እሰመ ቅንዓተ ቤትከ በልአኒ = የቤትህ ቅንዓት በላኝ ! መዝ ፷፰፥፱

/ሊቀ ጠበብት ማኅቶት የሻው/

ይህ የአቢይ ጾም የሦስተኛው ሣምንት ስያሜ ነው፤
ሠያሚውም ቅዱስ ያሬድ ነው
ምኩራብ = አዳራሽ ፣ ቤተ ጸሎት ፣ቤተ መቅደስ / የአይሁድ / የሚል ፍች ይኖረዋል ፤
ምኩራብ _ በብሉይ ኪዳን በየትኛውም ቦታ ይሠራ ነበር::  ቤተ መቅደስ ደግሞ ከኢየሩሳሌም ውጭ አይሠራም ነበር ፤ አሠራራቸውም ከስሙ እንደምንረዳው _
አዳራሽ አንድ ወጥ የሆነ ሰፋ ያለ ቅርጽ ሲሆን: ቤተ መቅደስ ደግሞ በተለያየ ቅርጽ ይሠራል ። ይህም በውስጡ ቅድስት ፣ቅኔ ማኅሌት እና መቅደስ የሚባሉትን ክፍሎች አካቶ ይይዛል ።

አንድነታቸው ደግሞ ሁሉም የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማሪያ መማሪያ ናቸው ። ይህ የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበት ቅዱሳን መላእክቱ 24 የማይለዩበት: ካህናቱ ከካህናተ ሰማይ ጋር ዘወትር የሚያመሰግኑበት: ምዕመናን ዘወትር በጸሎትና በምጽዋት ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙበት፣ እግዚአብሔርን በአንድነት ሆነው የሚያመልኩበት፣ የሚቀደሱበት፣ የሚዘምሩበት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ: ዳዊት በትንቢት መነጽር ክፉ ነገር በማየቱ በቁጭት “የቤትህ ቅንዓት በላኝ እንደ እሳትም አቃጠለኝ”  አለ::  ምክንያቱም አንተን በምናመልክበት በቤተ መቅደስህ አይሁድ ሥዕለ ጸሐይ አቁመውበት መሥዋዕተ እሪያ ሠዉተውበት ባየሁ ጊዜ ተበሳጨሁ ቀናሁ ብሏል በኀዘን ሰሜት ፤እንዲሁም አንተ አምላካቸው መናን ከደመና አውርደህ ውሃን ከዐለት አፍልቀህ ብታጠጣቸው ምንት ጣዕሙ ለዝ መና ወማይ ብለው ማጉረምረማቸውንና መገዳደራቸውን ሳይ ቀናሁ አቃጠለኝ ፤ ከሁሉም በላይ አንተ << ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው >> ዮሐ 6_52 ብለህ ብታስተምር እነሱ / የሰው ልጆች/ እንበላው ዘንድ ሥጋውን እንዴት ሊሰጠን ይችላል ብለው በመገዳደራቸው ይልቁንም በተቃራኒው ቤተ መቅደስሀን የንግድ ማዕከል ፣የገባያ አዳራሽ አድርገውት በማየቴ ተበሳጨሁ ቀናሁ እያለ በሀዘን በቁጭት ነፍሴንም በጾም አስመረርዃት ቀጣኋት ብሏል ።
በዚሁ ቀን ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ካስተማረ በኋላ ፣ ብዙ ከታገሰ በኋላ ቁጣውን ገልጿል ።

በዚህ ቀን

1) ቤተ መቅደሱን ያሰከበረበት ፣ያጸዳበት ፣ያነጻበት  ፣የለየበት ፣የቀደሰበት “ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ” ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል እንጅ የንግድ የገበያ ማእከል: የወንበዴዎች የአጭበርባሪዎች አይደለም ብሎ በውስጡ የሥጋ ገበያ የሚያካሂዱትን በጅራፍ እየገረፈ አስወጥቶ ቤተ መቅደሱን ያስከበረበት ዕለት ነው ። ዮሐ 2፥12

2 ) ሃይማኖት አለን ብለው ምግባር የሌላቸውን የገሠጸበት ፣የወቀሰበት፣ ስለቤተ መቅደሱ የቀናበት ቀን ነው:: (ያዕ 2፥14) በዚሁ ምኩራብ ተገኝቶ ለታሠሩት ነጻነትን ፣ለሞቱት ሕይወትን፣ በጨለማ ለሚመላለሱትም ንስሐን፣ በፍዳ የነበሩትን አመተ ምሕረትን እንዳስተማረ ቅዱስ ያሬድና ሊቃውንቱ የቀመሩት ምጡቅ መንፈሳዊ መጻሕፍት ያስረዱናል ። እንደ ቆርነሌዎስና ቤተሰቡን ቤተ መቅደሱን ያከበረ እንደሚከበር ይልቁንም ጸሎቱ ቅድመ እግዚአብሔር እንደሚደረስ የምንማርበት ነው:: በተቃራኒው በምን አለብኝነት እንደ አይሁድ በድፍረት ያለንሰሐ ሕይወት በባዶ መመላለስ እንደሚያስቀጣ: የዘመናችን የኮረና ጅራፍ አሳይቶናል:: እራሳችን የገመድንው የዘረኝነት ጅራፍም እራሳችንን እየገረፈ ከቤተ መቅደሱ እንዳሰወጣን ተምረንበታል ። ስለዚህ ሕንጻ ቤተ መቅደሱን አገልግለን ፣ ሕንጻ እግዚአብሔር ሰውን አክበረን ፣ ሕንጻ ቤተ መቅደስ ሰውነታችንን / ሕይወታችንን / በንስሐ አድሰን ከነቆርነሌዎስ ለመደመር ያብቃን ይቆየን::

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር !