“ጻድቃን ወደ ጌታቸው ሄዱ እንጂ አልሞቱም” ቅዱስ ያሬድ

“ጻድቃንሰ ኢሞቱ ኀበ እግዚኦሙ ነገዱ”
“ጻድቃን ወደ ጌታቸው ሄዱ እንጂ አልሞቱም” ቅዱስ ያሬድ

በ መ/ር ሃፍታሙ ኣባዲ

ከአባታቸው ጸጋ ዘአብ ከእናታቸው እግዚእ ኀረያ በስእለት የተወlዱት ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሕጻንነታቸው ጀምሮ ድንቅ ተአምራትን እያደረጉ ዕውቀትንና ኃይልን ተመልተው በመንፈስ ቅዱስ የጸኑ ቅዱስ አባት ናቸው። ዲቁና ይሾሙ ዘንድ ወደ ጳጳስ በተወሰዱ ጊዜ “ይህ ልጅ የተመረጠ ዕቃ ይሆናል” ተብሎ ትንቢት ተነገረላቸው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስን ምርጥ ዕቃ ብሎ እንደጠራው አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ ጣዖታትን ለማጥፋት፣ ሃይማኖትን ለማጽናት በእግዚአብሔር የተመረጡ ዕቃ ሆኑ። በዚህም ቅዱስ ጳውሎስን መሰሉት። በወጣትነት ዕድሜያቸው አራዊትን ሊያድኑ በሄዱ ጊዜ ጌታችን መልኩ በሚያምር ጎልማሳ አምሳል ተገለጠላቸው። “ወዳጄ አትፍራ ከእንግዲህ ወዲህ የኃጢአተኞችን ነፍስ ወደ ሕይወት የምታጠምድ ትሆናለህ እንጂ አራዊትን የምታድን አትሆንም ስምህ ተክለ ሃይማኖት ይሁን” አላቸው። በዚህም ዓሣ ከማጥመድ በወንጌል መርከብ ለመንግሥተ እግዚአብሔር የሰዎችን ነፍስ ወደ ማጥመድ የተጠራውን ስሙም ከኬፋነት ወደ ጴጥሮስነት የተቀየረውን የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስን መሰሉት።

የጌታን ጥሪ ተቀብለው፣ ገንዘባቸውን ለድሆች ሰጥተው “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል” ብለው ወጡ። (ማቴ. 16፥26) ከሊቀ ጳጳሱም ዘንድ ቅስና ተቀብለው አገልግሎት ጀመሩ። በመላ ኢትዮጵያ እየተዟዟሩ ወንጌልን ሰበኩ። አስተምረው አጠመቁ፤ሕሙማንን ፈወሱ፤ ብዙ ተአምራትን አደረጉ። ጠንቋዮች እና ሟርተኞችን አጠፉ። ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ በጾምና በጸሎት በስግደት ተጠምደው መንፈሳዊ ተጋድሎን ተጋደሉ። በአንድ እግራቸው ለሰባት ዓመት ቆመው እስከ መጸለይ የበረቱ ሆኑ። ብዙ መከራም ተቀበሉ። “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔር ከሁሉ ያድናቸዋል። እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፥ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም።” (መዝ. 33፥19-20) ተብሎ እንደተጻፈ አባታችን ብዙ መከራ ተቀበሉ። እግዚአብሔርም ጠበቃቸው። “እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊልንም እሰጥሃለሁ” (ራእ. 2፥10) የተባለውን ቃል ኪዳን እያሰቡ እስከ መጨረሻ ጸኑ።

ጌታችንም “አንተ በመከራዬ መሰልከኝ እኔም በመንግሥቴ ከእኔ ጋራ እንድትመስለኝ አደርጋለሁ። እነሆ የዚህ ዓለም ድካምህ ተፈጸመልህ በእኔ ዘንድም የምቀበለው ሆነ ከእንግዲህ መንግሥተ ሰማያትን ትወርስ ዘንድ ና።” ብሎ ጠራቸው። በንዳድ በሽታ ጥቂት ታመው ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀን ዕድሜያቸው ነሐሴ 24 ቀን በለመለመ ዕርጅና ዐረፉ። “ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።” ተብሎ የተነገረውን በሕይወታቸው አሳዩ። (ሮሜ. 6፥5)አባታችን ቅዱስ ያሬድ “ጻድቃንሰ ኢሞቱ ኀበ እግዚኦሙ ነገዱ፥ በመንግሥተ ሰማይ ይሁቦሙ ዘፈደቁ” ጻድቃን ወደ ጌታቸው ሄዱ እንጂ አልሞቱም፤ በመንግሥተ ሰማይም የወደዱትን ይሰጣቸዋል፡፡ ብሎ እንዳመሰገነው የጻድቃን ዕረፍታቸው ሕይወታቸው ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ ሕያዋን ናቸው እንጂ ሙታን አይደሉም። “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል።” እንዲል። (ዮሐ. 11፥25) አምላካቸውም የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። (ማቴ 22፥31-32፤ማር 12፥27፤ሉቃ 20፥38) ጻድቃን ከአምላካቸው በተሰጣቸው ቃል ኪዳንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትና በረከትን ያሰጣሉ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት “ስምህን ለሚጠራ፣ መታሰቢያህን ለሚያደርግ፣ ገድልህን ለሚጽፍ፣ ለሚያነበውና ለሚሰማው፣ ቤተ ክርስቲያንህን ለሚሠራ፣ በስምህ መባዕ ለሚሠጥ፣ ለድሆች በስምህ ለሚመጸውት፣ በመታሰቢያህም ቀን ለሚቆርብ ስለ አንተ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሌ እኔ እስከ አሥር ትውልድ እምርልሃለሁ” ብሎ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። እኛም ከዚህ ቃል ኪዳን እንድንጠቀም “የጻድቅ መታሰቢያው ለበረከት ነው” (ምሳ. 10፥7) የሚለውን አምላካዊ ቃል እያሰብን በእምነት በጻድቁ ስም የጽድቅን ሥራ ልንሠራ ይገባናል።

በዓሉ የሰላምና የፍቅር በዓል ይሁንልን፤የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በረከታቸው ይደርብን። አሜን