በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
“ልትድን ትወዳለህን?” ዮሐ. 5፥6

በመ/ር ሃፍታሙ ኣባዲ

አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት “መጻጒዕ” ይባላል፡፡ መጻጒዕ መጠሪያ ስም አይደለም፡፡ ደዌ የጸናበት፣ በሽተኛ፣ ሕመምተኛማለት ነው እንጂ፡፡ ስያሜው እንደ ሌሎቹ የዐቢይ ጾም ሰንበታት በኢትዮጵያዊው ሊቅ በቅዱስ ያሬድ የተሰየመ ሲሆን በዮሐንስ ወንጌል 5፥1-17 ላይ ተጽፎ የምናገኘው ደዌው የጸናበት፣ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቍራኛ ተይዞ የነበረ፥ ከደዌው ጽናት የተነሣ “መጻጒዕ” ተብሎ የተጠራ እና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈወሰ በሽተኛ ሰው ታሪክ መነሻ ያደረገ ስያሜ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “አሕየዎ ኢየሱስ ለመጻጉዕ ወፈወሶ በዕለተ ሰንበት – ኢየሱስ መጻጉዕን በዕለተ ሰንበት አዳነው ፈወሰው” እንዳለ። በረከቱ ይድረሰን ምልጃው አይለየንና ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በወንጌሉ አምስተኛው ምዕራፍ “በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፥ አምስት መመላለሻ ነበረባት።” ይለናል። ቤተ ሳይዳ ማለት ቤተ ሣሕል ማለት ነው፡፡ ቀጥሎም “በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸውም ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር።” ይላል፡፡ ቁጥር 3-4። መልአኩ ወደ ውኃው የሚመጣው አንድ ጊዜ ነው፥ አይቀርም። የሚመጣውም በቀዳሚት ሰንበት (ሰንበተ አይሁድ) ነበር። ቀድሞ ወደ ውኃው የገባ ይፈወሳል፤ ፈውሱ ግን አይደገምም። አለመቅረቱ ተአምራቱ በአባቶቻችን ጊዜ ይደረጋል እንጂ በእኛ ዘመንስ ቀርቷል እንዳይሉ፥ አለመደገሙ በኦሪት ፍጹም ድኅነት እንዳልተደረገ የሚያጠይቅ ነው።

መልአኩ የቀሳውስት፣ ውኃ የጥምቀት፣ አምስቱ እርክን የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር፣ አምስቱ ድውያን የአምስቱ ፆታ ምዕመናን ምሳሌ ናቸው። አምስቱ ጾታ ምዕመናን የሚባሉት አዕሩግ፣ ወራዙት፣ አንስት፣ ካህናት እና መነኮሳት ናቸው፡፡ የአዕሩግ ፆራቸው ፍቅረ ንዋይ ነው፥ ማን ይረዳናል እያሉ ገንዘብ ይሰበስባሉ። ይህን ትቶ በወራዙት ጾር በዝሙት ይቃወማቸዋል፥ በጥምቀት ባገኙት ኃይል ድል ይነሱታል። የወራዙት ጾር ዝሙት ነው። ይህን ትቶ በፍቅረ ንዋይ ይዋጋቸዋል በጥምቀት ባገኙት ኃይል ድል ይነሡታል። የአንስት ጾራቸው ትውዝፍት፣ ነው የምንዝር ጌጥ። ይህን ትቶ በሌላ ጾር ይዋጋቸዋል፥ በጥምቀት ባገኙት ኃይል ድል ይነሡታል። የካህናት ጾራቸው ትዕቢት ነው፣ አእምሯችን ረቂቅ መዓርጋችን ምጡቅ እያሉ ይታበያሉ። ይህን ትቶ በሌላ ፆር ይቃወማቸዋል፥ በጥምቀት ባገኙት ኃይል ድል ይነሠታል። የመነኮሳት ጾራቸው ስስት ነው። በሹት በፈለጉት ጊዜ አያገኙትምና ይህን ትቶ በአንስሐስሖ ዘበከንቱ (በከነቱ መነሳሳት፣ መሻት) ይቃወማቸዋል በጥምቀት ባገኙት ኃይል ድል ይነሱታልና። እነዚህ በየጾታው የተጠቀሱ ፈተናዎች በዘመናችንም ጎልተው የሚታዩ ፈተናዎች ናቸው። በጥምቀት ባገኘው ኃይል መንፈሳዊ ፈተናዎቹን ድል ማድረግ እንዲቻለን የጥምቀት ጸጋችንን መጠበቅ ይኖርብናል።

በዚህች በቤተ ሳይዳ ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነውን በሽተኛ (መጻጕዕ) ነበረ። በባሕርይው መሐሪ የሆነ ጌታ ደዌ እንደጸናበት በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ እንደተያዘ አውቆ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው። ጌታችን የፍቅርና የነጻነት አምላክ ነው በራሱ ድኅነት ራሱ እንዲወስንና እንዲፈቅድ ጠየቀው። በዕለተ ዓርብ በጥፊ የሚመታው ነውና “ያዳነህን በጥፊ ትመታለህን?” ቢሉት “ሳልጠይቀው በራሱ አዳነኝ እንጂ አድነኝ ብዬው አዳነኝን?” እንዳይል ምክንያትን ለማሳጣት ጠየቀው። የአዳምና ሔዋን ሕይወትና ሞት በተሰጣቸው ነጻ ፈቃድ (ዕጸ በለስ ባለመብላት እና በመብላት) የተመሠረተ እንደ ነበረ ሁሉ የመጻጉዕ ድኅነትም በራሱ ውሳኔ ላይ እንደሆነ ለማስረዳት “ልትድን ትወዳለህ?” ብሎ ጠየቀው። አዳኝና ሕይወት ሰጪ እርሱ ሆኖ ሳለ ለራሳችን ጥቅም የእኛን ፈቃድ የሚጠይቅ ግን ደግሞ ሁሉም የማድረግ ሥልጣን ያለው የፍቅር አባት ነው አምላክችን።

መጻጉዕ “ልትድን ትወዳለህን?” ተብሎ ሲጠየቅ “ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።” ጌታችንም “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ።” ዮሐ. 5፥7-9። ጥበብ እርሱ ጥበብ የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ጌታ በሽተኛውን ፈውሶ ሂድ ብቻ አላለውም አልጋህን ተሸከም አለው እንጂ። ደዌውን ምንኛ ጽኑ እንደነበረች ምን ያህልም እንደፈወሰው ይረዳና ያስተውል ዘንድ እንዲህ አለው።

በዘመናችን በደዌ ሥጋ ብቻ ያይደለ በደዌ ነፍስ ተይዘናል። ጥል፣ ክርክር፣ ዘረኝነት፣ መለያየት፣ እኔ ብቻ ይድላኝ ማለት፣ ለሥጋ ፍትወት መገዛት፣ ትዕቢት፣ ኑሮዬ ይበቃኛል አለማለት እና የመሳሰሉ የሥጋ ፈቃዳት ሰልጥነውብን፤ የመንፈስ ፍሬ ማፍራት አቅቶን፤ ለቤዛ ቀን የታተምንበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ እያሳዘንን፤ ከመልካም ምግባር ርቀን፣ ከጽድቅ ተራቁተን ባለንበት በዚህ ዘመን እንኳን “ልትድን ትወዳለህን?” ብሎ ሲጠይቀን “ጌታ ሆይ አድነን፣ የዳዊት ልጅ ሆይ ማረን፣ አቤቱ ይቅር በለን” እያልን አብዝተን ልንጮህ ይገባናል። አባታችን ቅዱስ ያዕቆብ “ካልባረከኝ አልለቅህም እንዳለ እኛም “አቤቱ አምላካችን ሆይ! በመሐሪነትህና በይቅር ባይነትህ ካልማርከን፣ የቀደመው በደላችንን ካልተውክልን፣ ወደ አንድነት ካልመለስከን፣ ከዘመኑ የዘረኝነት ክፉ ደዌ ካልፈወስከን አንለቅህም ዕለት ዕለትም ወዳንተ መጮህን አናቋርጥም” ልንለው ይገባል።

መጻጉዕ የዳነው በቀዳሚት ሰንበት (ሰንበተ አይሁድ) ነበርና ልባቸው ለክፋት ለምቀኝነት የማያርፍ አይሁድ የተፈወሰው ሰው አልጋውን ተሸክሞ ሲሄድ አይተው “ሰንበት ነው አልጋህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም” አሉት። በበሽተኛው መዳን ከመደሰት፥ በጌታ የማዳን ሥራ ከመደነቅ እግዚአብሔርንም ከማመስገን ይልቅ ልባቸው በከንቱ ቅንዓት ተጠመደች። ሰንበትን ያከበሩ መስሎአቸው ሰንበትን ያከበረ ያከበሯት ዘንድም ያዘዛቸው የሰንበት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ያደረገውን ድንቅ ሥራውን ተቃወሙ። ልቦናቸው ታውሯልና የሚያደርጉትን አያውቁም ነበር። ፍጡር ከፈጣሪው ሥራ ከሠሪው ተከባሪ ከአክባሪው እንደማይበልጥ ማን በነገራቸው።

የዳነው ሰውም “ያዳነኝ ያ ሰው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” ብሎ ለአይሁድ መለሰላቸው። ያ ሰው ማን እንደሆነ በጠየቁት ጊዜ በዚያ ስፍራ ሕዝብ ስለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም። ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውዬውን በመቅደስ አገኘውና “እነሆ ድነሃል ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ” አለው። እንግዲህ “ከዚህ የጠና እንዳያገኝህ ሁለተኛ እንዳትበድል አስተውል” ያለው ከዚህ የጠና ምን ቢኖር ነው እንዲህ ያለው?” ቢሉ የቀድሞው ደዌ ሥጋ ነበር ዛሬ ግን ደዌ ነፍስ ነው የሚያገኝህ ሲለው ነው። ይህም አልቀረ በዕለተ ዓርብ ጌታን በጥፊ ቢመታው የመታበት እጁ ሰሎ ደርቆ ቀርቷል። አራት ዓይነት ደዌ አለ። ደዌ ዘንጽሕ፣ ደዌ ዘዕሤት፣ ደዌ ዘመቅሠፍት እና ደዌ ዘኃጢአት። ደዌ ዘንጽሕ እንደ ጢሞቴዎስ ደዌ ዘዕሤት እንደ ኢዮብ ደዌ ዘመቅሠፍት እንደ ሳኦል እንደ ሄሮድስ ደዌ ዘኃጢአት እንደዚህ ሰው (እንደ መጻጉዕ) ያለ ነው።

“ታሞ የተነሣ እግዚአብሔርን ረሳ” እንዲሉ አበው፥ ሰውዬው ግን ጌታችን ያደረገለትን ረሰቶ የተናገረውን ቃል ትቶ ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደሆነ ለአይሁድ ነገራቸው። የትናንት በደላችንን ፍጹም ይቅር ብሎ ዳግም እንዳንበድል ዕድል የሰጠን ጌታን ትንሽ እንኳን ሳንቆይ መበደል፣ ያዳነንን ለከሳሾቹ አሳልፎ መስጠት ምንኛ ከባድ ጎስቋላነት ነው? “ከበሽታዬ እንድድን እወዳለሁ ነገር ግን ሰው የለኝም” ብሎ የልቡን ሐዘን የተናገረው መጻጉዕ ለእነዚያ በበሽታው ጊዜ ለረሱት እና ለተጸየፉት “ሰው የለኝም” እስኪል ድረስ ለዘነጉትና ለጣሉት ሰዎች ያዳነውን ጌታ አሳልፎ ሰጠው። “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” ይሉሃል እንዲህ ዓይነቱ ነው። በዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበት ይህንን የማዳን ሥራ ስለሠራ አይሁድ ያሳድዱት ነበር።

በዘመናችን መልካም ስለ ሠራ በዓለም የሚሰደድ፣ የሚሰደብ፣ የሚታሰር፣ የሚንገላታ፣ የሚጠላ፣ የሚገለል ክርስቲያን ቢኖር በሽተኛን በማዳኑ ምክንያት በአይሁድ ዘንድ የተጠላውን፣ የተሰዳደውን ጌታን፤ ጽድቅ ስለ ሠሩ እውነት ስለመሰከሩ ብቻ በዓለም የተሰደዱትን ኢየሱስ ክርስቶስን የመሰሉትን ቅዱሳንን ሊያስብ ይገባል። በክርስትና ሕይወታችን በቅዱስ ወንጌል “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፣ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ” የተባለውን ዘወትር ማስታወስ አለብን። ማቴ. 5፥10-11።

ከዘመኑ ደዌ እንድንድን ወደ እውነተኛው መድኃኒት ወደ አምላካችን መቅረብ ይገባል። ያዳነን ጌታን ከቅዱሳኑ ጋር እያመሰገንን በቤተ መቅደሱ ጸንተን መኖርን ይሰጠን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። በዘመናችን ካለው የዘረኝነት፣ የመከፋፈል፣ የመጠላላት፣ የመጠፋፋት፣ የእልቂት በሽታ ያድነን። በዋናነት ደግሞ ከልብ ዕውርነት ደዌ ፈውሶ በሃይማኖት በምግባር ጸንተን ለመኖር ያብቃን።

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።