በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

“የዓለም ፍጻሜ”

በዲ/ን አሰበልኝ ጨቡድ

የተወደዳችሁ አንባቢያን በሙሉ እንኳን ለዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት (ደብረ ዘይት)
አደረሳችሁ፡፡

ደብረ ዘይት

በቅዱስ ያሬድ ስያሜ መሠረት የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት/እኩሌታ/ ደብረ ዘይት ይባላል። ደብረዘይት ማለት የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ቀን በምኩራብ /በመቅደስ/ ሲያስተምር ውሎ ሌሊትበደብረ ዘይት ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር፡፡ (ሉቃ.21፥37) ወደ ሰማይ ያረገውም በዚሁ ተራራ ነው፤ዳግመኛም መጥቶ የሚፈርደው በዚሁ ተራራ ስለሆነ ደብረ ዘይት ተብሏል፡፡ “በዚያም ቀን እግሮቼበኢየሩሳሌም ትይዩ በምስራቅ በኩል ባለው ደብረ ዘይት ይቆማሉ፤ደብረ ዘይትም በመካከል ወደ ምስራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፤እጅግም ታላቅ ሸለቆ ይሆናል፤የተራራውም እኩሌታ ወደ ሰሜን እኩሌታውም ወደ ደቡብ ይርቃል፤የተራሮችም ሸለቆ እስከ አጸል ይደርሳልና በተራሮች ሸለቆ ትሸሻላችሁ፤ በይሁዳም ንጉሥ በዖዝያን ዘመን ከሆነው ከምድር መናወጥ ፊት እንደ ሸሻችሁ ትሸሻላችሁ፤ አምላኬ እግዚአብሔርም ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ይመጣል፡፡” እንዳለ ነቢዩ (ዘካ.14፥4)

“ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው “የዓለም ፍጻሜ ምልክቱ ምንድነው?” (ማቴ.24፥3) ብለው ሲጠይቁት እርሱም ስለ መጨረሻው ዘመን መቃረብ ምልክቶችን ነግሯቸዋል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን የደብረ ዘይት ሳምንት ስለ ነገረ ምጽአት (ክርስቶስ ዳግም ስለመምጣቱ ለጻድቃን ሊፈርድላቸው ለኃጥአን ሊፈርድባቸው እንደሚመጣ) አምልታ አስፍታ ታስተምራለች።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ምጽአቱን በደብረ ዘይት በታላቅ ተራራ መግለጡ ተራራ ልዑል እንደሆነ ሁሉ ይህም የዓለም ፍጻሜ ታላቅ ምሥጢር ነውና በታላቅ ተራራ ለደቀ መዛሙርቱ ገለጠላቸው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ይህንን ነገረ ምጽአት ሲያስረዳ “እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወስ ኵሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኵሎሙ ኃጥአነ ምድር ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበአዕላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእምኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት።”


ጌታችን በደብረ ዘይት ተቀምጦ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው እወቁ እንዳያስቷችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ እኔ ክርስቶስ ነኝ ብለው ብዙዎች በስሜ ይመጣሉ፤ትዕግሥትን ያዘወተረ እርሱ ይድናል የሰው ልጅ በሚመጣ ጊዜ የሰማያትና የምድር ኃይል ይናወጣል፤ያን ጊዜ የምድር ኃጥአን ሁሉ ያለቅሳሉ ከእግዚአብሔር ታዞ በሚደረግ የመለከት መነፋት፣ በአዕላፍ መላእክት ታጅቦ፣ በትእዛዙና በቃሉ ጌታችን ከሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል በዚያች ሰዓት በኃጢአት ከሚመጣ ፍርድ ይማረን ፤የሰንበት ጌታ እሱ ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።  ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችንን ስለዳግም ምጽአቱ “የዓለም መጨረሻ የመምጣትህ ምልክቱ ምንድነው?” ብለው አጥብቀው ጠየቁት፤ እርሱም ስለመጨረሻው ዘመን ምልክት አስረግጦ ነገራቸው፦

“ጌታችን በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።
ብዙዎች። እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።
ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።
ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፡፡
ርኃብ፣ ቸነፈር፣ የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፡፡ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሏችሁማል፡፡
ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፡፡
ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡
ከዓመጻም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች።
እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።

ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል። እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፡፡” (ማቴ 24፥3) አምላካችን የነገረንን የዓለም ፍጻሜ ምልክቶች ልብ ማድረግ አለብን፤ያለንበት ወቅት የዘመን ፍጻሜ ዋዜማ ላይ መሆናችንን በጥልቀት ተረድተን ራሳችንን በንስሐ ሕይወት ተመላልሰን ሥጋውን ደሙን ተቀብለን መዘጋጀት አለብን፡፡  ተመልከቱ ይኽን ሁሉ አሁን ካለንበት ዘመን ጋር ስናስበው ምን ላይ ነው ያለነው? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ? በክርስቶስ ስም የሚነግዱ ስንቶች ተነሡ? ስንቶችንስ አስካዱ? ጦርነት በዓለም በሀገራችን ጦርነት የምናየው ነው ሕዝብ በሕዝብ ላይ እያመጸ አይደለምን? ሀገር ከሀገር መንግሥት በመንግሥት ላይ በአመጽ አይደሉምን? በአሕዛብ ስንቶች ክርስቶሳውያን ተጠሉ ተገፉ? የክርስቶስ የሆኑት ክርስቲያኖችንና ቤተ ክርስቲያንን ሁሉ ለማጥፋት ስንት መከራ ወረደ ስንቶች ተገደሉ? በክፋት በኃጢአታችን ምክንያት ርኃብ፣ቸነፈርን አመጣን በዚህም ስንቶች አለቁ? ከክፋት ከተንኮል የተነሳ ስንቶች በመጠላላት ተጠላለፉ አሁን ከእኔ ይልቅ ለወንድሞቼ ለእኅቶቼ የሚል አለ? ፍቅር በሰው ልጆች የት ሄደች? የእግዚብሔርን ትእዛዝ አናውቅም እንዳንል ምስክር ትሆን ዘንድ ርትዕት የሆነች ወንጌል በተለያየ መንገድ ለዓለም ደርሳለች፡፡ ግን አንሰማም፤ባለንበት ጊዜ በክርስቶስ ስም የሚነግዱ የሐሰተኞች ነቢያት ስንት ናቸው? በሣር በቅጠሉ እየቀለዱብን አይደለንም? ብዙዎችስ ከክርስቶስ ይልቅ የግለሰቦች ተከታዮች አልሆኑምንዴ? የሐሰተኞች ነቢያት፣የሐሰተኛ አጥማቅያን ፣ትንቢት ተናገርን ለሚሉ ሁሉ ተከታዮች የሆንን ስንቶች ነን? በተቀደሰው ቦታ ስንት ካህናት፣ኦርቶዶክሳውያን ተገደሉ? ስንቶች ቤተ መቅደስን ተዘባበቱባት? በቤተ መቅደስ ስንት ነገር አየን? ስለዚህ ”የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ባያችሁ ጊዜ” አንባቢው ያስተውል እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል ተብለናልና በማስተዋል በሃይማኖት በመጽናት በምግባር በመቃኘት መከራ ቢበዛም በዓለም ፍጻሜ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ ኑ! የአባቴ ቡሩካን መንግስቴን ውረሱ የሚለውን የደስታ ቃል ለመስማት እስከ መጨረሻ መጽናት ያስፈልጋል፡፡ በክርስትናችን ሰማዕትነት እስከ መቀበል ድረስ እስከ ፍጻሜው ጸንተን እንድንድን ቅዱስ እግዚአብሔር ኃይል መንፈሳዊ ያድለን፤በዳግም ምጽአት በኃጢአት ከሚመጣ ፍርድ ያድነን፤ የሰንበት ጌታ እሱ ክርስቶስ ሕይወትን የሚሰጥ ነውና በዚያች ሰዓት ይማረን፡፡ አሜን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር