በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

“ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች።” (ማቴ 21÷13)

በአክሊለ ሰማዕት

ምኩራብ

ቤተ መቅደስ ከደብተራ ኦሪት (ድንኳን) በኋላ ተሠርቶ ለአገልግሎት የበቃው በንጉሥ ሰሎሞን ሲሆን፤ ይኸውም ናቡከደነፆር አፍርሶት በድጋሚ በዘሩባቤል ተሠርቶ ነበር፡፡ በዚህ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህናቱ በዓመት አንድ ጊዜ በአይሁድ ፋሲካ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ የእንስሳ መሥዋዕት አቅርቦ ደሙን እየረጨ የራሱንም የሕዝቡንም ኃጢአት ያስተሠርይ ነበር፡፡ ለጊዜያዊ አገልግሎቶችም የርግብና የሌሎች እንስሳት ደም መስዋዕት እንዲቀርብላቸው የሚፈልጉ ሰዎች እንስሳቱንም ርግቦችን ከዚያው ይገዙ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ነበር በአካባቢው ይህን የመሰለው ገበያ የተፈጠረው፡፡ በዚሁ ላይ ደግሞ አገልጋዮቹ የሰባውን በከሳው በሬና ላም እያቀያየሩ አለአግባብ ገንዘብ ያተራረፉና ይወስዱ ነበር፡፡ ስለዚህም ከገበያው ትርምስ በተጨማሪ አካባቢው በከሲታ እንስሳት ግርግርና ቆሻሻ ተሞልቶ ነበር፡፡ ይህ ተግባር የመቅደሱን ክብር ነክቶት ነበርና አገልግሎቱም ተዳክሞ እንደ ምኩራብ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ምኩራብ እንደ ዳስ ወይም አዳራሽ የሚሠራና አይሁድ በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ሊኖር የሚችል፤ የራሱ አለቃ ያለው፤ ሕግና ነቢያት የሚነበቡለት የጉባኤ ቦታ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ምኩራብ የእንስሳ መስዋዕት አይቀርብበትም ነበር፡፡ የዚሁ ምኩራብ የተሰኘው ሰንበት ስያሜም የተገኘው ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ሔደ ብሎ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ከዘመረው በመነሳት ነው፡፡ ጌታችን በምኩራብ ተገኝቶ መጽሐፍ ተርጉሞአል፤ቃሉን አስተምሮአል፤ ድውያንን ፈውሶአል። ስለዚህም ወደ ምኩራብ የሔደው አንዴ ብቻ አይደለም፤ ይህ በዮሐ 2-12 የተጠቀሰው ግን በኃይል ሥራ የሠራበት ስለሆነ ነው፡፡ ይኸውም ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ጅራፍ አንስቷል፤ ሻጮች ለዋጮችን አስነስቷል፤ እንዲሁም፤ እንስሳቱን እየገረፈ አስወጥቷል፡፡ ወንጌል “በገመድ ጅራፍ አበጅቶ” ያለችው ደቀመዛሙርቱ አበጅተውለት ነው፡፡ ይህም በእሱ ትዕዛዝ የተሠራ ስለነበር ነው፡፡ ማለትም አሽከር የሠራው ለንጉሥ እንደሚሰጥ ያለ ነው፡፡ የሻጮች የለዋጮችን መደብ ቢገለባብጥባቸውም ንብረታቸውን ግን በተአምራቱ በየራሱ ሳይደባለቅ አግኝተውታል፡፡ እንስሳቱንም እየገረፈ ማስወጣቱ የኦሪት መሥዋዕት ከዚህ በኋላ እንደማይጠቅም ለማጠየቅ ነው፡፡ እውነታውም የኦሪት መሥዋዕት ጊዜአዊ ሥርየት ከማሰጠት ውጪ ዘለዓለማዊ ድኀነት አላመጣም፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ሊቀ ካህናቱ በዓመት አንድ ጊዜ የሚያደርገውን የሥርየት መሥዋዕት ደግሞም በቀጣዩ ዓመት ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ፍጹም ንጹሕና እና ዘለዓለማዊ ድኅነት እንዳላመጣላቸው ሕሊናቸው ስለሚመሰክርባቸው ነው፡፡ ከሥጋ ኃጢአት እንጂ ከነፍስ ቁራኝነት ወይም ሲኦል ከመውረድ አላዳነምና ይህንን ዘለዓለማዊና ፍጹም ድኅነት ለማምጣት ንጹሕና ፍጹም መስዋዕት ያስፈልግ ነበርና፤ የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ የተወለደው አምላክ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ይሄንኑ ሊያደርግ ነበር የመጣው፡፡ እንስሳቱንም ማስወጣቱ እርሱ ፍጹም፣ እውነተኛ እና ዘለዓለማዊ ድኀነት የሚያሰጥ መሥዋዕት ሆኖ ወደ መቅደስ መግባቱን ለማመልከት ነው፡፡ የአማናዊው በግ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙም በዚህ ምክንያት የተሰጠነና ዕለት ዕለት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚዘጋጀው መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ፤ የዘለዓለም ሕይወትንም የሚሰጥ ነው፡፡

ተግሳጹ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት የሚል ነበር፡፡ ለጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ መቅደስ በአሁኑ አጠራር ቤተ ክርስቲያን አካሉ ናት፤ ቤቱም ናትና ደግሞ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች አላት፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት በላችኝ፣ አቃጠለችኝ የተባለውን የነቢዩ ዳዊትን ትንቢት አስታወሱ፡፡ እግዚአብሔር በሁሉ የመላ አምላክ ቢሆንም የክብሩ መገለጫ የተለየ ቦታ ያስፈልገዋል፡፡ ይኸውም ቤተ መቅደስ ቤተ እግዚአብሔር ነው፡፡ ክቡር ዳዊት ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ እንዳለ፡፡ ቤተ እግዚአብሔር ማምለኪያ መማጸኛ፤ የእንባ ማፍሰሻ፤ የኃጢአት መደምሰሻ፤ የስሙ መቀደሻ ናት፡፡ “እኔ ግን በምህረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ ስምህንም በመፍራት ወደ መቅደስህ እሰግዳለሁ” (መዝ 137-1) እንዳለ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣው ወይም የሚገለገለው በፍርሃት ነው፡፡ ጌታችን ግን ሥርዓት ያጣና ድፍረት የተሞላው እንዲሁም ግርግርና ጫጫታ የበዛበት ገበያ እስኪመስል ድረስ ተበላሽቶ ስላገኘው በተግሳጽና በጅራፍ ጭምር አስተካከለው፡፡ በተጨማሪም አብ የመረጣት ወልድ ያደረባት መንፈስ ቅዱስ የጸለላት እንደአበርሃም ድንኳን የሥላሴ ማደሪያ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ለልጇ ቤቱ ናት፡፡ “እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታል፤ ማደሪያው ትሆን ዘንድ” እንደተባለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅጸኗ አድሮ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ተዋህዷልና፡፡

የቤትህ ቅናት በላችኝ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ላይ ወደቀ እንደተባለ (መዝ 68-9) ሁለቱም ከእኛ ከክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡በቅድሚያ የቤቱ ቅናት ሊቃጥለን ይገባል፡፡ በቤተ ከርስቲያን አካባቢ ለአምልኮተ እግዚአብሔር የማይመጥን ተግባር ስናይ ሊሰማን ይገባል፡፡ የማይገቡ ጩኸቶች፤ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጋር የማይገናኙ ገበያዎች፤ በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውስጥ የማይገባ ዓለማዊ ወሬና ሳቅ የሚያደርጉ ሰዎች፤ በቅዳሴ ጊዜ ወዲያ ወዲህ የሚመላለሱ ሰዎች፤ ሌላውን በፍቅር መምከር ሲገባ በቁጣ የሚያሰደነግጡ፤ ከሕግ እግዚአብሔር ውጪ የሆነ አለባበስ የሚጠቀሙ ሰዎች፤ካለቅጥ የሚጮሁና ከመጠን የበዙ እንዲሁም ያልተፈቀዱ የመዝሙር መሣሪያዎች፤ አሥራት በሚገባ ባለመክፈላችን ቤተ ክርስቲያን ሳይገባት የምታደርጋቸው የገንዘብ ማሰባሰቦች፤ በቅዳሴ ማብቂያ ላይ ልጆቻቸውን ለማቁረብ የሚመጡ ወላጆችና ሌሎችም ችግሮች በእውነት ሊያቃጥሉን ይገባል፡፡ ይህም በሌሎች ለመፍረድ ሳይሆን እኛም ከእነዚህ ተግባራት ራሳችንን እንድንጠብቅ፤ ሁኔታዎቹ ደግሞ እንዲስተካከሉ በፍቅር እንድንነጋገርና እንድንመካከር ነው፡፡ ቤቱ ድንግል ማርያምም ክብር ይግባትና የማይገባትን ስም የሚሰጧት አሉ፡፡ የሚሰድቡህ ስድብ በላዬ ወደቀ እንደተባለ፤ አቤቱ በድንግልና ተጸንሰህ በድንግልና መወለድህን፤ የዘር ኃጢአት ካላገኛት ከንጽሕት ድንግል መወለድህን፤ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ መንሳትህን፤ ሰው የሆንክ አምላክ መሆንህን፡ በመስቀል ሞተህ መነሳትህንና ወደ አባትህ ማረግህን ወዘተ መካዳቸው ተሰማኝ የምንል ክርስቲያኖች መሆን አለብን፡፡ የድንግል ማርያምም ወላዲተ አምላክነት፤ ዘለዓለማዊ ድንግልና፣ ቃል ኪዳንና አማላጅነት ሲካድ የሚያሳዝነን መሆንም ይገባናል፡፡ የቤቱ ቅናት የሚያቃጥለን ክህደቱና ስድቡ የሚሰማን የሚያመን እንድንሆን አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር