በመጋቤ ምሥጢር ያሬድ መኮንን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና፤በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ
ነው፡፡

(መዝ 117፥25)

ጌታችን የሆሳዕና በዓል የምድርን ሁለንተና የዞረ በመሐል እጁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕጻናት ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው በማለት በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ሲሆን ስያሜውን ያገኘው በዕለቱ ከተዘመረው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር ነው፡፡ ሆሳዕና ማለትም እባክህ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ ይህ በዓል ለትንሣኤ አንድ ሳምንት ሲቀረው የሚከበረው የጌታ በዓል ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ሲሆን በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሐት ጸሎተ አስተስርዮ ስለማይፈጸም ጸሎተ ፍትሐትና አስተስርዮ የሚደረገው በዚሁ ዕለት ነው፡፡ ከአዳም ጀምሮ ከጽድቅ ድሆች ሆነው በኃጢአት ቀንበር ተይዘው በመንጸፈ ደይን በሲዖል ወድቀው በእግረ ዲያብሎስ ተረግጠው ይማቅቁ የነበሩ የሰው ልጆችን በቤዛነቱ ባዕለጸጋ ለማድረግ የመጣው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ በደረሰ ጊዜ በደብረ ዘይት አጠገብ ከቤተ ፋጌ ደረሰ ። ቤተ ፋጌ ማለት የድሆች መንደር ማለት ነውና ።

ከስድስት ቀን በኃላ በቀራንዮ አደባባይ መስቀል ላይ ሁኖ ዓለም ከኃጢአት ማሰሪያ የሚፈታ ጌታ በተመሳቀለ መንገድ ላይ ቁሞ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ከውርንጫዋ ጋር የታሰረችውን አህያ ፈትታችሁ አምጡልኝ! ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ አላቸው ። በመንደር የታሰሩትን የመረጠበት ምክንያት በሲዖል መንደር በወንበዴ ዲያብሎስ ተሰርቀው የሚማቅቁ አዳም እና ሔዋን ከነልጆቻቸው ከማዕሠረ ኃጢአት የሚፈቱበት ጊዜ መቅረቡን ለማጠየቅ ነው። ሁለቱን ደቀ መዛሙርት መላኩም ከኃጢአት ማሠሪያ ይፈቱ ዘንድ ካህናትን ወደ ዓለም መላኩን ያስረዳል ። በተጨማሪም አህያይቱ የእስራኤል ፣የሕገ ኦሪት ፤ውርንጫዋ የአህዛብ ፣የሕገ ወንጌል ምሳሌዎች ናቸው።

አህያይቱን እና ውርንጫዋን ፈትተው ካመጡለት በኋላ በቸርነቱ ብዛት ኃጢአታችንን የሚሰውር የማትቆረቁር ፍጻሜዋ ፍቅር የሆነ ሕገ ወንጌልን የሠራ ነውና የሚቆረቁረውን ኮርቻ ትተው ልብሳቸውን በአህዮች ላይ ጫኑ በእነርሱም ላይ ተቀመጠባቸው። ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባም እንኳን አንተ የተቀመጥክባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ እኩሌቶቹ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ ሲያነጥፉ ግማሾቹ የዘንባባ የወይራ ቅጠል እየቆረጡ ያነጥፉ ነበር ። ይህንም ማድረጋቸውም ዘንባባ እሾኻም መሆኑ የኃያልነት የአሸናፊነት የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫ ሆኖ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ይኸውም ሣራ የወላድነት ዕድሜዋን ጨርሳ ልማደ አንስት ከተቋረጠባት በኋላ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ የጎበኛትን አምላክ አመስግነዋል፡፡ እስራኤል ከአስከፊው የግብጻውያን አገዛዝ ተላቀው ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ሲሻገሩ የተሰማቸውን እጥፍ ድርብ ደስታ በገለጡ ጊዜ፣ እንዲሁም ዮዲት የተባለች ንግሥተ እስራኤል ሆሎፎርኒስ የተባለ አላዊ ንጉሥን ድል ባደረገች ጊዜ ቤተ እስራኤል እንደ ሰንደቅ ዓለማ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ አደባባይ ወጥተው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በዘመነ ሐዲስም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከሲዖል ባርነት ነጻ ለማውጣት ወደ ዙፋን መስቀሉ (ሉቃ.22፤18) በተጓዘ ጊዜ ሕጻናት እና አእሩግ ነጻ የሚወጡበት ቀን መድረሱን እነርሱ ሳያውቁ እግዚአብሔር ባወቀ ዘንባባ በመያዝ ዘምረዋል፡፡ እስራኤል ዘንባባ በመያዝ እንዳመሰገኑት እኛም አስራኤል ዘነፍስ ዕለቱን ዘንባባ /ጸበርት/ በግንባራችን በማሰር በዓሉን በየዓመቱ እያስታወስን እናከብራለን፡፡ በዚህ ዕለት ዘንባባ እየተባረከ ለሕዝቡ ይታደላል፡፡ ሕጻናትና አእሩግ ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል፡ እያሉ ዘምረዋል፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲሆን በሌላ በኩል የነበረው አቀባበል ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ሥርዓተ ኦሪትን፣ ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከተላለን ይሉ የነበሩ ጸሐፍት ፈሪሳውያን መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህን ገስጻቸው አሉት፡፡ ጌታችንም መልሶ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ  ሲል መልሶላቸዋል፡፡ ቅናት አቅላቸውን ያሳታቸው ፈሪሳውያንም የዋህ የሆነው ሕዝብ ምስጋና ወደ ጥላቻ እንዲለወጥ አድርገዋል፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው በዕለተ ሆሳዕና እሑድ ዘንባባ ይዘው የዘመሩለትን ጌታ ዓርብ ይሰቀል ዘንድ ይገባል ብለዋል፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ በነቢዩ ዘካርያስ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል (ዘካ.9፡9) ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲሆንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታም እውነተኛ የኅሊና ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲለን በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ሕይወታችን ተጉዟል፡፡ በሌላ በኩልም በአህያ ጀርባ መቀመጡ በአህያ ጀርባ የተቀመጠ ሰው ሌላውን አሳድዶ አይዝም፣ እርሱም ሮጦ አያመልጥም፡፡ በዚህም ጌታችን በእምነት ለሚፈልጉት የሚገኝ ቅርብ ሲሆን በእምነት ለማይፈልጉት ግን የማይገኝ መሆኑን አስተምሯል፡፡የአህያን ጀርባ ያልናቀ ጌታችን ትሑት ሰብእና እና የተሰበረ ልቡና ወዳለው ሰው ዘወትር ይጓዛል፣ የተዋረደውንና የተሰበረውን ልብ አይንቅም፡፡ (ኢሳ.66፡2)፤ ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ ሰው የሆነ ጌታችን ከማሰሪያዋ በተፈታች አህያ እንደተቀመጠ ሁሉ ከኃጢአት እስራት በተፈታ ሕይወት ዛሬም ያድራልና የኅሊና ሰላምን ለማግኘት ንስሐ ገብተን ጌታችንን ሆሳዕና በአርያም እያልን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ ሁላችንንም ከታሰርንበት የኃጢአት ማሠሪያ ይፍታን፡፡ አሜን፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።