“መላእክት ዘወትር ምግብሽን እያመጡ፤በቤተ መቅደስ ኖርሽ” አንቀጸ ብርሃን

“መላእክት ዘወትር ምግብሽን እያመጡ፤በቤተ መቅደስ ኖርሽ” አንቀጸ ብርሃን

የእመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ መግባት

ኢያቄምና ሐና የሚባሉ በተቀደሰ ትዳር የሚኖሩ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም ፤ ሐናና ኢያቄም ልጅ ስለሌላቸው ያዝኑ ነበር፤ሁልጊዜም ወደ ቤተ እግዚአብሔር እየሄዱ እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ልመና ያቀርቡ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሲሄዱ ሐና “ርግቦች ከልጆቻቸቸው ጋር ሲጫወቱ” አየች ለእነዚህ አዕዋፋት ልጆች የሰጠህ ምነው እኔን ልጅ ነሳኸኝ? ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፡፡ ኋላም ከቤተ እግዚአብሔር ደርሰው ወንድ ልጅ ብትሰጠን አርሶ፣ቆፍሮ፣ወጥቶ ወርዶ፣ነግዶ ይርዳን አንልም፤ለቤት እግዚአብሔር አንጣፊ፣መጋረጃ ጋራጅ ይሆን ዘንድ እንሰጣለን፤ሴት ብትሰጠን ውኃ ቀድታ እንጨት ለቅማ ትርዳን አንልም፤ለቤተ እግዚአብሔር ማይ ቀድታ፣መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣መጋረጃ ፈትላ እንድታገለግል እንሰጣለን ብለው ተሳሉ፡፡ እግዚአብሔርም የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ኀዘናቸውንና ልመናቸውን ሰማ ልጅንም ሰጣቸው፡፡ ሐናም በፈቃደ አምላክ ነሐሴ ሰባት ቀን ጸንሳ በግንቦት አንድ ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደች፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት ሲሆናት፤ሐና ኢያቄምን በስለት ያገኘናት ልጃችን አፏ እህል ሳይለምድ ሆዷ ዘመድ ሳይወድ ለቤተ እግዚአብሔር እንስጥ? አለችው፡፡ እርሱም ፍቅርሽ ይወጣልሽ እንደሆነ ብየ ነው እንጂ ብሏት ይሁን ይሁን ተባብለው በተሳሉት ስለት መሠረት ልጃቸውን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፡፡ በቤተ መቅደስ የካህናት አለቃ የነበረው ካህኑ ዘካርያስ ተቀበላቸው፡፡ ሐና እና ኢያቄም ለእግዚአብሔር የገቡትን ቃል የተደረገላቸውንም ድንቅ ተአምር ነገሩት፡፡ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስም የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ እያደነቀ ሳለ አንድ ነገር አሳሰበው የሦስት ዓመት ብላቴና ምን እናበላታለን? ምን እናጠጣታለን? ብሎ ከካህናቱ ጋር ሲያወጡ ሲያወርዱ ወዲያው ከሰማይ መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ ይዞ ረቦ ታየ፡፡

ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ለእርሱ የወረደ መስሎት ቢነሣ ወደ ላይ ራቀበት፤ከካህናቱም ቢነሡ ራቀባቸው፤ሐናና ኢያቄምም ቢነሱ ራቀባቸው፤ሐናን ምናልባት ለዚህች ብላቴና የመጣ እነደሆነ እስቲ ፈቀቅ በይ አሏት፡፡ ትታት ፈቀቅ ብትል እመቤታችን ወደ እናቷ ድንኩል ድንኩል እያለች ስትሄድ መልአኩ ወርዶ እመቤታችንን በሰው ቁመት ያክል ከፍ አድርጎ አንድ ክንፉን አንጥፎ በአንድ ክንፉ ጋርዶ ኅብስቱን መግቧት ጽዋውን አጠጥቷት ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ “ወሶቤሃ ወረደ ፋኑኤል ሊቀ መላእክት ወጸለላ በአክናፊሁ ወተለዐለ ላዕለ መጠነ ቆመ ብእሲ ወወሀባ ወመጠዋ ወዐርገ ውስተ ሰማይ” እንዲል

ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስና ሕዝቡም እግዚአብሔር ምግቧን እና መጠጧን እንዳዘጋጀላት ተመለከቱ፡፡ ከዚያም ካህኑ ዘካርያስ የምግቧ ነገር ከተያዘልንማ ከሰው ጋር መኖር ምን ያደርግላታል ብሎ በፍጹም ደስታ እመቤታችንን ተቀብሎ ታኅሣሥ ሦስት ቀን በሦስት ዓመቷ ወደ ቤተ መቅደስ አስገባት ይህም ዕለት በዓታ ለማርያም ተብሎ በድምቀት ይከበራል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት መነጽር ንጽሕናዋን ቅድስናዋን አይቶ እግዚአብሔር ለእናትነት እንደመረጣት ተመልክቶ እንዳመሰገነ “ልጄ ሆይ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፣ወገንሽን የአባትሽንም ቤት እርሽ፣ ንጉሥ ውበትሽን ወዷልና፣እርሱ ጌታሽ ነው” መዝ 44÷10 ያለው ተፈጽሞ “በእግዚአብሔር ሥዕል የተሣሉ ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ እንቺ ነሽ” የተባለች መቅደስ እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ ገብታ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረች፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘእሑድ) መላእክት እየጎበኟት ምግቧን እያመጡ ዐሥራ ሁለት ዓመታትን በቤተ መቅደስ ስለመቆየቷ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን እንዲህ ብሎ ገልጿል “ከንጹሓን ይልቅ ንጽሕት የሆንሽ አንቺ ነሽ፤ ከማይነቅዝ ዕንጨት እንደተሠራ በወርቅ
እንደተጌጠና ዋጋው ብዙ በሆነ በሚያበራ ዕንቊ እንደተለበጠ ታቦት በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖርሽ የተመረጥሽ ድንግል ነሽ፤ እንዲህ ሆነሽ በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ፤ መላእክት ዘወትር ምግብሽን ያመጡ ነበር፤ መላእክት እየጎበኙሽ እንዲህ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖርሽ፤ መጠጥሽም የሕይወት መጠጥ ነበር፤ ምግብሽም የሰማይ ኅብስት ነበር፡፡” ብሏል አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው ስለጽንሰቷ ፣ መላእክት እየጎበኟት እየመገቧት በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ ስለመኖሯ እንዲህ ብሎ አመስግኗታል፡፡

“ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም፤በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጅ፤ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ፤ ድንግል ሆይ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ኅብስትን ነው እንጂ፤ ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ፤ ድንግል ሆይ ከአንቺ አስቀድሞ ከአንቺም በኋላ እንዳሉ ሴቶች መተዳደፍን የምታውቂ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና ያጌጥሽ ነሽ እንጂ፤ ድንግል ሆይ የሚያታልሉ ጐልማሶች ያረጋጉሽ አይደለም የሰማይ መላእክት ጎበኙሽ እንጂ እንደተነገረ ካህናትና የካህናት አለቆች አመሰገኑሽ እንጂ”

እመቤታችንን አመስግነን ንጽሕናዋን ተጎናጽፈን በቅድስና እንድንኖር የእግዚአብሔር ቸርነት የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ አይለየን።

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር፡፡