ማኅበረ ቅዱሳን ካናዳ ማእከል ለማእከልና ለንዑሳን ማእከላት ሥራ አስፈጻሚ (አመራር) አባላት ለሦስት ቀናት የቆየ
ስልታዊ አመራር (strategic leadership) ስልጠና ተሰጠ።

ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግሮችን ያገናዘበና የመፍትሔ አቅጣጫን ለማመላከትና የሥራ አስፈጻሚ አባላትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ከመጋቢት 20 ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ከአሜሪካ ማእከል መምህር ትእዛዙ ካሳ ስልታዊ አመራር (strategic leadership) በሚል ከ35 በላይ የሚሆኑ የካናዳ ማእከልና ንዑሳን ማእከላት የሥራ አስፈጻሚ አባላት በተገኙበት በ Zoom ስልጠናው ተሰጥቷል።

በስልጠናው መግቢያ ሐሳብ ለማንሳት እንደተሞከረው ፦የአመራር ዘዴ እንደ ካናዳ ማእከል ሳይሆን ማኅበረ ቅዱሳን እንደተቋም የተማረ የሰው ኃይል ቢኖርም ገና የአመራር ስልቱ የሚጠበቅበት ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ ተጠቁሟል። ይኸውም በቤተ ክርስቲያንና በአገልጋዮች ላይ ፈተናዎች በተለያዩ ቁጥር ተስፋ መቁረጥ ፣አጋር በማጣት፣ምቹ ሁኔታዎች በመፈለግ፣ችግሮችን ለመጋፈጥ በመፍራት፣ቸልተኝነት ፣የአቅም ውስንነት፣ዘመኑ የደረሰበትን አሠራር ከዚያም ቀድሞ አለማሰብ ፣በግምት ሳይሆን በስሌት አለመስራት፣ይኸ ሁሉ ተደማምሮ መዳከም ቢኖርም ማኀበረ ቅዱሳን በጥቂቱም ቢሆን ለተፈጠሩ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች እሳት የማጥፋት ሥራ እየሠራ ነው። ነገር ግን የመስሪያ ክልላችንን አስፍተን ስልታዊ ትግበራችንን አጠናክረን ከመሥሪያ ክልል ውጭ በማሰብ ዘላቂ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች የመፍትሔ አካል መሆን እንዳለብን የመግቢያ ሐሳብ ተሰጥቷል።

የቤተ ክርስቲያን መዋቅር እስከ አጥቢያ ያለን አገልጋዮችና ምእመናን በጥቂት ነገሮች ከመደሰት በጉባኤ ስለተሰባሰብን ብቻ በቂ ነው ብሎ ከማሰብ ይልቅ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ፣በሰንበት ት/ቤት ፣በማኅበረ ቅዱሳን መዋቅር የራሳችንን አቅም በመጨመር እንደወቅቱ አጀንዳ የመስጠትና የመምራት ስልትን በመጠቀም ፤በትንሽ አገልግሎት እየተደነቅን ከመቆም፤ ከአጭር ጊዜ እይታ ይልቅ የረጅም ጊዜ እይታ ላይ በማተኮር የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የሆኑ ሁሉ ራሳቸውን እንደመሪ በማሰብና በመረዳት ከዘመኑ በመቅደም ራሳቸውን በማዘጋጀት ቤተ ክርስቲያን የጣለችብንን አደራ መወጣት እንደሚያስፈልግ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስን መረባችሁን በቀኝ ጣሉ እንዳላቸው ከዚያም ጌታችን ያለውን ሰምተው በቀኝ ሲጥሉት መረቡ በዓሣ እንደሞላለት ፤ሁላችን አገልጋዮች እስከዛሬ ከደከምንበት በተለየ ራሳችንን በስትራቴጂክ አመራር ውስጥ አስገብተን መረባችንን በቀኝ ከጣልነው ውጤታማ እንሆናለን መረባችንን በቀኝ ካልጣልን ከንቱ ድካም ይሆንብናል ሲሉ መምህሩ አስገንዝበዋል። አክለውም ስልታዊ አመራር ስናስብ እንደ ካናዳ ማእከል በተለየ መልኩ ከሌሎች ማእከላት በተለየ ሁኔታ ቢሠራበት ውጤታማ ሊያደርገው የሚችለውን ጉዳይ መለየት ማቀድና መተግበር አለበት። የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ፤የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ሁሉ ምቹ ሁኔታ ከመፈለግ ይልቅ መከራ በበዛበት ወቅት ስልታዊ በሆነ መንገድ በማሰብ በማቀድ በተግባር ማዋል ፤እንደ ቤተ ክርስቲያን፣እንደ ማኅበር በተቋማዊ የአመራር ስልት ራሳችንን ካጠናከርን በኋላ በማኅበራዊ ጉዳዮች በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ይቻላል ። ከዚያም በጎ ሥራ ለሠሩ ለሚሠሩ አድናቆት መስጠት ማበረታታት ለተለየ ተልእኮ ማብቃት ማገዝ ያስፈልጋል። ሲሉ አሳስበዋል። በመጨረሻው ዕለትም ከ35 በላይ የሥራ አስፈጻሚ አባላት በተገኙበት የካናዳ ማእከል የትኩረት አቅጣጫና ያሉትን ችግሮች መፍትሔ እየሰጠ እንዴት የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት መፈጸም እንዳለበት ይልቁንም ስልታዊ አመራርን በራስ ሕይወት ላይ መተግበር መጀመር እንዳለበትና ሁሉም በተሳተፉበት የጋራ ውይይት ተካናውኗል።

የውይይት አንኳር ነጥቦችም
ሀ. የማኅበረ ቅዱሳን ርእይን ለማሳካት አባላቱ ወሳኝ ናቸውና አባላት በአገልግሎት ማትጋት በተመለከተ
ለ. ከአጋር አካላት ከሀገረ ስብከትና ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ከመንግሥት ተወካዮች ጋር ያለን ግንኙነት በተመለከተ
ሐ. የሰዓታት ልዩነት ቢኖርም Task Based ሥራዎች እንዴት መፈጸም እንደሚገባ
መ. ካህናት ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ እንዲያገለግሉ በመደገፍ ወጣቶችን በተለየ ሁኔታ እንዲሠራባቸው ከማድረግ አንጻርና
ሌሎችም ሐሳቦች ውይይት ተደርጎባቸው
ካናዳ ማእከል የትኩረት አቅጣጫውን በመለየት ፕሮጀክት ተኮር ጉዳዮችን በመቅረጽ ማከናዎን እንደሚገባ የአጭርም ይሁን የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት መሠረት ያደረገ አገልግሎት መፈጸም አባላትን በማሳተፍ የሚያበረታና ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጾ፤ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በሚታዩ ነገሮች ላይ የታሪክ ባለቤት ለመሆን ያስችላቸው ዘንድ ለዚህም ሁሉንም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ባሉበት ልጆችን ሳይቀር ዘላቂነት ባለው አገልግሎት መፈጸም እንደሚገባና ፤አባላት በየ ንዑሳን ማእከላቱ በሚመቻቸው ጊዜና ሰዓት መርሐ ግብር በመቅረጽ ፣የጋራ ውይይት በማድረግ፣አገልጋዮች በሥራ ቦታ ባሉበት ሆነው ሥራ በመስጠት መከታተል ውጤታማነቱን መገምገም ይበልጥ አገልግሎቱን እንደሚያሳልጠው ተጠቁሟል። በተጨሪም ከተለያዩ ማእከላት የጋራ አጀንዳ በመያዝ ውይይቶችን በማድረግ የጋራ ስልታዊ እቅድ በማቀድ ትግበራ የሚጠይቁትን በመለየት የበለጠ መሥራትና፤ከአጋር አካላት ጋር በየጊዜው በመናበብ ይልቁንም ካህናትን ወጣቶችን ምእመናንን ያሳተፈ ዘመኑ የሚጠይቀውን አገልግሎት መፈጸም እንደሚገባ ተዳስሶበታል።

በመጨረሻም የሦስት ቀናትቱ የሥራ አስፈጻሚ (አመራር) ስልጠና በተመለከተ በሰልጣኞች አስተያየትና በማእከሉ ም/ሰብሳቤ አቶ ሳሙኤል ማሞ የወደፊት የማእከሉ ትኩረት የሚሰጡ ጉዳዮችን በተመለከተ መልእክት ተላልፎ፤በአባታችን በሊቀ ትጉኀን ቀሲስ አልዓዛር ምክረ ሐሳብ ተሰጥቶ ጉባኤው በጸሎት ተፈጽሟል።