አዲስ ዓመት – ሐዲስ ሕይወት

ጳጉሜን ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

እንኳን ለዘመነ ማርቆስ አደረሰን!

ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ወቅቶችን ያፈራርቃል፤ ዝናብን ያዘንባል፤ ፀሐይን ያወጣል፡፡ ይህን ማድረጉ ለሰው ሁሉ ነው እንጂ በእርሱ ለሚያምኑ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ግን ለሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር የተሰጠ (የሚሰጥ) መክሊት ነው፡፡ የጊዜያዊውን ፀሐይ መውጣት፤ ዝናቡን መዝነብ ተመልክቶ ዘለዓለማዊ የምትሆን የጽድቅ ፀሐይ እንድትወጣለት፤ አምላካዊት የምትሆን የምሕረቱ ዝናብም በሕይወቱ እንድዘንምለት በእውነት የሚናፍቅና ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው በተሰጡት መክሊቶች ያተረፈ ሰው ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ዕድሜ ተሰጥቶት፤ የወቅቶች መፈራረቅ፤ የፀሐይ መውጣትና የዝናማት መዝነምን እንደ ሕይወቱ የመጨረሻ ግብ አድርጎ በምድር ላይ የሚኖር፤ ማለትም በዚህ ጊዜያዊ ዓለም የተዋጠ ሰው እግዚአብሔርን አያስብም፤ ጽድቁንም በእርሱም የሚገኘውን ሐዲስ ሕይወት አይናፍቅም፡፡ ይህ ደግሞ ከሕይወት መስመር መውጣት ነው፡፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ የሕይወትን አዲስነት ካልያዝንበት አዲሱ ዓመት ጥቅሙ ምንድነው? ለዚህም ነው ከኀጢአት ዕርጅና ወጥተን አዲስ የምንሆንበትን ንስሐን ያስተማረንን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ማሰባችን፡፡ ሰው ለንስሐ የሚገባ ፍሬ የማያደርግ ከሆነ ዓመቱ ብቻውን እንዴት አዲስ ይሆናል? 

ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆኑ ምክንያት ለሰው የጠፋበትን ሰውነት (ሰው መሆንን) ዳግም ለመስጠት ነው፡፡ ሐዲስ ሕይወትን ጸጋ አድርጎ ለመስጠት መድኅን ክርስቶስ በሥጋ ወደ እኛ መጣ፡፡ መጥቶም የመጀመሪያው ትምህርቱ ያደረገው ንስሐን ነው፡፡ ያለ ንስሐ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አይቻልምና፡፡ የሕይወት ባለቤት የሆነ እግዚአብሔር አዲስ ሕይወትን የሚሰጥ ወደ እርሱ በንስሐ ለቀረቡት ነውና፡፡ ይልቁንስ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር በመተው አዲሱን ሰው (ክርስቶስን) በሃይማኖትና በምግባር ለሚለብሱት አዲስ ሕይወት ጸጋ ሆና ትሰጣዋለች (ቆላ. 3፥9)፡፡ አዲስ ዓመትን ስንታደል በሐዲስ ሕይወት ለመመላለስ መፈለግና መናፈቅ አለብን፡፡ በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር ከተቀበርን ከክርስቶስ ጋር በሐዲስ ሕይወት እንደምንኖር ዳግመኛ ይህ የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ያስተምረናል (ሮሜ 6፥4)፡፡

ዛሬ አዲስ ዓመት አድርገን የምናከብራት ቀን፤ በብሉይ ኪዳን የተቀደሰች ቀን መሆኗ የተነገረላት፤ እስራኤል መሥዋዕትን የሚያቀርቡባት፤ መለከት የሚነፋባት የተባረከች ቀን ናት፡፡ እስረኤል ይህችን ቀን ያከብሩ ዘንድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታዘዋል (ዘሌ 23፡ 24-25፤ ዘኁ 29፡ 1-2)፡፡ የምስጋና ዝማሬዎችም በዚህች ቀን ይቀርቡባታል፡፡

ለእኛ ለክርቲያኖችም ይህ ቀን እውነተኛውን ምስጋና የምናቀርብበት ዕለት ነው፡፡ ዘመናት የሚሰጡን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ሆነን እንድንኖርባቸው በመሆኑ አዲስ ዓመትን ስንታደል የምናተርፍበትን መክሊት የታደልን አድርገን መረዳት ይገባናል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብም መሠረታዊው ጉዳይ ንስሐን መያዝ ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ እንደሚስተምረን የንስሐን ፍሬ ማድረግ ይገባናል፡፡ ለአይሁድ አብርሃም አባት አለን ብላችሁ እንደምትሉት አይደለም ብሎ አስተምሮ ነበር፡፡ ዛሬም እኛ ተጠምቀናል፤ ኦርቶዶክሳውያን ነን ማለታችን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ፍቅርን ይዘን በንስሐ ወደ መድኅን ክርስቶስ ብንቀርብ ሕይወታችን በጸጋ እና በጣዕም የተመላች ትሆናለች፡፡ አምላካችን በአዲሱ ዓመት ወደ ሐዲስ ሕይወት ያስገባን ዘንድ ቸርነቱን ያድርግልን፡፡ አሜን!