫ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ክብርና ምስጋና ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ከተማዋ በዝማሬና በአመስጋኞች ጩኸት ተናወጠች፡፡
ይህ ያበሳጫቸው ፈሪሳዊያንና አይሁድ የሚያመሰግኑትን ዝም እንዲያሰኝ ጌታችንን ቢጠይቁትም “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ያመሰግኑኛል” ብሎ መልሶላቸዋል፡፡ በነብዩ ዳዊት “ከሚጠቡ ሕጻናትና ከልጆች ምሥጋናን አዘጋጀህ” (መዝ. 8÷2) ተብሎ የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸምም የአርባ የሰማንያ ቀን የዓመት የሁለት ዓመት ሕጻናትም አመስግነውታል፡፡
ክቡር ዳዊት “ጸላኢ ገፋኢ ደስ አይበለው ብለህ ከሕጻናትና ከሚጠቡ ጨቅላዎች አንደበት ምሥጋናን አዘጋጀህ” ያለው ትንቢት ሲፈጸም ጸላኢ ገፋኢ (ግፈኛ ጠላት) የተባለ ዲያቢሎስ የሚወገድበት ጊዜ መድረሱን ያመላክታል፡፡ ዲያቢሎስ የሰውን ልብ ዙፋን ሰውነቱን ድንኳን ኃጢአትን አጥር አድርጐ 5,500 ዘመን ቢኖርም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል እሱን ከሰዎች ልቦና የሚያስወግድበት ቀን ቀርቦ እንደነበር እናስተውላለን፡፡
አዋቂዎችም ሕጻናትም “ሆሳዕና በአርያም” እያሉ ማመስገናቸው “መድኃኒት መባል ለአንተ ይገባሃል” ማለታቸው ነው።
በበዓለ ሆሳዕና ጉዳይ ከሚነሳው የአህያዋና የውርንጫዋ ነገር ነው፡፡ ጌታችን ኪሩቤል በሚሸከሙት ዙፋን የሚቀመጥ አምላክ ሲሆን ትሁት ሆኖ በአህያ ላይ ተቀመጠ፡፡ አህያዋን ከነውርንጫዋ “ፈታችሁ አምጡልኝ” ማለቱ የሰውን ልጅ ከኃጢአት እሥራት ለመፍታት የመጣ አምላክ መሆኑን ያሳየናል፡፡
ደቀ መዛሙርቱም አህዮቹን ፈተው ማምጣታቸው ሥልጣነ ክህነታቸውን ያመለክታል፡፡ “በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሁን” እንዲል፡፡
በአህያ ላይ ልብሳቸውን ማንጠፋቸው ደግሞ የምትመች የማትቆረቁር የወንጌልን ሕግ ሰጠኸን ሲሉ ነው፡፡
በአህያ የተቀመጠ ሰው በፈረስ እንደተቀመጠ ሰው ፈጥኖ አያመልጥም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከፈለጉኝ አያጡኝም ሲል በአህያ ተቀምጧል፡፡
ከግለሰብ ደጅ የተፈታችን አህያ “ ጌታዋ ይፈልጋታል” ብሎ ያስፈታት በፈጣሪነቱ ወይም ስለፈጠራት ገንዘቡ ስለሆነች ነው፡፡ አህያን ያልናቀ አምላክ እኛም ከኃጢአት ርቀን ብንፈልገው ማደሪያዎቹ ሊያደርገን ፈቃዱ ነው፡፡ የአህያዋን መፈታት የፈለገ ጌታ እኛም ወደካህናት ቀርበን ኃጢአታችንን ተናዘን ከበደል እሥራት እንድንፈታ ይፈልጋል፡፡
ከኃጢአት እሥራት ተፈተን፣ የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ማደሪያዎች እንድንሆን የእግዚአብሔር ቸርነት የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይርዳን፡፡
ወስብሀት ለእግዚአብሔር