ለምን ጾምን! አንተ ግን አልሰማኸንም ?
በተክለማርያም ( ኪችነር : ካናዳ)
ጾም ለተወሰነ ሰዓት ከምግብ እና ከመጠጥ መከልከል መሆኑን መንፈሳዊዉም ሆነ ሥጋዊው ዓለም ይስማማበታል ።
ሥጋዊ ዓለምና መንፈሳዊው ዓለም በአላማ ልዩነት ቢኖራቸውም አንድ ላይ ሆነው ዘመናትን ተሻግረዋል:: ምግብ ለህልውናችን እና ለጤናችን አስፈላጊ መሆኑን ሁለቱም ያውቃሉ ። የምንመገብበት ሁኔታ: ዓይነትና የመመገቢያ ወቅታችን ከመለያየቱ የተነሳ: ከምንመገበው ምግብ የምናገኘው ስጋዊ ጠቀሜታ በሁላችንም ዘንድ ይለያያል:: ከምግብ ጋር ጥሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች የተመገቡት ምግብ የሰውነታቸውን ጡንቻ ገንብቶት ጤናማ ህይወትን ሲመሩ ይታያሉ: በአንፃሩ ምግብን ተመግበው የሚተኙ ብዙም የአካል እንቅስቃሴ ሥራ የማይሰሩ ሰዎች ደግሞ ለጥቅም ብለው የተመገቡት ምግብ ሆዳቸው ላይና ሌላም የሰውነት አካላቸው ላይ ለጤና መታወክ ሲግጥማቸው ይታያል ።
ለበሽታም ሊያጋልጣቸው ይችላል:: የምግቡን ጥራት ጨምሮ እነዚህ ሁሉ ወሳኝ የምግብ ሥርዓቶች በሥጋዊ ጤንነታችን ላይ የሚያመጡት ውጤት ወሳኝነት አለው ።
ይህ በሥጋዊ አካሄድ ሲሆን በመንፈሳዊ ሥርዓት ደግሞ ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም በግዚአብሔር ቃል ነውንጅ ሁልጊዜ ለምግብ ብቻ የሰው ልጅ ክቆመ ክሥጋ በሽታ አልፎ ለነፍስ በሽታ ይዳረጋል ። ምክንያቱም ፈቃደ ነፍሳቺንን ለፈቃደ ሥጋችን ካስገዛን ነፍስ ትታመማለች በተቃራኒው ግን ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ካስገዛን ነፍሳችን ብቻ ሳይሆን ሥጋችንም ክልዩ ልዩ ደዌ ይድናል ። < ጾም የነፍስን ቁስል ታድናለች ነውና › ቅ.ያሬድ
የፆማችን እና የፀሎታች ምላሽ ለምን ዘገየ? እንዲያውም ለምን በተቃራኒው በመከራ ላይ ወደቅን? ለምንስ የአህዛብና የወደረኞቻችን መሳቂያ ሆንን? ይህ የብዙ ክርስቲያኖች ጥያቄ ነው:: ለጥያቄያችን መልስ ያጣን የመሰለን ጾምን እምንለው ከእህልና ከውሃ ብቻ ስለሆነ ነው ። መጽሐፍ ግን ልብ ይጹም ፣ ልሳን ዪጹም፣ዓይን ይጹም፣ጆሮም ይጹም፣ እጅና እግር ይጹም በጠቅላላ የሰውነት ህዋሳቶች ይጹሙ ነው እሚለው ። ልብ እንበል! ሙሉ ሥራ ሣይሠሩ ሙሉ ደመወዝ አይገኝም ። እስራኤላውያን ፈጣሪያቸውን በተደጋጋሚ ጠይቀዋል እግዚአብሔርም ህዝቦቹ ይሰሙት ዘንድ በሚችሉት ደረጃ እራሱን ዝቅ አድርጎ በተደጋጋሚ መልስ ሰጥቷቸዋል:: ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ የእስራኤልን ጥያቄ እና የእግዚአብሔርን መልስ እንዴት እንዳስቀመጠው እንመልከት::
የእስራኤል ጥያቄ:- ትንቢተ ኢሳይያስ 58፥3
ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም?
የእግዚአብሔር መልስ:- “እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥
ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ” ይህ የእግዚአብሔር
መልስ እራሱን ለሚያውቅ እና ህሊናውን ላላሸፈተ ሁሉ በቂ መልስ ነው::
ታዲያ ነቢዩ ኢሳይያስ ለእስራኤል የነገራቸው ለምን ፆማቸው እንዳልተሰማ እና ምላሽ እንዳላመጣ ብቻ አልነበረም ይልቁንስ በእርግጠኝነት የጾማቸውን እና የእንባቸውን ምላሽ በፍጥነት የሚያገኙበትን ብቸኛ አምላካዊ ምሥጢር እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ ገልፆላቸዋል::
ክርስቲያኖች ልብ እንበል ይህ መልዕክት ለእኛም ጭምር ነው እና በጾማችን እና በጸሎታችን ውስጥ ለእስራኤል የተነገረው የሚከተለውን አምላካዊ መመሪያ መፈፀማችንን እርግጠኞች እንሁን::
“እንጀራህን ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ…ከመካከልህ ቀንበርን
ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ/መቀሰር/ ብትተው፥ ባታንጐራጕርም፥ …ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፥የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፥ የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ..” በተጨማሪም “በድሆችና በምስኪኖች ዘንድ ልታየው ያልቻልከውን ክርስቶስን ቤተክርስቲያን ውስጥ አታገኘውም::” የሚለው የአበው ምክርም የመንፈሳዊ ህይወት ወሳኝ እሴቶቻችንን እንድናስብ የሚያደርገን ነው::
ከላይ የተመለከትነው የእስራኤላውያን ደካማ የጾም አስተሳሰብ በጌታችን መዋዕለ ሥጋዌም እጅግ ተስፋፍቶ ነበር:: ለምሳሌ ጌታችን ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል የማቴዎስ ወንጌል 6፥16 “ስትጾሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጾመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” የሚለው ትምህርት ትልቅ ማሳያ ነው:: እውነት ነው ሥጋን ማስራብ ብቻ ነፍስን ማጥገብ ሊሆን አይችልም:: ይልቅስ በፆም ወራት የነፍስ ምግብ የሆነውን ቃለ እግዚአብሔርን እና ጸሎትን አብዝተው ሊጨምሩላት ይገባል::
የሥጋ በምግብ እጦት መድከም ለነፍስ ፈቃዷን ለመፈፀም እድል ይሰጣታል እና ምግባረ ትሩፋቱን በጾም ወራት ለመለማመድ እና ባለውም ላይ ለመጨመር የተመቸ ነው:: በጾም የታጀበች ጸሎት ቅድመ እግዚአብሔር ትደርሳለች:: ቅድመ እግዚአብሔር የደረሰች ጸሎት ደግሞ ሁልግዜ የምሥራች ይዛ ትመጣለች::
የጾም ሌላው መለኪያ ደግሞ ስጋችን ለመብላት እና ለመጠጣት እየቻለ ነገር ግን መብላት እያማረ ስትተወው እና እራስ መግዛትን ገንዘብ ስታደርግ ነው:: ይህን ዓይነት የፆም ልምምድ ያረገች የክርስቲያን ነፍስ ሌሎችንም ተመሳሳይ ተጋድሎዎችን እና በሥጋዊ ሥልጣናችን ማድረግ እየቻልን ለመንፈሳዊው ጥቅም ብለን የምንተዋቸውን ነገሮች ሁሉ መለማመድ ይቻላል:: ለምሳሌ:- ለሰደቡን መስደብ ስንችል: ክፉ ላደረጉብን ክፉ ማድረግ ስንችል: ጠላቶቻችን ብለን ያልናቸው ሰዎች መከራ ሲደርስባቸው ጮቤ መርገጥ ስንችል: በቂ ገንዘብ አለን ብለን ማባከን ስንችል: ሰው አላየንም ብለን ኃጢአት መሥራት ስንችል እናም ሌሎችን ተመሳሳይ ክፉ ነገሮች ማድረግ ስንችል ልክ ምግቡን መመገብ እየቻልን ታግሰን ባለመመገብ እንዳለፍነው ሁሉ አሁንም እግዚአብሔርን ከመፍራት የተነሳ እነዚህን የሥጋ ፈቃዳቻችንን ወደን ፈቅደን ብንተዋቸው እና ይልቅስ ክርስቲያን እንደመሆናችን መከራን በፈቃዳችን ለመቀበል እራሳችንን ያዘጋጀን ከሆንን ጽድቅ ይሆንልናል::
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን ሲያስረግጥልን በአንደኛ መልዕክቱ 4፥15 “ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።” የጸሎት እህት የተባለች ጾምን ምን ያህል ኃይል ያላት መሆኗን ሲገልጽም እግዚአብሔር እንዲህ አለ “ይህ ዓይነቱ ከጾምና ከጸሎት በቀር አይወጣም” ማቴ 17፥21 የምግባረ ትሩፋት አክሊል እና የመንፈሳዊ ተጋድሎ የመጨረሻዋ ብርቱ ጉልበት የሆነችውን ቅድስት ጾማችንን በሚገባ ፈጽመን ቅድመ መንበረ ሥላሴ ጸሎታችንን አድርሳ ሁነኛ መልስ የምታስገኝልን ትሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን::
ወስብሐት ለእግዚአብሔር