“እኔ ነኝ በአንተ ልጠመቅ የሚገባኝ እንጂ አንተ እንዴት ወደ እኔ ትመጣለህ?” ማቴ. 3፥14-15

ቅዱስ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ አይሁዳውያንን ሲያጠምቅ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተራ ሰው መስሎ መጣ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ገርሞት “እኔ ነኝ በአንተ ልጠመቅ የሚገባኝ እንጂ አንተ እንዴት ወደ እኔ ትመጣለህ?” ማቴ. 3፥14-15 በማለት ማጥመቁን እምቢ አለ፡፡ ኢየሱስ ግን “አሁንስ ተው አትከልክለኝ የምጠይቅህን ጥምቀት ስጠኝ፡፡ ምክንያቱም ሕግን ሁሉ መፈጸም  ተገቢ ነው፡፡” ሲለው የጥምቀት ውኃ በራሱ አፈሰሰበት፡፡ ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወደያው በራሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፡፡ ሰማይም ተከፈተ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ማቴ. 3፥17 የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣ፡፡ ኢየሱስ የተጠመቀው ግዳጅ ስለነበረበት አይደለም፡፡ ሕግን ሁሉ መፈጸም እንዳለበት በተለይ ደግሞ ምስጢረ ጥምቀት ለደኀንነታችን የግድ አስፈላጊ መሆኑን ሊያስተምር ፈልጐ ነው፡፡ ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ እንደገና ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይችልም” ዮሐንስ 3፡5 ሲል ተናገረው እንዲሁም “ወደ ዓለም ሙሉ ሄዳችሁ ወንጌልን ለሕዝብ ሁሉ ስበኩ በአብ፣ በወለድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው፡፡ ያመነና የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል” ማር. 16፡16

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ከዮርዳኖስ ወንዝ ሳይወጣ እዚያው ቆሞ እያለ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ወረደ፡፡ “በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው” እያለ እግዚአብሔር አብ ተናገረ፡፡ ይህ ጥምቀት በሚቀበል በእያንዳንዱ ሰው ይደገማል፡፡ እኛ ጥምቀትን ስንቀበል መንፈስ ቅዱስ በማይታይ ሁኔታ በእኛ ላይ ይወርዳል፡፡ እግዚአብሔር ያን ጊዜ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” እያለ ተሰስቶ ይቀበለናል የላቀና የጠለቀ ደስታውን ይገልጣል፣ የእግዚአብሔር ልጆችና የመንግሥተ ሰማያት መራሾች ያደርገናል፣ በጥምቀት ጸጋ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከባርነት ወደ ነጻነትና ጽድቅ እንሻገራለን፣ የቅድስት ሥላሴ ማደሪያና ምድራዊ መኖሪያ እንሆናለን፡፡ ጥምቀት ስንት መንፈሳዊ ሀብትና ጸጋ እንደሁም ከፍ ያለ የእግዚአብሔር ልጆች ክብር ይሰጠናል፡፡ እኛም  ከማኅፀነ ዮርዳኖስ  ከአብራከ  መንፈስ  ቅዱስ ስለተወለድን ነው የቅድስት ሥላሴ ልጆች የሆነው::

ግን ምድራዊ ሀብት ጠንቀቅ ብለን ካልጠበቅነው ሊጠፋና ሳንጠቀምበት ሊቀር እንደሚችል እንዲሁም የጥምቀት መንፈሳዊ ሀብት ተግተንና ነቅተን ካልሰራንበት ጥቅም ሳይሰጠን ባክኖ ሊቀር ይችላል፡፡ ጥምቀት ስለተቀበልን ድነናል ብቁዎችም ሆነናል መንግሥተ ሰማያትን ወርሰናል ማለት አይደለም፡፡ ደኀንነታችን ፍጹም እንዲሆን መንግሥተ ሰማያት እንድንገባ በበኩላችን በደካማ አቅማችን በሚፈቅደው ያላሰለሰ ጥረትና ትግል ማድረግ አለብን፣ የደኀንነታችን መሠረት ልንቀጥለውና መልካም ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ ልናሳድገው እንዲሁም ግራና ቀኝ ሳንል በደኀንነት ጐዳና እንድንጓዝ ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ አንድ ጊዜ ጥምቀት ተቀብለናል፣ ተጠምቀናል ይበቃናል፣ አሁንስ ለዘለዓለም ድነናል ብለን ከመንፈሳዊ ጥረት ውጊያ ተግባር ማረፍና ማቋረጥ አይገባንም፡፡ በጥምቀት ጸጋ ተመርተን እንድንሄድና ኑሮአችን ከሕይወታችን አረማማድ ከመንፈስ ጥምቀት እንዲስማማ ማድረግ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ “እምነት ያለሥራ የሞተ ነው” ያዕቆብ 2፥26 እያለ ያስጠነቅቀናል፡፡

ቤተክርስቲያን ስንጠመቅ “በዘለዓለም ሕይወት ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ ከፈለግህ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ጠብቅ፣ እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ ውደድ፣ ባለንጀራህንም እንደራስህ አድርገህ ውደድ፤ ሰይጣንና ሥራውን ሁሉ ካድ በኢየሱስ እመን” እያለች ታስጠነቅቀናለች፡፡ እኛም ደግሞ እክዳለሁ … አምናለሁ …” እያልን እንመልስላታለን፡፡ እንግዲህ ቃላችንን እንጠብቅ መሐላችንንና እምነታችንን ፍሬ አፍርተን በተግባር እናሳይ፡፡ ያን የጥምቀት ጸጋ በበለጠ ጥረት ኰትኩተን እናዳብር፡፡

መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንልን፡፡ አሜን ።