“ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ፡— ልትድን ትወዳለህን? አለው።” ዮሐ 5፥6

ዲ/ን ደምሴ ታደለ

መጋቢት11, 2014 ዓ.ም.

የዐቢይ ጾም ዐራተኛው ሳምንት መፃጉዕ በመባል ይታወቃል። መፃጉዕ ለ38 ዓመታት በአልጋ ቁራኛ  ተይዞ በቤተሳይዳ በሚገኘው የመጠመቂያ ቦታ ተኝቶ ድህነትን ይጠብቅ ነበረ። የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ውኃውን  ሲያናውጠው መጀመሪያ የገባ ብቻ ይድን ነበር። ለ38 ዓመታት ማለትም ለ13,879.5 ቀናት መልአኩ እየመጣ ቢያናውጠውም መፃጉዕ  ግን የመግባትና የመፈወስ እድልን አላገኘም። ወደውኃው የሚያስገባው ሰው በማጣቱ፣ ዘመድ አዝማዶቹ ስለተሰላቹት። ጌታችን ግን ውኃውን ማናወጽ ሳያስፈልገው፣ “ልትድን ትወዳለህን? አለው።” ዮሐ 5፥6 መዳን የሚቻለው በውኃ ውስጥ ብቻ በመግባት ስለመሰለው  ችግሩን ዘረዘረ”፡— ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።” ዮሐ 5፥7 ። በበሽታዎችና እርኩሳን አጋንንት ላይ ስልጣን ያለው ጌታ “ተነሳና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ”አለው::  38 ዓመታት በተሸከመው አልጋ ስልጣን ኖረውና ተሸከመው።

እግዚአብሔር ለሚሰራው ድንቅ ሥራ ጊዜ አለው፣ “መፃጉዕ  ለ38 ዓመታት ባለበት ቦታ ሆኖ ጠበቀ”ተብለን ስንማር እኛስ ለምን ያህል ጊዜ የመጠበቅ ትእግስት አለን? በተለይ ያመንን የተጠመቅን የአምላካችንን የማዳን ሥራና ጥልቅ ፍቅሩን ለተረዳን ጥበቃችን እስከምንድረስ ነው? የሚለውን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ለሚደርስብን ፈተና የእግዚአብሔር መልስ እስከ መቼ ነው? በማህበራዊ ሕይወታችን ብዙ ውጣ ውረድና ምስቅልቅል ለገባን እስኪስተካከል እስከመቼ እንጠብቅ? በቤተሰብ (በትዳር)ሕይወታችን በፈተና ውስጥ ለወደቅን እስከመቼ ነው የምንታገሰው? ለሁሉም መልስ ባለንበት ቦታ ሆነን በጾምና በጸሎት ጸንተን መጠበቅ አለብን።

እግዚአብሔር የሚያመጣው መፍትሔ ሁሌ እኛ በምንጠብቀው መንገድ ብቻ አይደለም፣ እግዚአብሔር ችግርን የሚፈታበት መንገዱ ብዙ ነው። ስለዚህ ጌታችን ችግሮቻችንን መፍትሔ ከሰጠን በኋላ፣ በወደቅንበት ፈተና ደግመን መውደቅ የለብንም።

“ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና፡— “እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ፡ አለው።” ዮሐ 5፥14

ከችግሮቻችን መፍትሔ ማግኘት በኋላ ደግመን ከወደቅን ለመነሳት እጅግ አደገኛና አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። በመሆኑም ራሳችንን ፈተና ላይ መጣል የለብንም። መፃጉዕ ኋላ ላይ የቀድሞን ድህነቱን ረስቶ ጌታን በእለተ ስቅለቱ በጥፊ እንደመታው ይነገራል። ይህ ከውድቀት ሁሉ የከፋ ውድቀት ነው። በመሆኑም መጻጉን ስናስብ ውድቀቱን ሳይሆን ድህነቱን፣ አልጋውን መሸከሙን እና በአልጋው ላይ የኖረበትን ዘመንን ልናስብ ይገባል። እግዚአብሔርን በትእግስትና በጸሎት ጠብቀን ከችግሮቻችን ሁሉ የምንወጣበትን መፍትሔ ይሰጠን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን።

እግዚአብሔር ከጾሙ በረከት ረድኤት ያድለን።