“ዘወረደ” – የልዑል እግዚአብሔር ትሕትና

ዲያቆን ሚክያስ አስረስ

ስለ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ልዕልና ብዙ ጊዜ በመምህራን ሲነገር እንሰማለን፡፡ እውነት ነው፤ ልዑል እግዚአብሔር የክብሩ ገናናነት እንዲህ ነው ተብሎ ከመታሰብ በላይ ነው፡፡ እርሱን ገናናነት የሰው ኅሊናም የመላእክትም አእምሮ ሲያስበው አይጀምረውም፡፡ እግዚአብሔር በቸርነቱ ብዛት ራሱን ለመረጣቸው ቅዱሳን በተለያዩ አምሳላት ሲገልጥ እንኳ ግርማው ያስፈራል፡፡ ቅዱሳን ሲያስቡት “ዕጹብ” እያሉ ይደነቁበታል፡፡ የልዑል እግዚአብሔር ገናናነቱ ከሰው አሳብ፤ መረዳት እና ቋንቋ በላይ እንደሆነ እንዲሁ፤ ይኸው አምላክ በትሕትናውም እጅግ የሚደነቅ ነው፡፡ እንደ እርሱ ትሑት የሆነ ማንም የለም፡፡ ምዕመናን እርሱን መስለው ትሑታን ቢሆኑ በጸጋ መንግሥቱን እንደሚሰጣቸው በሐዋርያት ያስነገረው አምላክ ትሕትናው ረቂቅ ነው፡፡ ስለ ልዕልናው ለማሰብ መጀመር እንደማይቻል እንዲሁ ትሕትናውም ከፍጡር ሕሊና በላይ ነው፡፡ ቀድሞ ራሱን ለፈጠረው ዓለም ሲገልጥ፤ ራሱን ፍጡር ሊረዳው በሚችል መልኩ ው ፍጡር መረዳት ራሱን ዝቅ በማድረጉ ትሕትናው ታወቀ፡፡ ለአባቶቻችን መገለጡንና ቅዱሳት መጻሕፍት ማጻፉ የዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ልዑል እና ረቂቅ ሆኖ ሳለ በሰው ቋንቋ ይገለጽ (ይነገርለት) ዘንድ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡ ኋላም ሰውን ለማዳን ባደረገው ሥጋዌ (ሰው በመሆኑ) ትሕትናው ፍጹም ተገለጠ፡፡ የማይታየው አምላክ የሚታይ ሥጋን ከእመቤታችን ነሥቶ ተዋሕዷልና፡፡

ከዐቢይ ጾም ሳምንታት የመጀመሪያ የሆነው “ዘወረደ” ዋናው መልእክቱ አምላክ ከሰማያት መውረዱን (ሰው መሆኑን) ማስታወስና ማስተማር፤ ትሕትናውንም ማሳሰብ ነው፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮት ላይ የሚነበቡ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች የእግዚአብሔር ልጅ ከሰማይ መውረዱን፤ ወደ ሰማያትም ለማረግ ብቸኛ ሥልጣን ያለው እርሱ መሆን የሚናገሩ ናቸው፡፡ በእርሱ ያመኑ ምዕመናን ወደ ሰማይ ከፍ ቢሉ በእርሱ ኀይል እንጂ በራሳቸው ሥልጣን አይደለምና፡፡ በቅዱስ ወንጌል “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” (ዮሐ 3፡ 13) በማለት መድኅን ክርስቶስ የተናገረው በዘወረደ ሳምንት የምንሰማው የወንጌል ክፍል ነው፡፡ ለከፍታው መጠን የሌለው አምላክ ዝቅ ማለትን አሳየ፡፡ ከዚህም ሌላ በምድር ላይ ተመላልሶ ማስተማሩ፤ የደቀ መዛሙርቱን እግሮች ዝቅ ብሎ ማጠቡ፤ ከምንም በላይ ደግሞ በፈቃዱ ስለ ሰው ልጅ ሕማማትን እና ሞትን መቀበሉ ሁሉ የትሕትናው ማሳያዎች ናቸው፡፡ እርሱ ዝቅ ብሎ ራሱን ሲገልጥ እርሱን በትሕትና የመሰሉ ደቀ መዛሙርት አሉ፡፡ ከእመቤታችን ጀምሮ ሐዋርያቱ ሁሉ ለዚህ ምሳሌ ናቸው፡፡ እመቤታችን በጸሎቷ “አዕበዮሙ ለትሑታን፤ ትሑታንን ከፍ ከፍ አደረጋቸው” (ሉቃ 1፡ 52) ብላ የጸለየችው ስለ ደቀ መዛሙርቱ ነውና፡፡ እርሱን ዐይተው በትሕትና መገለጡን ያስተዋሉት፤ በትሕትና የመሰሉት ናቸው፡፡ በተቃራኒው የእርሱን በትሕትና መገለጡን ያላስተዋሉ፤ እርሱ ስለ እውነት ሲናገር ራሱን ከፍ ማድረጉ እንደሆነ አድርገው ያሰቡት አድሞ በሐሰት ከሰውት የሰቀሉት ናቸው፡፡ ከላይ የወረደውን በዓመጽ ሰቀሉት፡፡ “ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ፤ ከላይ (ከሰማይ) ወረደውን አይሁድ ሰቀሉት” (ጾመ ድጓ ዘዘወረደ) የሚለው የቅዱስ ያሬድ ቃል የእግዚአብሔርን ቸርነት እና የሰው በደል ምን ያህል እንደሚራራቅ የሚያመለክት ነው፡፡ አይሁድ የሚሰቅሉት እንደሚሆነ የሚያውቅ እግዚአብሔር በትሕትና ሰው ከመሆን ራሱን አልከለከለም፡፡ የሰውን መዳኑን የሚወድ አምላክ ነውና፡፡

አሁንም ሰው የእግዚአብሔርን ትሕትናውን ቢያስተውል፤ እርሱንም እመሰለ ቢኖር የማይጠፋ ሕይወትን ያገኛል፡፡ በበደልና በክህደት የሚኖር ግን ክርስቶስን ሳይሆን ሰቃዮቹን የሚመስል ነውና ከሕይወት መንገድ ይወጣል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ኀጢአትና በደልን ማድረግ የእግዚአብሔርን ልጅ ዳግም መስቀል እንደሆነ አስተምሯል (ዕብ 6፡ 6)፡፡ በመሆኑም ለእግዚአብሔር የምንገዛበት ጾም በፍጹም ደስታ ልንቀበለው ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ጥበቡን ይገልጥልን ዘንድ፤ እውነተኛ ሰላምና ፍቅርንም ያድለን ዘንድ ጾሙን ከመብል ይልቅ በንስሐ ልንቀበለው ይገባናል፡፡ በቸርነቱ ትሑታን የምንሆንበትን ማስተዋል ያድለን ዘንድ፤ በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ዘወትር ትሑት ወደ ሆነው አምላክ እናድግ ዘንድ፡፡ በእውነት ጾመው መንፈሳዊ ጥቅምን ተጠቀሙ የቅዱሳንን በረከታቸውን ያድለን፡፡ አሜን፡፡