ገብር ኄር እና እኛ

 ተክለማርያም ( ኪችነር )

መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም.

.

“ገብር ኄር ” ወይም ቸር እና ታማኝ አገልጋይ የሚለው ቃል ለዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት መጠሪያ እንዲሆን በቅዱስ ያሬድ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡

  ስለ መክሊት ወይም የፀጋ ስጦታ በወንጌል ውስጥ ከተጠቀሱት ብዙ ትምህርቶች ከፍተኛውን ቦታ የሚይዘው በማቴዎስ 25፥14 ላይ የፃፈው የጌታችን የምሳሌ ትምህርት ነው : ይህም ትምህርት በአጭሩ ሲገለፅ  አምስት መክሊት ፥ ሁለት መክሊት እና አንድ መክሊት ከተቀበሉ አገልጋዮች መካከል ሁለቱ አገልጋዮች እንደተደተሰጣቸው መጠን ሰርተውና አትርፈው ለጌታችው ሲያስረክቡ አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ግን በተሰጠው መክሊት ልክ በአቅሙ ሰርቶ አትርፎ ለጌታው ማስረከብ ሲገባው  ይህን አላደረገም ይልቅስ ይባስ ብሎ ላለመስራቱ እና ላለማትረፉ ምክንያት ተጠያቂ ያደረገው በቸርነቱ ብዛት በነፃ መክሊት የሰጠውን ቸሩ ጌታውን ነበርና እንዲህ አለ “ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ” ማቴ 25፥24-25

  ይህ ከላይ ያየነውን የመልካም እና የክፉ አገልጋዮች ምሳሌን ጌታችን በዚሁ ምዕራፍ ላይ በሌላ ምሳሌ ሲያስተምር  “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?” ማቴ24፥45 በማለት ከጠየቀ በኃላ ሹመቱን ( መክሊቱን ) ያለአግባብ ተጠቅሞ ከእርሱ በታች የነበሩትን አገልጋዮች ሲያሰቃይ የነበረውን ክፉ ባርያ ( አገልጋይ ) የዘላለም ቅጣት እንደተገባው ነግሮናል::

    የሰነፍ አገልጋይ ትልቁ ድካሙ የተሰጠውን መክሊት አትርፎ አለማስረከቡ ብቻ ሳይሆን ለድካሙ እና ለስንፍናው ሌሎችን ተጠያቂ ማድረጉ ነው:: ደካሞችን ከማገዝ ይልቅ ሰራተኞችን በመንቀፍ ግዜውን ያባክናል ፥ የራሱን ኃጥያት እያሰበ ከማልቀስ ይልቅ በሌሎች ኃጥያት ይሳለቃል: ይህ ሰነፍ አገልጋይ የስንፍናው ጥግ ልክ የሌለው ነውና ጌታውንጨካኝበማለት ወደ መጥራት ደርሷል:: ቸር እና ታማኝ አገልጋይ ግን እንዲህ አይደለም::

    ገብር ኄር ( መልካም አገልጋይ ) የአገልግሎቱ መሠረት ክርስቶስ ነውና ስራውን በትህትና ጀምሮ በትህትና ይፈፅማል ፥ ለሰጠኸኝ መክሊት የምመጥን ሰው አይደለሁም በማለት የመክሊቱን እና የመክሊት ሰጪውን ክብር ከፍ ከፍ ያደርጋል: ዘወትር በፊቱ እግዚአብሔርን ያያልና ስለሌሎች ኃጥያት የሚያስብበት ግዜ የለውም: ይልቁንስ ስለኃጥያተኞች ድኅነት፥  ስለጠፉት በጎች መገኘት ፥ ስለ ወደቁት መነሳት ፥ ስለቆሰሉት መፈወስ ፥ ስለጠላቶቹም መመለስ ጭምር ለሊትና ቀን ያለማቋረጥ ይተጋል :: ግፈኞች ወይም ያልተረዱት ሰዎች ሲሰድቡት ሲያዋርዱት እና ሲጠሉት ይገኙ እንደሆን እንጂ እርሱ ሌሎችን ሲሰድብ ሲያዋርድ እና ሲጣላ አይገኝም:: ” የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም” 2ጢሞ 2፥24 – መልካም አገልጋይ በመከራ ሁሉ ይፀናል ፥ ሁሉን ይታገሳል ፥ ሁልግዜም ያለማቋረጥ ምግበ ነፍስ ከሆነው ከቃለ እግዚአብሔር ተለይቶ ስለማያውቅ በዚህ ዓለም ከንቱ ሃሳብ አይታለልም  ፥ ይልቁንስ የምትመጣዋን የእግዚአብሔርን መንግስት እያሰበ እስከ ሞት ድረስ የታመነ ሆኖ የተጠራለትን የአገልግሎት ሩጫ ይፈፅማል:: እንግዲያውስ በቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ አስተምህሮ እኛ ሁላችን ክርስቲያኖች በየመክሊታችን አገልጋዮች መሆናችንን በሚገባ በማወቅ ፥ እኛ ጋር ያለች ትንሽ የምትመስለን ማንኛውም ዓይነት ፀጋ ለሌላው መዳን እጅግ ወሳኝ እና ህይወት ቀያሪ ምዕራፍ ልትሆን እንደምትችል አምነን በትጋት ሆነን መንፈሳዊውን የአገልግሎት ሥራ እንድንሰራ ይገባናል:: ለዚሁም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኃይልና ብርታት ይሰጠን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን::

       ይትባረክ እግዚአብሔር

          አምላከ አበዊነ