ደብረ ዘይት
የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት
አክሊለ ሰማዕት
መጋቢት 17, 2014 ዓ.ም.
.
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመድጓው የዐቢይ ጾም ሳምንታትን ከፋፍሎ ሲያስቀምጥና አገልግሎቱን በምስጢር ሲያስተሳስር አምስተኛውን ሰንበት ደብረ ዘይት ብሎታል፡፡
.
ደብረዘይት ደብር እና ዘይት የሚሉ ቃላት ጥምር ሲሆን የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ማለት ነው፡፡ ይህ ተራራ የሚገኘው ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ በኩል ነው፡፡
.
በደብረዘይት ተራራ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈጸማቸው ተግባራት መካከል ቀን ሲያስተምር ውሎ ሌሊት ይጸልይበት ነበር (ሉቃ.21÷37)፡፡ በተጨማሪም ስለ ዓለም ፍጻሜና ምልክቶቹ ለደቀመዛሙርቱ አስተምሮበታል (ማር.13÷3)፡፡ እንዲሁም ወደ ሰማይ ያረገው ከዚሁ ደብረ ዘይት ተራራ ነበር (ሉቃ. 24÷51)፡፡ በቅድስት ቤተክርስቲያናችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ መምጣቱ በዚሁ በደብረ ዘይት በዓል የሚታሰበው፣ የሚሰበከውም በዚያው ስፍራ የመጨረሻውን ምልክት በማስተማሩ እንዲሁም ዳግመኛ ለፍርድ ሲመጣ በደብረ ዘይት ተራራ አንጻር በመሆኑ ነው፡፡
.
ጌታችንን በወንጌል የዘመኑን ፍጻሜ ሲያስተምር በአስር ቆነጃጅት ምሳሌ አድርጐ ነበር (ማቴ. 25÷1)፡፡ በዚህም ዕለተ ምጽአትንም ዕለተ ሞትንም አገናዝቦ ማስተማሩን ሊቃውንት አባቶቻችን ተርጉመውልናል፡፡ አንዳንድ ሰው ዕለተ ምጽአት መቼ እንደሚሆን ቢያውቅ ደስ ይለዋል፡፡ ነገር ግን ሞቱ ከቀደመችው አይጠቅመውምና መዘጋጀት የሚገባው ከዕለተ ሞት በፊት መሆኑን የአስሩ ቆነጃጅት ምሳሌ ያስተምረናል፡፡ ይህንንም ሲገልጽ “ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ተኙ ” (ማቴ. 25÷5)ይላል፡፡
.
ሙሽራው በመጣ ጊዜም የተቀበሉት ቀድመው ባዘጋጁት ዘይት እንደነበረ: አምስቱ በቂ ሌሎች አምስቱ ጥቂት እንደነበራቸውና ዝግጅታቸው ጥሩ አለመሆኑን ወንጌል ይነግረናል፡፡ ይህም ማለት ቀድሞ የተዘጋጁት ልባም ቆነጃጅት ከሙሽራው ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መንግስት ሰማያት የሚገቡት ምግባር ትሩፋት ከሃይማኖት ጋር አስተካክለው የያዙ ምዕመናን ምሳሌዎች መሆናቸው ነው፡፡ ሃይማኖት አጽንቶ ምግባር ትሩፋት ሰርቶ መገኘት የሚገባው ከሞት በፊት ነውና፡፡ ይህን ያላደረጉት ሃይማኖት ከምግባር አስማምተው ያልያዙት ሰነፎች ቆነጃጅት ለመልካም ስራ ቀጠሮ ሲያበዙ ሞት የቀድማቸውና በሩ የተዘጋባቸው ምዕመናን ምሳሌ ናቸው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአክሊለ ስብአት በግርማ መለኮት በሚመጣ ጊዜ እንደቀድሞ ለመከራ ለመስቀል ያይደል የመጨረሻውን ፍርድ በኃጥአንና በጻድቃን ላይ ይሰጣል፡፡ ማለትም በጻድቃን “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ፤ ዓለም ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር ወደተዘጋጀላችሁ ስፍራ ግቡ” ብሎ ይፈርድላቸዋል፡፡ በኃጥአን ላይም “ከእኔ ሂዱ” ብሎ ይፈርድባቸዋል፡፡ የቀኝና የግራ ቁመትንም በበግና በፍየል መስሎ አስቀድሞ ተናግሮታል ለምሳሌም ፍየል ኃፍረቷን አትሸፍንም እንደዚሁም ኃጥአን የወንድማቸውን በደል በይቅርታ፣ የራሳቸውን በደል በንስሀ አይሸፍኑም፡፡ ስለዚህም በግራ መቆም ወይም የገሃነም ፍርድ ይጠብቃቸዋል አለ፡፡ ጻድቃንም ከጸሐይ ሰባት እጅግ አብርው በቀኙ ይቆማሉ መንግስቱን ይወርሳሉ፡፡
.
ጌታችን ይሄንና የመጨረሻውን ዘመን ምልክት ያስተማረው በዚሁ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነበር፡፡ የመምጫው ምልክት የሚሆኑትን መከራዎች ሁሉ ለደቀመዛሙርቱ አስረድቶ ለእኛም በቅዱስ ወንጌሉ ደርሶናል፡፡ በተጨማሪም ቀድመው የተነገሩትን ምልክቶች በጆሮአችን እንደሰማን፤ በአይናችን እያየን ያለን ትውልድ መሆናችንን ማስተዋል ይገባል፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት አንጻር ፀሐይ በምስራቅ ወጥታ በምዕራብ እንደምትታይ ሁሉም በግልጽ እያየው ይመጣል(መዝ.49÷2)፡፡ ሲመጣም ከእመቤታችን ከቅድሰት ድንግል ማርያም በተዋሀደው ሥጋ በግርማ መለኮቱ ነው፡፡ ይህም እንዲታወቅ ከደብረ ዘይት ተራራ በደቀመዛሙርቱ ፊት ባረገ ጊዜ መላእክት “… ከፍ ከፍ እያለ እንዳረገ እንዲሁ ዝቅ ዝቅ እያለ ይመጣል ” ማለትም ዳግመኛ ተወልዶ ሳይሆን ወይም ቀድሞ የነሳውን ሥጋ ትቶ ሳይሆን በተዋህዶ በመለኮት ግርማ ይመጣል ብለዋቸዋል፡፡ (የሐዋርያት ስራ 1÷12)፡፡
.
ከዚም በኋላ ንስሐ ወይም ምግባር መስራት የለምና፣ ከዕለተ ምጽአት ይልቅ ዕለተ ሞታችንን ፣ አስበን ፣ ዛሬውኑ በሃይማኖት ጸንተን ምግባር ትሩፋት ሰርተን እንድንገኝ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
.
ወስብሀት ለእግዚአብሔር