ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም)

/ሊቀ ጠበብት ማኅቶት የሻው/

ኅዳር 17 ቀን 2015 ዓመተ ምሕረት

በየአመቱ ከኅዳር 15 ጀምሮ የምንጾመው ጾም: ጾመ ነቢያት ይባላል::  ነቢያት  ክርስቶስ  ይወርዳል  ይወለዳል  እያሉ ሲሰብኩ ፣ ሲተነብዩ፣ ዘመንን እና ጊዜን ወደፊትም ወደኋላም ሲመለከቱበት  የነበረው  ትልቁ መሣሪየቸው ጾም ነበር:: በተለይም የትንቢት መስታወታቸው ይህ ጾም እንደሆነ እናምናለን። ብዙዎች  ላለመጾም ሲፈልጉ ስንፍናቸውን ለመሸፈን“የቄስ ጾም ነው” በሚል የሚጠራ ሳይሆን  መባል ያለበት የክርስቲያን  ጾም ነው::  የኛ ነው ። ቅዱስ  ጳውሎስ  ኤፌ.2፥19 ላይ  እንዲህ  ብሏልና “በሐዋርያት እና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” :: ክርስቲያን  የተባለውን  የድኅነት  ስም ያገኘነው  አምለክ  ተወልዶ ክርሰቶስ  ከተባለ  በኋላ  ነው::  ለእኛ  ለደቂቀ አዳም ድኅነት ብለው የተነበዩት፣  የጻፉት፣ ያስተማሩት፣  የጾሙት፣ ነቢያት ናቸው።  እኛ   የተዋህዶ አማኞች  ነቢያትን እና ኦሪትን፣ ሐዲስን እና ሐዋርያትን የምንቀበል፣ የምናምን እና የምናስተምር:  በዚህ  ልዩ ሥርዓትም የምንሄድ እንደመሆናችን  መጠን፣ ከ7ቱ የዐዋጅ አጽዋማት አንዱ የሆነውን ይህን የነቢያትን ጾም የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል:: እያጉረመረሙ  የሚበሉት  ይንቃል፥  እያጉረመረሙ  የሚጾሙትም ጾም ለክፉ ፈተና አሳልፎ ይሰጣል:: ፈሪሳውያን  ተጎድተውበታል ። ሉቃ 18፥12

ነቢያት ጾመው ምን አገኙ?

የነቢያት  አለቃ  ታላቁ  ነቢይ  ሙሴን ስንመለከት: በሲና ተራራ 40 ቀን 40 ሌሊት በመጾሙ እሥራኤልን ከባርነት ነፃ አወጣቸው፣ ከጥፋትም ታደጋቸው:: ሙሴ በጾም ምክንያት  ለአምላክ  የቅርብ ወዳጅ በመሆኑ  ታላቅ  ክብርንና ሞገስን አጎናጽፎታል:: እግዚአብሔርም  የፍቅሩ መግለጫና  የጾሙን ዋጋ አክሊል ጽላት ሸልሞታል (ዘጸ. 32፥15፤34፥1) እድለኞች ሆነን ይህች የእግዚአብሔር  ማደሪያ  የሆነችው በእግዚአብሔር  ጣት አሠርቱ  ትእዛዛት የተጻፉባት  ጽላተ ሙሴ ዛሬ በሀገራችን ትገኛለች:: ከጾምን ከጸለይን ዛሬም ትረዳናለች። ቅዱስ ያሬድ  “ሃሌ ሃሌ  ሉያ በጾም ወበጸሎት ተመጠወ ሙሴ ኦሪተ ጽላተ አሥሮነ ቃላተ” ( የነበረ  ያለና የሚኖር እግዚአብሔር  ሙሴ በመጸለዩ እና በመጾሙ አሥሩ የኦሪትን ቃላት የጻፈበትን ጽላት ለሙሴ ሰጠው ) ወይንም ሙሴ ተቀበለ ብሏል:: ኢሳይያስም በበኩሉ በጾምና በተሰጠው ሀብተ ትንቢት እግዚአብሔርን እንደተወለደ አድርጎ አይቶታል:: አስቀድሞ እንደሚወለድ ከተነበየ በኋላ ወዲያውኑ ደግሞ ተወልዶ እንዳየው ሆኖ በእምነት  ማረጋገጫ  አስቀምጦልናል።

ትንቢቱ  (ት.ኢሳ. 7፥14  እነሆ ድንግል  ትጸንሳለች  ወንድ ልጅም ትወልዳለች  ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች) ( ት.ኢሳ.9፥6  ሕፃን  ተወልዶልናልና  ወንድ  ልጅም  ተሰቶናልና አለቅነትም  ከጫንቃው  ላይ ይሆናል:: ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም  አባት  የሰላም  አለቃ  ተብሎ ይጠራል  )

 አረጋዊ  ስምዖን _ ክርስቶስ  እንደሚወለድ  ከተነበዩት እና ከጻፉት አንዱ ነው:: በጾምና በጸሎት ተወስኖ የእስራኤልን መዳን የእግዚአብሔርን  የማዳን ትንቢት  ሲጠባበቅ የነበረ ሲሆን፣ ክርሰቶስ  ተወልዶ በዓይኑ አይቶ በቤተ መቅደስ ተገኝቶ አምላኩን ታቅፎ የጾሙን ዋጋ እድሜ ተጨምሮለት በእድሜ ታድሷል። ኢየሱስ ክርስቶስ  እራሱ አባቶቹ እና ልጆቹ የጾሙትን እሱም 40 ቀንና ሌሊት በመጾም አጋንንትን ድል ነስቷል:: ክፉ ፈተናን አርቆበታል

እኛም ዛሬ በጾም እና በልዩ ልዩ አገልግሎት  ከበረታን ጤንነትን፣ እድሜን፣  በረከትን፣  ሀብትንና  በጎ የተመኘነውን  እናገኛለን ።

በአጠቃላይ ጾም ለሥጋም  ለነፍስም ጥቅም አለው:: በሥጋ ከምንፈራቸው ልዩ ልዩ በሽታዎች የምንከላከልበት  ነው ፤ የሥጋ ፍትወትንም ለነፍስ ፍትወት የምናስገዛበት ነው::   እነ ኤልያስ በመጾማቸው ወደ ብሔረ ሕያዋን  ዓርገዋል ፤ ሠለስቱ  ደቂቅ ጣዖታትን አጥፍተዋል ፤ የነነዌ ሰዎች ከመቅሰፍት ድነዋል:: ከላይ በስፋት እንደተባለው  የጾም ውጤት እራስን መሆን ነው ፤ የጾም ውጤት አባቶቻችንን መምሰል ነው:: (ዕብ.13፥7) ፤ የጾም ውጤት እግዚአብሔርን  በቅርብ ማግኘት ነው:: እንደአባቶቻችን ጾመን የአባቶቻችንን በረከት ለመቀበል ያብቃን ።

ወስብሐት  ለእግዚአብሔር!