ኒቆዲሞስ
አክሊለ ሰማዕት
.
በቅዱስ ያሬድ ጾመድጓ መሠረት የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡
ኒቆዲሞስ በዕውቀትም ፣በሥልጣንም፣ በሀብትም ከአይሁድ መካከል ላቅ ያለ ነበርና የአይሁድ አለቃ ተብሏል፡፡ ከፈሪሳዊያን ወገንም ነበር (ዮሐ. 3÷1)፡፡ ፈሪሳዊያን መሲሁ ሲመጣ ምድራዊ መንግስት መስርቶ እኛን ሹሞቹ ያደርገናል የሚል እምነት የነበራቸውና የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መሲህነት ያልተቀበሉ ወገኖች ነበሩ፡፡ ጌታችንን አምኖ የተከተለውን ከመካከላቸው ለይተው እንደሚያስወጡት ሕግ አዘጋጅተው ስለነበር ኒቆዲሞስ ምንም እንኳን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ቢያምንም በቀን ወደ እርሱ መጥቶ መማር አልቻለም ፡ ፡
በዚህ ምክንያት ኒቆዲሞስ ወደ ጌታችን በሌሊት መጣ፡፡ እምነቱንም ‘’እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን ምልክቶች ማድረግ የሚችል የለምና ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን ‘’(ዮሐ.3÷2) ብሎ መስክሯል፡፡ ይህንንም ሲል መለኮት ካልተዋሐደው በቀር የፍጡር ሥጋ ብቻውን አንተ የምትሰራውን አምላካዊ ተአምራት ማድረግ አይችልም ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ የተላከ የባህርይ አምላክ መሆኑን እንዳመነ መናገሩ ነው፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከማመን ባለፈ ለመዳን የመጠመቅን አስፈላጊነት ገልጾ አስተምሮታል፡፡
“ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም (ዮሐ.3÷3)” ሲለው ኒቆዲሞስ እንደገና ከእናት ማህጸን ስለመወለድ የተናገረ ስለመሰለው ደግሞ ጠየቀ፡፡ ጌታችንም ከሥጋ መወለድን አንድ ብሎ በጥምቀት መወለድን ዳግም ወይም ዳግመኛ በማለት፣ ከሴት ማህጸን ከወንድ አብራክ የሚሆነው ልደት ሥጋዊ እንደሆነ ገልጾለታል፡፡ ሁለተኛው ልደት መንፈሳዊ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህጸነ ዮርዳኖስ መሆኑን በመግለጽ ከውሃና ከመንፈስ መወለድ እንደሚገባ ነግሮታል፡፡
ለዚሁ ረቂቅ ልደት ምሳሌ እንዲሆን የነፋስን ነገር በማንሳት ነፋስ ከየት መጥቶ ወደየት እንደሚሄድ ሳይታይ ዛፍ ሲያወዛውዝ፣ ወፍጮ ሲያንቀሳቅስ…. መኖሩ እንደሚታወቅ ሁሉ፤ መንፈስ ቅዱስም በዳግመኛ ልደት ወይም በጥምቀት ምክንያት ልዩ ልዩ ጸጋን በሰዎች ላይ ሲያሳድር አይታይም፡፡ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ስራ ሲያሰራ ግን ይኸው ይታወቃል፡፡
ይህም ሁኔታ ረቂቅ ቢሆንም ሰዎችን እንዲያስተምሩ፣ ትንቢት እንዲናገሩ፣ ወይም በተለያየ ጸጋ እንዲያገለግሉ ሲያደርግ በሰዎች ማደሩ ይታወቃል፡፡ የሙሴ ጸጋ በኢያሱ፣ የኤልያስ ጸጋ በኤልሳዕ ሲያድር አልታየም በሥራቸው ግን ተገልጿል፡፡ በዚህ ሁሉ ምሳሌ ከመንፈስ የመወለድን ነገር ረቂቅነት አስረድቶታል፡፡
በዚሁም ምሥጢረ ሥላሴን ዳስሶለታል፡፡ ጌታችን “የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን” (ዮሐ. 3÷11) ብሎ በመናገሩ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውን የሕልውና አንድነት አሳይቷል፡፡ ይህም ማለት ሥላሴን በልብ በቃል በእስትንፋስ ኩነት እንደምንረዳው አብ ለራሱ ልብ ሆኖ ለወልድም ለመንፈስ ቅዱስም ልባቸው ነው እንደሚለው ያለ ነው፡፡
“ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም” (ዮሐ.3 ÷13) ብሎ ከልዕልና ወደ ትህትና ወርዶ ሰው የሆነው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ የማረጉን ነገር አስረድቶት “እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” ብሎ በሕልውና ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ እንዳልተለየ አስገንዝቦታል፡፡
ኒቆዲሞስ በሌሊት ከጌታችን አንደበት ከተማራቸው ጉዳዮች መካከል ነገረድህነት ይገኝበታል፡፡ ጌታችን የሚያምኑበት የዘለዓለም ሕይወት እንዲያገኙ በመስቀል እንደሚሰቀል ለኒቆዲሞስ ነግሮታል፡፡ ለዚህም ምሳሌ ያደረገው ሙሴ በምድረበዳ የሰቀለውን እባብ ነው፡፡ እሥራኤል ከአህዛብ ሴቶች ጋር በዝሙት በመውደቃቸው ተቆጥቶ በመርዘኛ እባብ እንዲነደፉ ያደረጋቸው እግዚአብሔር፤ በሙሴና በአሮን ልመና ከቁጣው ተመልሶ ሙሴ የነሐስ እባብ ሰርቶ በቋሚ ላይ እንዲሰቅለው አዘዘው፡፡ ከዚያም በቅርብ ያሉት የናሱን እባብ አይተው፤ በሩቅ ያሉት የናሱን የምት ድምጽ ሰምተው ተፈውሰዋል፡፡
ተናዳፊው እባብ መርዘኛ ሲሆን የነሐሱ እባብ መርዝ እንደሌለው ሁሉ ጌታችንም ራሱን በነሐሱ እባብ መስሎ ስለ ስቅለቱ ተናግሯል፡፡ እሥራኤል በነሐሱ እባብ ምክንያት ከመቅሰፍት እንደዳኑ ሰዎች ሁሉ የሚድኑት ራሱን በነሐስ እባብ መስሎ የተናገረውን በአንደበቱ ሀሰት በሰውነቱ ክፋት ሳይገኝበት ዕዳ በደል ሳይኖርበት በመስቀል ላይ የተሰቀለውን መድኀኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን በማመናቸው ነው (ዮሐ. 3÷18)፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከክፋት መራቅና መልካም መስራት ከጨለማ ወደ ብርሃን እንደሚያወጣ ለኒቆዲሞስ አስተምሮታል፡፡ ክፉ የሚያደርጉ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን የሚወዱ እንደሆኑና እውነትና ጽድቅ የሚያደርጉም የብርሃን ልጆች እንደሆኑ ገልጾለታል (ዮሐ. 3 ÷21)፡፡
ከኒቆዲሞስ የምንማራቸው በርካታ ነገሮች ሲኖሩ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ለመማር እኔ ታላቅ ነኝ ታናሽ ነኝ አይባልም፡፡ የአይሁድ አለቃ ኒቆዲሞስ መምህር አለቃ ነኝ ሳይል ወደ ጌታችን ሊማር መጥቶአልና፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢረ ጥምቀትንና፣ ምሥጢረ ሥጋዌን፣ እንዲሁም ምሥጢረ ሥላሴን አስተምሮታል፡፡ ክርስቲያን ነኝ የሚል ማንም ሰው እንዲሁ አምስቱን አዕማደ ምሥጢር ጠንቅቆ ማወቅ ይገባዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ለመማር ይሉኝታ ወይም ፍርሀት አይገባም፡፡ ኒቆዲሞስ ይሉኝታና ፍርሃትን ለማስወገድ በሌሊት ወደ ጌታችን መጥቶ ተምሯል፡፡
ሰዎች ሃይማኖትን ለመማር “ጊዜ ማጣት” አይገባቸውም፡፡ ኒቆዲሞስ ጊዜውን አመቻችቶ የሕይወትን ትምህርት ለመስማት ችሏልና ከዚሁ መማር ይገባል፡፡ ለኒቆዲሞስ ምሥጢሩን ገልጾ ያስተማረ አምላክ ለእኛም ምሥጢሩን ይግለጽልን፡፡
ወስብሀት ለእግዚአብሔር