“ጰንጠቆስጤ/ጰንጠቆስቴ/”(ሐዋ 2÷1)

በ ዲ/ን አሰበልኝ ጨቡድ

እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ አደረሳችሁ!

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት በዕርገቱ “እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ኃይልን ከአርያም እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” ብሏቸው ነበርና ባረገ በአሥረኛው ቀን አጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፤ይህ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ የሚከበርበት በዓል በዓለ ጰራቅሊጦስ፣ በዓለ ሃምሳ፣ ጰንጠቆስጤ/ጰንጠቆስቴ/ ይባላል፡፡

“ሰላም ለድሜጥሮስ ሐጋጌ አጽዋም እምስቴ፤ ወሠራዔ መብልዕ በጰንጠቆስቴ፤እመ ኢኮነ ላዕሌሁ መንፈስ ቅዱስ ካሳቴ፤እፎ ይተከሠት ዌትረከብ በአይቴ፤ሐሳበ ዘመን ዘስሙ ዓበቅቴ፡፡…” (ስንክሳር ጥቅ 12)
በዓለ ጰንቆስጤ/በዓለ ጰራቅሊጦስ/ ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት ዓላት አንዱ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በንጽሕና ያጌጠ ዲሜጥሮስ የበዓላትና አጽዋማት ቀመር በሠራልን መሠረት ቀኑ በዚያ ይታወቃል፤ዕለቱ ግን ዕርገት ሐሙስን እንደማይለቅ ሁሉ ጰራቅሊጦስም እንደ ሆሳዕናና ትንሣኤ እሑድን አይለቅም፡፡

ጌታችን ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በ50ኛው ቀን ባረገ በ10ኛው ቀን ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበትን ዕለት በማሰብ በዓለ ጰራቅሊጦስን/ጰንጠቆስጤን/ እናከብራለን፡፡ “ጰራቅሊጦስ” ማለትም ከሦስቱ አካላት አንዱ ለሆነ ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስሙ ነው፡፡ በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት እንደምናውቀው ሥላሴ በአገዛዝ፡ በባሕርይ ፡በሕልውና አንድ ሲሆኑ በአካል፡ በግብር፡ በስም፡ ሦስት ናቸው፡፡ አንድ ሲሆኑ ሦስት ፤ሦስት ሲሆኑ አንድ፤ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ብሎ የፍጡራን ልብ ሊመረምረው የማይችል ረቂቅ ምሥጢር ነው፡፡ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል “ጰራቅሊጦስ/መንፈስ ቅዱስ/” በእምነት የሚያጸና፣ ከኃጢአት የሚያነጻ፣ ያዘኑትን የሚያረጋጋ፣የተጨነቁትን የሚያስደስት፣ ከሣቲ ምሥጢር (ምሥጢርን የሚገልጽ) ማለት ነው፡፡

በሉቃ 24፥49 እንደተጻፈው የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያርግ ሲል ቅዱሳን ሐዋርያትን “እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” እንዳላቸው እነሱም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ሐዋርያት፣አርድእት፣ቅዱሳት አንስት በኢየሩሳሌም ከተማ በጽርሐ ጽዮን በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ሁሉም ለጸሎት ተሰብስበው በአንድነት ሳሉ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዐረገ በአሥረኛው ቀን በተነሣ በሃምሳኛው ቀን እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ድንገት ከሰማይ መጣና የነበሩበትን ቤት ሞላው፡፡ ከዚያም እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎች በሁሉም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሁላቸውም መንፈስ ቅዱስን ከተሞሉ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ባደላቸው መጠን በየአገሩ ቋንቋዎች ሁሉ መናገር ጀመሩ።(ሐዋ 2፥1-4)ጌታችን አጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት ይህ ዐቢይ በዓል ጰራቅሊጦስ/በዓለ ጰንጠቆስጤ/ ይባላል፡፡

ሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወርዶ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትና ጸጋን አድሏቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላም በአእምሮ ጎልምሰዋል፤ ጥቡዓን (ቈራጦች)፣ ፍርሐት ከውስጣቸው ተወግዶ መንፈሳዊ ድፍረት አግኝተዋል፤ ጽኑዓን ሆነዋል፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላም ጾምን የአገልግሎታቸው መጀመሪያ አድርገውታል፡፡ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ (ድኅረ ጰራቅሊጦስ) የጾሙት፤ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርገው ነው፡፡ እርሱ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ጌትነቱን ለመመስከር ከወረደ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ በዚያ 40 መዓልትና 40 ሌሊት ጾሟልና ፤እነርሱም ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት ከተቀበሉ በኋላ ጾምን የሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገዋል፡፡

በዚህም መሠረት የሐዋርያት ጾም የሚጀምረው ከጰራቅሊጦስ ማግስት ዕለተ ሰኞ ሆኖ ፍፃሜው ሐምሌ 5 ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕትነት በተቀበሉበት ቀን ነው ። ይህ ጾም ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ነውና ምዕመናን ሁላችን የሐዋርያትን በረከት ለማግኘት፤ኃይል መንፈሳዊ አግኝተን ዲያብሎስን ድል ለመንሣት እንጾማለን፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ሐዋርያት ጸሎት ይርዳን፡፡
አሜን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር!!!