“ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡” (ማር 16÷19)
በ ዲ/ን አሰበልኝ ጨቡድ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ከተነሣ በኋላ ሐዋርያትና አርድእትን እና ቅዱሳት አንስትን (ማለትም 120 ውን ቤተሰብ) ለዐርባ ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን፣ሕግጋትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አስተምሯቸው፤” ወናሁ እፌኑ ተስፋሁ ለአቡዬ ላዕሌክሙ” እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ኃይልን ከአርያም እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ ብሏቸው፤ ከዚያም ወደ አፍኣ እስከ ቢታንያ አውጥቶ በአንብሮተ እድ እስከ ፓትርያርክነት ያለውን ማዕረግ ሾሟቸው፤ በዐርባኛው ቀን በይባቤ በምስጋና ዐርጓል፡፡ (ሉቃ 24÷49) ይህም በዓል በዓለ ዕርገት ይባላል፡፡ ዕርገት ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ “ዕርገት” (Ascension) የሚለው ቃል ከታች ወደ ላይ መውጣትን፣ ማረግን የሚያመለክት ነው፡፡
ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት እንዲህ ብሏል “እግዚአብሔር አምላክ በእልልታ፣በመለከት ድምጽ ዐረገ፤ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ፤ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ፡፡” (መዝ 46÷5) በዘወትር ጸሎታችን በ“ጸሎተ ሃይማኖት” ላይ እንደምናገኘው “ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ…/ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ…” በማለት ዕርገቱን በኒቅያ ጉባኤ የተሰበሰቡ አበው ቅዱሳን ጽፈውልናል፡፡ እግዚአብሔር ሰው የሆነው እኛን የአዳምን ልጆች ከወደቅንበት ለማንሣት ወደ ክብር ለመመለስ ነውና የባሕርይ አምላክ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የድኅነትን ሥራ ፈጽሞ በይባቤ በምስጋና ዐረገ። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ስለ ጌታችን ዕርገት በመጽሐፈ ምሥጢር በመደነቅ አገላለጽ እንዲህ ይሉናል፡፡
“የእግዚአብሔር ወዳጅ አብርሃም ሆይ ከእኛ ጋር በዓል ታደርግ ዘንድ ና፤በድንኳን ደጃፍ አጠገብ ባለ የወይራ ዛፍ አጠገብ ከአንተ ጋር የተቀመጠ የሦስት መስፈሪያ ስንዴ ዱቄት የተጋገረ እንጎቻ የበላ፤አንተም እርጎና ማር የሰባ ወይፈንም ያቀረብክለት እርሱ ዛሬም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በደብረ ዘይት ምሳ አደረገ፤ከምሳም በኋላ ባርኳቸው ከሴት ልጅህ በነሳው ሥጋ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ይስሐቅ ሆይ ከእኛ ጋር በዓል ታደርግ ዘንድ ና ከአባትህ ከአብርሃም ሾተል ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ በተያዘ በግ ደም የተቤዠህ እርሱ እንደ በግ ሊታረድ መጣ ለመታረድም እጆቹን በመስቀል ግንድ ላይ ዘረጋ በደሙም ሰይጣን የተናጠቃቸውን ተቤዣቸው ቁስላቸውም በሞቱ ቁስል ደረቀ፤ ተነሥቶም የሰውና የመላእክት አእምሮ ወደማይደርስበት ዐረገ፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ያዕቆብ ሆይ ከእኛ ጋር በዓል ታደርግ ዘንድ ና እነሆ በሎዛ ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ ያየኸው የወርቅ መሰላል እሰርሱ በደብረ ዘይት ተተከለ ቁመቱም እስከ አርያም ከፍታ ደረሰ ወልድ ሥጋ ከደብረ ዘይት ወደ ጽርሐ አርያም ከማረጉ በቀር የወርቅ መሰላል ምንድነው?… በደብረ ዘይት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደተቀመጠ ባሰብነው ጊዜ በመላእክቱ እልልታ እንዳረገ በወላጁም ቀኝ እንደተቀመጠ እናስታውሳለን” (መጽ. ምሥጢር ምዕ 28÷15-18) በእውነት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከበዓለ ዕርገቱ በረከትን ያድለን፤በይባቤ በክብር እንዳረገ ዳግም ለፍርድ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በሚመጣበት ጊዜ በቀኙ ያቆመን ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፡፡