“ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ” (ጾመ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ) እንኳን ለዐቢይ ጾም አደረሳችሁ።

 “ጾምሰ እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ፣ ወነቅዓ ለአንብዕ ወጥንተ ኩሉ ገድል ሠናይት፡፡” እንዳለ ሊቁ ጾም የጸሎት እናት፣የአርምሞ እኅት፣የዕንባ ምንጭና የመልካም ገድል የትሩፋት ሁሉ ጥንተ መሠረት ናት፡፡ ጾም ማለት ለሰውነት የሚያምረውንና የሚያስጎመጀወን ነገር መከልከል፣ከጥሉላት ምግብ መከልከል፣ለጊዜው ከእህል ውኃ መከልከል፣እየወደዱ መራብና መጠማት በአጠቃላይ ፈቃደ አምላክ የምንፈጽምበት፤ ኃጢአታችንን ለማስተስረይ ደካማ ሥጋችንን ለነባቢት ነፍስ የምናስገዛበት እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን ባደረግን ጊዜ ትሩፋተ ገድል ይጸናልናል፣የነፍስ ሐሴት ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና ሥርዓት መሠረት ሰባት የአዋጅ አጽዋማት አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ዐቢይ ጾም ነው፡፡ የዚህ ዓመት ዐቢይ ጾም በባሕረ ሐሳብ አስተምህሮ መሠረት መባጃ ሐመር 18 ስለዋለ ጾመ ነነዌ የካቲት 18 ሰኞ ውላለች። የዐቢይ ጾም ተውሳክ ደግሞ 14 ነው። 18ንና 14 ስንደምራቸው 32 ይሆናሉ። 30ውን ስንገድፍ ሁለት ስለሚቀር መጋቢት 2 ሰኞ ዐቢይ ጾም ገብቷል። ይኽም ጾም ዐቢይ ጾም /ታላቅ ጾም/ የተባለበትም ምክንያት ልዑል እግዚአብሔር የባሕርይ አምላክ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጾመውና በዚህም አርዕስተ ኃጣውእን፣ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስን ድል ነስቶ ፤ እንድንጾም በማዘዝ ፣እኛም ብንጾም የሚመጣብንን ፈተና ሁሉ በእርሱ ኃይል ድል እንደምንነሳ ለማስተማር ፣ለአብነት ስለጾመው ዐቢይ ጾም ተብሏል፡፡ (ማቴ 4፡1-11፤6፡16)

ዐቢይ ጾም ከምሥጢራዊ ትርጉም አንጻርም ጾመ ሁዳዴ/ኩዳዴ/፣የቀድሶተ ገዳም ጾም፣የአስተምህሮ ጾም፣የድል ጾም፣የካሳ ጾም ይባላል፡፡ ይህም ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት (ሃምሳ አምስት ቀናት) አሉት፡፡ የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡ ስያሜው ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው “ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ“ ያለውን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ እግዚአብሔር አካላዊ ቃል ወልድ ለድኅነተ ዓለም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው በመሆኑ፤ በዚህም አምላክ ሰው ሰው አምላክ የሆነበትን የተዋሕዶ ምሥጢር በማሰብ የምንጾመው ጾም ነውና ዘወረደ ተባለ፡፡ (ዕብ 2፡14 ፤ ዮሐ 1፡9-14) ‹ጾመ ሕርቃል›ም ይባላል፤ሕርቃል በ614 ዓ.ም የቤንዛንታይን ንጉሥ የነበረ በዘመኑ ፋርሶች ወርረው የጌታችንን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ ምእመናን “ተዋግተህ አስመልስልን” አሉት እሱም ሐዋርያት “ነፍስ የገደለ መላ ዘመኑን ይጹም” ብለዋል አላቸው፡፡ እኛ እንጾምልሃለን አሉት። እንዲያስ ከሆነ የጌታ መስቀልን አስመልሳለሁ ብሎ ዘምቶ ተዋግቶ መስቀሉን ከፋርስ አምጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም አስመለሰ፡፡ ይኸንን በማሰብ የመስቀል ፍቅር የተገለጠበት ጾም ነውና ከዐቢይ ጾም ሳምንት ውስጥ አስገቡት ለዚህም ጾመ ሕርቃል ተባለ፡፡ ስለዚህም ከዘወረደ ጀምረን ስምንቱንም ሳምንታት እንድንጾም አባቶቻችን ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡(ፍትሕ.ነገ 15፡596)  ስለዚህም ጾምና ጸሎት የማይነጣጠሉ እናትና ልጅ ስለሆኑ፤ ጾም የትሩፋት ሁሉ ምንጭም ናትና በትሩፋት ስንጾም ስንጸልይ ኃይል መንፈሳዊ እናገኛለን አጋንንትን ድል እንነሳለን፡፡ በትጋት በፍጹም ፍቅርና በትኅትና ጾመን ልዑል እግዚአብሔር በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ያድለን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር