“ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግባቸውን ሰጠሃቸው፡፡” መዝ 73፡4

“ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግባቸውን ሰጠሃቸው፡፡” መዝ 73፡4

ኢትዮጵያዊው ሊቅ፣ማኅሌታይና የዜማ ደራሲ ቅዱስ ያሬድ ግንቦት 11 የተሠወረበት ቀን ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን የመላእክትን ምግብ /ምስጋና/ እንደበሉ ቅዱስ ዳዊት ሲገልጽ “ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግባቸውን ሰጠሃቸው” ብሏል ምግብ የተባለም ምስጋና ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ምግብ የተባለ የመላእክትን ምስጋና በሊቁ ቅዱስ ያሬድ አማካኝነት አግኝታለች፡፡

ቅዱስ ያሬድ ከአባቱ ከአብዩድ/ይስሐቅ/ ከእናቱ ከክርስቲና/ታውክልያ/ በ505 ዓ.ም ሚያዚያ 5 ቀን በአክሱም ከተማ ተወለደ፡፡ ቅዱስ ያሬድ የሰባት ዓመት ብላቴና በሆነ ጊዜ አባቱ ስለሞተ አጎቱ እንዲያሳድገውና እዲያስተምረው የአክሱም ገበዝ መምህር ለነበረው አጎቱ ጌዴዎን ተሰጠ፡፡ መምህር ጌዴዎን አቅሙንና እውቀቱን በመገመት ለተማሪዎች በሉ ፊደል አስቆጥሩት አላቸውና ትምህርቱን ጀመረ፡፡ ሆኖም ቃለ እግዚአብሔርን የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለነበር አብረው የሚማሩትም ሕፃናት “ሰነፍ ያሬድ እንጨት ስበር ውኃ ቅዳ” እያሉ ሲያፌዙበትና ሲቀልዱበት አጎቱ ጌዴዎንም ከሕፃናቱ ጋር ሊወዳደር ባለመቻሉና መዝሙረ ዳዊትን ማጥናት አቅቶት ወደ ኋላ በመቅረቱ ከትምህርቱ ድክመት የተነሳ በጨንገር (በአለንጋ) ቢገርፈው ሕፃኑ ያሬድም በዚህ ተበሳጭቶና ተስፋ ቆርጦ ከአክሱም ከተማ ወጥቶ ወደ እናቱ መንደር ሲጓዝ የኢትዮጵዊቷ ንግሥተ ሳባ እና የንጉሠ እስራኤል ሰሎሞን ልጅ ቀዳማዊ ምኒልክ (እብነ ሐኪም) የተቀበረበት ማይኪራህ ቦታ ደረሰ ፡፡

ማይኪራህ ከምትባል ቦታ በውኃው ዳር በአንዲት ዛፍ ሥር ተጠግቶ እያዘነ ሳለ አንድ ትል የዛፏን ፍሬ ለመመገብ ፈልጎ ወደ ላይ እየወጣና እየወደቀ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ ከቆየ በኃላ በሰባተኛው ጊዜ ወደ ዛፉ ወጥቶ ፍሬዋን ሲመገብ ተመለከተ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከዚህ ትል ትዕግስት ፣ጽናት ፣ጥረት፣ ስኬት ትምህርት ወስዶ እኔም እኮ ተስፋ ሳልቆርጥ ብዙ ጥረት ካደረኩ እግዚአብሔር ያሳካልኛል ብሎ በተስፋ ተጽናንቶ እንደገና ወደ መምህሩ በመመለስ ትምህርቱን ለመቀጠል ወሰነ፡፡ ማይኪራህ ማለትም ማይ የተባለው ውኃው ኪራህ (ኬራዋሕ) የተባለው ዛፉ ነው ፡፡ የሀገሬው ሰው ማይ አቡነ ያሬድ (የአባታችን ያሬድ ውኃ ) እያለ እስከ ዛሬ ድረስ ከጥላዋ ሳያርፍ ከውኃው ሳይጠጣ አያልፍም፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ያሬድ ስላረፈባት ኋላም ስለጸለየባት ከድካም ታሳርፋለች ከሕመም ትፈውሳለችና ነው ፡፡

ቅዱስ ያሬድም ወደ መምህሩ ተመልሶ አጎቱን ይቅርታ ጠየቀ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡አጎቱም ተደስቶ እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናውን ያበራለት ዘንድ እያለቀሰ ፈጣሪውን ለመነለት ከዚያም ቅዱስ ያሬድ ትምህርቱን በመቀጠል መጻሕፍትን ጠንቅቆ ዐወቀ፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን በተመለከተ የሚከተለውን ዐርኬ ደርሰውለታል፡፡ “ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ። እንተ አዕረገ በልቡ ኅሊና መንፈስ ረዋጼ። ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ። በብዙኅ ጻማ ዘአልቦ ሑጻጼ። መልዕልተ ጒንደ ዖም ነጺሮ እንዘ የዐርግ ዕዴ።

ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ፤
እንተ አዕረገ በልቡ ኅሊና መንፈስ ረዋጼ፤
ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ፤
በብዙኅ ፃማ ዘአልቦ ሑፃፄ፤
መልዕልተ ጕንደ ዖም ነጺሮ እንዘ የዓርግ ዕፄ፡፡

(ይህን ዐርኬ መምህራን ጠዋት ጉባኤ ሲዘረጉ ተማሪዎቻቸውን ያስደርሳሉ፡፡)

ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግባቸውን ሰጠሃቸው እንዳለ ነቢዩ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ሆኖ ወደ ቅዱስ ያሬድ ከኤዶም ገነት በሥላሴ አምሳል ሦስት አእዋፋትን ላከ፤ እነሱም በግእዝ፣ በዕዝል እና በአራራይ ዜማ ቅዱስ ያሬድ በቆመበት ቦታ ፊት ለፊት በአየር ላይ ቆመው መንፈስ ቅዱስ በወፍ ተመስሎ ለቅዱስ ያሬድ ዜማ ሲገልጽለት፤ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ወደ ሰማይ ተመልክቶ እናንተ በሰው አንደበት የምትናገሩ ወፎች ከወዴት መጣችሁ›› አላቸው? ከሦስቱ አንዲቱ እንዲህ ስትል ተናገረችው፤ ‹‹ከኤዶም ገነት ወደ አንተ ተልከን፤ከሃያ አራቱ ካህነተ ሰማይ ማሕሌትን ትማር ዘንድ ልንነግርህ መጣን›› አሉት፡፡ ቅዱስ ያሬድም ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በአካል ተነጠቀ፡፡

ሊቁ በሰማይ የሰማውን የመላእክትን ዜማ አድንቆ ሲነግረን እንዲህ አለ “ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ቅዱሳን እንዘ ይብሉ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር መልአ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ” ከቅዱሳን መላእክት በሰማይ የሰማኹት ዜማ ዋ! ምን ይደንቅ! ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ፥ የክብርህ ምስጋና ሰማያትንና ምድርን መላ እያሉ ብሎ ገልጾታል፡፡

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ተነጥቆ ከተወሰደበት ቀድሞ ወደ ነበረበት ቦታ ተመልሶ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ”አርያም” የተባለውን የመጀመሪያውን ዜማ አደረሰ፡፡
የቅዱስ ያሬድ የዜማ ዓይነቶች ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም ግእዝ፣ ዕዝልና አራራይ በመባል ይጠራሉ፡፡ ሦስቱም የዜማ ዓይነቶች ምን ጊዜም ሕያዋን ሆነው በቤተ ክርስቲያን ሰፊ አገልግሎት ሲሰጡ ይኖራሉ፡፡

ቅዱስ ያሬድ አምስት የዜማ መጻሕፍትን ደርሷል እነሱም ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬና መዋሥዕት ናቸው፡፡ የ፲፬ቱ ቅዳሴያት የዜማ ባለቤትም ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ብሉይን ከሐዲስ ያስማማ፣ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በሚገባ የያዘ፣ለአራቱ የዓመቱ ወቅቶች እንዲስማማ አድርጎ ለበጋ፣ ለክረምት፣ ለመጸውና ለጸደይ(ለበልግ) እንደሚሆን አድርጎ፤ለየበዓላትም ተስማሚ በሆነ መልክ ድርሰቱን በግእዝ፣ በዕዝልና በአራራይ ዜማ ያዘጋጀ ታላቅ ሊቅ ነው፡፡ የዜማ ድርሰቱ ለልዑል እግዚአብሔር፣ለእመቤታችን፣ለቅዱሳን መላእክት፣ ለጻድቃንና ለሰማዕታት ተገቢ የሆነውን ምስጋና የያዘ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድም ስውር ዋሻ ውስጥ ገብቶ ከሰሜን ተራራዎች ውስጥ እየጾመና እየጸለየ በብህትውና ለብዙ ዘመን ከኖረ በኋላ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን እንዲህ በማለት ለመነው፡፡ “ዘገብረ ተዝካርየ ወተዝካረ ጌድዮን መምህርየ ወተዝካረ አዳም አቡነ ምንት እንከ አስቡ፤ መታሰቢያዬን የመምህሬን የጌድንንን መታሰቢያ የሁላችንንም አባት የአዳምን መታሰቢያ ያደረገ እንግዲህ ዋጋው ምንድን ነው?” አለው፡፡

እግዚአብሔርም እንዲህ አለው “የክብር መቀመጫ አስቀምጠው ዘንድ በመንግሥቴ ማልኩልኽ በፍርድ ቀን ማለትም በዕለተ ምጽአት ያለ ሐፍረት በግልጥ ከአንተ ጋራ ይለፍ” አለው፡፡ እንዲሁም “መታሰቢያህን ያደረገ የገድልህንም መጽሐፍ የጻፈ ፣ያጻፈ ንዑድ ምስጉን ክቡር ነው፤ እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጠዋለሁ፤ የክብር ዙፋንም አወርሰዋለሁ” አለው፡፡ ይህንንም ቃል ኪዳን ጌታችን ከሰጠው በኋላ በሰሜናዊ ምሥራቅ በኩል ግንቦት 11 ቀን ተሠወረ::

የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት የሊቁ ቅዱስ ያሬድ በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር!