ለእናቷ አንዲት ናት፤ለወለደቻትም የተመረጠች ናት፡፡ (መኃ 6፥9)

ለእናቷ አንዲት ናት፤ለወለደቻትም የተመረጠች ናት፡፡ (መኃ 6፥9)

እንኳን ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ !

እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱሳን ከሆኑ ከኢያቄምና ከሐና የተወለደችበት ቀን ነው፡፡ አያቶቿና ወላጆቿ ንጹሐን፣ ቅድሳን እንደሆኑ ቅዱስ ዳዊት “መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው” /መዝ.86፥1/ በማለት መሥክሯል፡፡ ይህ ምስክርነት አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ለኩነተ ሥጋ የመረጣት ቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆቿ ንጹሐን፣ ቅዱሳን የሆኑ እግዚአብሔርን የሚወዱና የሚያከብሩ መሆናቸውን የሚያስረዳን ነው፡፡ ስለሆነም የሰው ልጆች ሁሉ የድኅነት ምልክት የሆነች እናታችን ለእናቷ አንዲት የተመረጠች የሆነች ቅድስተ ቅዱሳን ንጽሕተ ንጹሐን እመቤታችን ድንግል ማርያም በዛሬው ቀን በሊባኖስ ተራራ የተወለደችበት በዓል ነው፡፡

ሶሪያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም “አክሊለ ምክሕነ ወቀዳሚተ መድኃኒትነ፡፡ ወመሠረተ ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል፡- የመመኪያችን ዘውድ የድኅንነታችን መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሠረት በድንግል ማርያም ሆነልን” በማለት የድኅነታችን ምክንያት የሆነች ቅድስተ ቅዱሳን እናታችን መሆኗን መስክሯል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሊባኖስ ተራራ እንደ ተወለደች የሐና ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ በሰሙ ጊዜ ፍጹም ደስ ብሏቸው ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰበሰቡ፡፡ ሕፃኗን /እመቤታችንን/ ተመልክተው ፍጹም አደነቁ፡፡ እርስ በርሳቸውም እንደዚች ያለች ብላቴና ከቶ አይተን አናውቅም ተባባሉ፤ ጸጋ እግዚአብሔር በእርሷ አድሯልና፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በሰውነቷ ሁሉ መልቷልና፡፡ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት ሐና ጋራ ደስ እያላቸው የእግዚአብሔርን ቸርነት እየተናገሩ ሰባት ቀን ተቀመጡ፤ ያችንም ብላቴና ስምዋን ማርያም አሏት ይኸውም የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው፡፡

በተራራው ላይም ሌላ የሚበሉት ነገር ስላልነበር በእነዚህ ቀናት ጥሬ ቀቅለው ይመገቡ ነበር። በዚህ ትውፊት መሠረት ምእመናን በየዓመቱ ግንቦት 1 ቀን የእመቤታችንን ልደት በማሰብ ከቤታቸው ወጥተው ከያሉበት በመሰባሰብ ንፍሮ ቀቅለው፣ አነባብሮ ጋግረውና ዝክር አዘጋጅተው በመንፈሳዊ ደስታ በምስጋናና በዝማሬ የእመቤታችን የልደት በዓል ያከብራሉ፡፡

ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም

በእመቤታችን ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ሆነ፡፡