“ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” ኢሳ 7÷14

++ ፈኑ እዴከ እምአርያም
አድኅነኒ ወባልሐኒ እማይ ብዙኅ
ወእምእዴሆሙ ለደቂቀ ነኪር መዝ ፻፵፫፥፯ ++

ትርጉም፦

እጅህን ከአርያም ላክ
ከብዙ ውኃም አድነኝ
ከባዕድ ልጆችም አድነኝ

ምሥጢር፦

ረድኤትህን ከአርያም ላክ አንድም ልጅህን በሥጋ ላክ ከብዙ ጦር/ሠራዊት አድነኝ አንድም ከፍትወታት እኩያት ከኃጣውእ ርኩሳት ከፍዳ ከመከራ ነፍስ ፈጽመህ አድነኝ ከነናምሩድ ከነሳኦል ልጆች እጅ አድነኝ አንድም ከዲያብሎስ ወገኖች ሥልጣን አድነኝ:: እጅ/ክንድ ከአካል ሳይለይ የወደቀ እንደሚያነሣ፤ የራቀ እንደሚያቀርብ፤ የቀረበ እንደሚያርቅ፤ የተበተነ እንደሚሰበስብ የወደቀ አዳምን አንሥቷል የራቀ አዳምን አቅርቧል የተበተነውን መንጋ ሰብስቧልና እጅህን ላክልን እያለ ዳዊት የተማኅፅኖ ጸሎት አቀረበ።


አንድም የሰው ኃይሉ በክንዱ እንዲታወቅ የአብም ኃይሉ በወልድ ታውቋልና እጅህን ላክ አለ።
አንድም ኃጥአንን ሑሩ እምኔየ ብሎ ያርቅበታልና ጻድቃንን ንዑ ኀቤየ ብሎ ያቀርብበታልና ፈኑ እዴከ አለ።

መጣ ስንልም የሌለበት ስፍራ ኖሮ ወዳልነበረበት ዓለም ወይም ቦታ መጣ ማለታችን አይደለም። ሁሉ በመሐል እጁ የተያዘ ነውና የሌለበት ስፍራ የለምና ካለበት ዓለም ወዳለበት ዓለም መጣ እንላለን።

በዘመናችን ካሉ ሊቃውንት አንዱ ሊቅ እንዲህ ብለዋል
“ሰው በያዘው ነገር ላይ መቀመጥ አይችልም በያዘው ዓለም ላይ መቀመጥ የታቸለው እግዚአብሔር ብቻ ነው” ሰማይ ዙፋኑ ምድር የእግሩ መረገጫ ሲሆኑ ተወስኖ ታይቷልና።

ምሥጢሩ የዚህን ያህል ጥልቅና ረቂቅ ከሆነ በምሥጢረ ሥጋዌ ዙሪያ አምላክ እንዴት ሰው እንደሆነ ሰውም እንዴት አምላክ እንደሆነ ተመራምሬ እደርሳለሁ ማለት የውቅያኖስን ውኃ በእንቁላል ቅርፊት ቀድቶ ለመጨረስ እንደመሞከር ነው።

የዕለቱ ወንጌል፦ ዮሐ ፩፥፵፬ – ፍጻሜ

ቅዳሴ፦  ዘእግዚእነ

ከወንጌሉ ንባብ በጥቂቱ፦

የቅዱስ ፊልጶስ ጥሪና ምስክርነቱ ጌታችን ፊልጶስን ተከለኝ ብሎ ካስከተለው በኋላ ያለመዘግየት ስለተከተለው ወይም እንዲከተለው ስለፈቀደለት አምላክ ለመመስከርና ሌሎችን እሱ ወደተጠራበት ለመጥራት ጊዜ አላባከነም። ሙሴ በኦሪት ነቢያትም በትንቢት መጽሐፍ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘው ብሎ ለናትናኤል ምስክርነቱን በመስጠት ወደዚህ ሕይወት እንዲመጣ ጠርቶታል።
እዚህ ላይ የዮሴፍ ልጅ የሚለው ኃይለ ቃል በትርጓሜያችን የተቃና መሆኑን ልብ ይሏል። አይሁድ ባለማወቅ የዮሴፍ ልጅ የሚሉት፤ ሙሴ በኦሪቱ የጻፈለት፤ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት፤ እኛም አምላክ ወልደ አምላክ ብለን የምናምንበት የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘው ብሎ ለናትናኤል እንደመሰከረለት ተብራርቷል። ዮሴፍ ስንኳን በገቢር በሐልዮ ይህን ነጥብ አያውቀውም። ይህም በመልአኩ ቃል ተረጋግጧል። “ይህ ሁሉ የሆነው ከእግዚአብሔር ዘንድ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው” በማለት ዮሴፍ የተጨነቀበትን ሐሳብ ሲያርቅለት እናያለን። ማቴ ፩፥፳፤


በነቢይ የተነገረውም “ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” የሚለው ነው።
የሚሰመርበት ነጥብ፦ “ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች” የሚለው ነው። ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቀር በድንግልና የፀነሰች ፈጽማ የለችም አትኖርምም። ይህም ከሆነ ዮሴፍ አባት የተባለው ወይም ሊባል የቻለው አሳዳጊ በመሆኑ ብቻ እንደሆነ ንጹሕ ሕሊና ያለው ሰው የሚረዳው እውነት ነው። ስለ ዮሴፍ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ጻድቅ ስለሆነ” በማለት ነው። ጻድቅ ከሆነ ደግሞ የእግዚአብሔርን ሥራ አይዳፈርም አይጋፋምም። በረድኤት የተገለጠባትን ደብረ ሲና እንኳ ማንም ሊነካት አልደፈረም። በኩነተ ሥጋ የተገለጠባትን አማናዊቷን ቤተ መቅደስ ጻድቅ ተብሎ የተገለጠው ዮሴፍ እንዴት ሊዳፈር ይችላል? ቴዎዶጦስ የተባለ ሊቅ ነገረ ሥጋዌን በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል። “ወህየንተ እድ ዘዝየ ዘይለክዖ ለቃል በጽሒፍ አእምር በህየ ከመ እግዝእትነ ድንግል ማርያም ይእቲ ዘወለደቶ ለቃል በሥጋ” ብሏል። ወደአማርኛ ሲመለስም “በጽሕፈት ጊዜ ቃልን ስለሚጽፈው እዚህ ስላለ እጅ ፈንታ በወዲህ ቃልን በሥጋ የወለደችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሆነች እወቅ” ማለት ነው። ሃይ አበው ፶፫፥፳
ሊቁ ይህን የተናገረበት ምክንያት፦
ከልብ የተገኘ ቃልን ለመጻፍ ብንፈልግ በልባችን ያለውን ቃል በሠሌዳ ስንቀርፀው ቃል አካላዊ በመሆን ይገለጣል። ይሁን እንጂ በጽሑፍ የተገለጠው ቃል በጽሑፍ ከመገለጡ በፊት በልብ ህልው እንደነበረ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ ማርያም ከመገለጡ በፊት በአብ ህልው እንደነበረ ማስረጃ ነው። የአምላካችን ልደት በእንዲህ ዓይነት ምሥጢር የተከናወነ መሆኑን ብርዕና ቀለም ሆና ያላየነውን እግዚአብሔርን እንድናየው ያደረገችን እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት ሲል ሊቁ ቴዎዶጦስ በምሳሌ አስተማረን።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ፦
“አንተሰ ኦ ብእሲ ኢታስተንዕስ መጠና ለሃይማኖት ቅድመ አዕይንቲከ – አንተ ሰው የሃይማኖትን መጠን በልቡናህ አታሳንስ አንድም አዋርደህ አትያት” ብሏል። ድር. ዘዮሐ አፈ ወርቅ ፱፥፺፭

ለእኛ ያልተረዳን ሁሉ ስሕተት፤ እኛ ልክ ነው ያልነው ሁሉ እውነት ሊሆን አይችልም። የእኛን ስሜት ብቻ ተከትለን በሄድን መጠን የሃይማኖታችንን ምሥጢር እያሳነስነው ልንሄድ እንችላለንና።