የካናዳ ማእከል አባላት ዕለተ አኮቴት/የምስጋና ቀን/ መርሐ ግብር አከናወኑ፡፡

የማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን አባላት በሀገርና ከሀገር ውጭ ያሉ አባላት (በአንድነት) በመሆን አባላትን በአንድነት በመንፈሳዊ አገልግሎት እንዲነቃቁ ለማድረግና ለነበሩ አገልግሎቶች በአንድነት እግዚአብሔርን በማመስገን ወደፊትም ለምናከናውናቸው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች እግዚአብሔር እንዲረዳን በጸሎት የምንጠይቅበት መርሐ ግብር ነው፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን በውጭ ካሉ 7 ማእከላት ውስጥ አንዱ ካናዳ ማእከል እግዚአብሔር ለዓለም ሁሉ ሰላሙን እንዲሰጠን በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት መከራ ያወጣት ዘንድ፤ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያለባትን ፈተና ያስወግድላት ዘንድ፤ብሎም ማኅበረ ቅዱሳን ሠላሳ ሁለት የአገልግሎት ዓመታት እግዚአብሔር ረድቶት ስላከናወናቸው አገልግሎቶቹ እግዚአብሔርን ለማመስገንና በፈተና ውስጥም እግዚአብሔር መንገድ አለውና የወደፊት አገልግሎታችንን እግዚአብሔር እንዲረዳን በጸሎት ለመጠየቅ በአንድ አካባቢ ያሉ አባላት በአጥቢያ ተሰብስበው ፣በተለያየ ከተማ ያሉ አባላት ደግሞ ባሉበት ሆነው በ zoom Meeting ቅዳሜ ሚያዝያ 19, 2016 ዓ.ም. ዕለተ አኮቴት መርሐ ግብርን አከናውነዋል፡፡

የተከናወኑ መርሐ ግብራትም ጸሎት (ጸሎተ ነቢያት፣መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን፣የሰባቱ ቀናት ውዳሴ ማርያም፣አንቀጸ ብርሃን፣ይዌድስዋ መላእክት ፣መስተብቁዕ፣ምስባክ ተሰብኮ ጸሎተ ወንጌል ፣ኪዳን) ተደርጎ መዝሙር በጉባኤው ቀርቦ፣ትምህርተ ወንጌል (ስለመንፈሳዊና ስለኅብረት አገልግሎትና)፣ የበገና መዝሙር በተጋባዥ እንግዶች የበገና ዝማሬ ቀርቧል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ካናዳ ማእከል ሰብሳቢ ዶ/ር ደረጀ አሸብር በመልእክት መግቢያቸው እንደገለጹት የማኅበረ ቅዱሳንን መልእክት አስተላልፍላችኋለሁ በማለት “መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፡፡” (፪ኛ ጴጥ. ፩÷ ፲) በሚል ርዕስ ጀምረው ለተሳታፊዎች የማኅበረ ቅዱሳንን መልእክት አስተላልፈዋል፤በመልእክቱ መጨረሻ ላይም አባላትና ተጋባዥ እንግዶች በጸሎትና በአገልግሎት ተግተን በፍቅርና በአንድነት ተባብረን ከነበረን አገልግሎት የበለጠ በመሥራት የቤተ ክርስቲያንን ችግር ለመቅረፍ ሁላችንም በቁርጠኝነት እንድንዘጋጅ በማለት መልእክታቸውን በአጽንዖት አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም በተለያየ ቦታ ሆነው የተሳተፉ አባላት በአቅራቢያቸው ወደ አለ ቤተ ክርስቲያን ሄደው በኪዳንና በቅዳሴ እንዲሳተፉና እዛው ቤተ ክርስቲያን ሆነው በኅብረት በጉባኤው የገቡትም በጋራ እንዲያስቀድሱና የቻሉ ከምስጢራት እንዲሳተፉ ከዚያም አጋፔ በማድረግ ስለመንፈሳዊ አገልግሎትና ስለ ማኅበራቸው ቀጣይ ሥራዎች እንዲወያዩ መልእክት ተላልፎና በ zoom Meeting የነበሩ የጸሎት፣የትምህርት፣የመዝሙርና የመልእክት መርሐ ግብራት ተጠናቀው ጉባኤው በአባቶች ጸሎት ተፈጽሟል፡፡