“ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፡፡” መዝ 59÷4

“ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፡፡” መዝ 59÷4


✞  እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ✞

እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ በአርአያውና በምሳሌው አክብሮ የፈጠረው ፍጥረት ሰው ነው፡፡ ነገር ግን “ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ እንደ አላዋቂ ሆነ” ብሎ ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረው (መዝ 48 ÷12) ሰው ነጻነቱንና ታላቅነቱን ባለማወቁ ትዕዛዘ እግዚአብሔርን ጥሶ ሕጉን በማፍረሱ የሞት ሞት አገኘው፡፡ ኋላም እግዚአብሔር ሰውን ከሞት ያድነው ዘንድ እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኖ በዮርዳኖስ ተጠምቆ በቀራንዮ አደባባይ በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ ሞትን በሞቱ ገድሎ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን አጥፍቶ ሕይወትን ሰጥቶናል፡፡ በመስቀሉ ጥልን ገደለ እንዳለ፡፡ ኤፌ 2÷16

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሰቀሉት አይሁድ ምንም በደል የሌለበትን ሰቅለው ገደሉት ይሉናል በማለት የጌታችን ክቡር አካሉ ያረፈበት፣ እጆቹና እግሮቹ የተቸነከሩበት፣ ጎኑ በጦር ተወግቶ ደሙ የፈሰሰበትን ቅዱስ መስቀል ክርስቲያኖች እየተሳለሙና እየዳሰሱ በተአምራት እንዳይድኑበት መስቀሉን ጉድጓድ ቆፍረው ቀብረውታል፡፡ ይህ ቅዱስ መስቀል ተቀብሮ ሦስት መቶ ዓመት ቢያስቆጥርም ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ “የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለምና” እንዳለ (ማቴ 10÷26) እግዚአብሔር በጥበቡ የተሰወረው ተገልጦ እንዲወጣ ፈቃዱ በመሆኑ ቅድስት እሌኒንና ልጇ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን መስቀሉን እንዲፈልጉ አድርጎ አስነሣቸው፡፡ ቅድሰት እሌኒም መስቀሉን ፍለጋ ከሮም ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች፤ ልጇ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም የመስቀሉን ኃይልና አሸናፊነት በሰማይ ሰሌዳ በብርሃን ተቀርጾ ስላዬ ለእናቱ አስፈላጊውን ሁሉ አግዟታል፡፡ እሷም የመስቀሉን ነገር ስትመረምር ኪራኮስ የተባለ አረጋዊ መስቀሉ “ከሦስቱ ተራራዎች በአንዱ እንዳለ ይነገራል” ብሏታል

እርሷም ሱባኤ ብትገባ መልአከ እግዚአብሔር እያመለከታት ካህናትን ጠርታ ጸሎት አድርሰው ሕዝቡን ደመራ አሰብስባ ጸሎተ ዕጣን የተጸለየበትን ዕጣን በመጨመር ደመራው በእሳት ሲለኮስ የደመራው ጢስ (የዕጣኑ ጢስ) መስቀሉ ያለበትን ተራራ መስከረም ዐሥራ ስድስት ቀን አመላክቷታል፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ዳዊት “ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፡፡” ያለው፡፡ እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸው በመፍራት ለሚያመሰግኑት ኃይሉን በማመን በፍጹም ልብ ለሚፈልጉት ምልክትን እንደሚያሳይ የመስቀሉ ነገር ታላቅ ምስክር ነው፡፡

ቅድሰት ንግሥት እሌኒ ምልክቱን ኳየች በኋላ በተራራው የተቀበረውን መስቀል ለማስወጣት መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ማስቆፈር ጀምራ መጋቢት ዐሥር ቀን እንደ ፀሐይ የሚያበራው ጌታችን የተሰቀለበት መስቀል ከተቀበረበት ወጥቷል፡፡ ይህንን የደመራና የመስቀል በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ እኛ አማኞች ሁላችንም መስቀል የማያቋርጥ የእግዚአብሔር ኃይል መገለጫ መሆኑን በማመን በዓሉን ወደ ደመራ ቦታ በመሄድ “መስቀል ከሁሉ በላይ ነው፤ዛሬ መስቀል ከበረ፣ዓለም ለድኅነት ተጠራ፣ሰውም ነጻ ወጣ፡፡” በማለት የቅዱስ ያሬድን ዝማሬ እየዘመርን በታላቅ ድምቀት እናከብረዋለን፡፡ የመስቀሉ ኃይል ጽንዕ ይሁነን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡