በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን

እመቤታችን ተነስታለች!

/አክሊለ ሰማዕት/

“አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት፡፡” መዝ.131÷8

ክቡር ዳዊት ከላይ የተጠቀሰውን መዝሙር ለጊዜው ለባቢሎን ምርኮ ትሩፋን ወይም ቅሬታዎችና ለዘሩባቤል ተናግሮታል፡፡ ለፍጻሜው ግን ስለ እመቤታችን ትንሳኤ ገልጾበታል፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ተነስቶ እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞታ አትቀርምና፤ አንተ ብቻ ሳትሆን አማናዊት የመቅደስህ ታቦት የተባለች እመቤታችንን ይዘህ ተነስ ሲል ነው፡፡ ዳሩ የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ የሁላችንም (የጻድቃንም የኃጥአንም) ትንሳኤ ነው፡፡ በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጆት ሁሉ ከሞት ይነሳሉና፡፡

ታዲያ በጌታችን አማካኝነት ለሁሉ የተሰጠ ትንሳኤ ለእመቤታችን ቀድሞ መደረጉ ምን ያስደንቃል? የሚያስደንቀው የመለኮት እናት ሆና ሳለ ሞትን መቅመሷ ነው እንጂ፡፡ ለዚህም ነው ሊቁ “ሞትስ የሚሞትን ሥጋ ለለበሰ ሰው  ይገባዋል፤ የድንግል ማርያም ሞት ግን ለሁሉም ይደንቃል፡፡” ያለው፡፡

እመቤታችን የመቅደሱ ታቦት ምሳሌ መሆኗን መረዳት አስፈላጊ ሲሆን፤ እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡

አስቀድሞ እግዚአብሔር ለሙሴ ጽላትን ከሰጠው በኋላ ከግራር እንጨት ታቦትን እንዲሠራ አዘዘው፡፡ ታቦት ማለት ማደሪያ ማለት ነው፡፡ ይህም የጽላቱ ማኖሪያ ማደሪያ መሆኑ ነው፡፡ ታቦቱ የእመቤታችን ጽላቱም የጌታችን ምሳሌ ሲሆን፤ ጽላቱ በታቦቱ ውስጥ እንደሚያድር ጌታችንም በማህጸነ ድንግል ማርያም አድሯል፡፡ “እንደ እመቤታችን እንደማርያም የወልድ ማደሪያ የሆነ ማን ነው;” እንደሚል መቅድመ ተአምር፡፡ ነገርግን ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግል ማህጸን አድሮ ብቻ የወጣ አይደለም፤ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ተዋህዶ ነው እንጂ፡፡ ስለዚህም ለተዋህዶ የመረጣትን አካል በምድር አይተዋትም፡፡

ክቡር ዳዊት ቅዱስ የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል? (ሳሙ.6÷9) ብሎ የጠየቀው  በወርቅ የተለበጠው ታቦት ከአሚናዳብ ቤት ወደ ከተማው ሲመጣ ነበር፡፡ እመቤታችንም አማናዊት ታቦት ሆና ጌታን በማህጸኗ ተሸክማ ወደ ቅድስት ኤልሳቤጥ ብትሔድ “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?” (ሉቃ 1÷43) በማለቷ የታቦቱን የእመቤታችን ምሳሌነት አጉልቶ ያሳያል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ታቦቷን ሳይገባው የነካት ዖዛ መቀጣቱን እናገናዝባለን፡፡ እንደዚሁ የእመቤታችን ሥጋዋ አርፎበት የነበረውን አልጋ ከይሁድ ተልኮ በድፍረት የነካው ታውፋንያ በመልአኩ ሰይፍ እጁን ተቀጥቷል ::

በተጨማሪም በደብተራ ኦሪት በድንኳን በኋላም በሰዎች ቤት የነበረችው ታቦተ ጽዮን ጊዜው ሲደርስ በሰሎሞን ወደተሰራው ቤተ መቅደስ ገብታለች (2ኛ ዜና 5)፡፡ እመቤታችንም አማናዊት ታቦት ናትና ጥቂት ጊዜ ከወላጆችዋ ጋር ከቆየች በኋላ ወደቤተመቅደስ ገብታለች፡፡ “ንጽሕተ ንጹሐን ከዊና፡ ከመታቦት ዘዱር ዘሲና ውስተ ቤተ መቅደስ ነበረት በድንግልና” ማለትም ከንጹሐን ሁሉ ንጽሕት ሆና በዱር እንደነበረች እንደሲናዋ ታቦት በቤተ መቅደስ ኖረች እንዳለ፡፡ እንዲሁም ‘’አንቲ ውእቱ ንጽሕት እምንጹሐን ዘነበርኪ ውስተ ቤተ መቅደስ ከመ ታቦት” እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡

ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መካከልም ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ “ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸች በውስጥና በውጪ በወርቅ የተለበጠች ታቦት አንቺ ነሽ” ይላታል፡፡ እንዲሁም “ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ጌታ ማደሪያው ሆንሽ፤ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህጸንሽ ተሸክመሽዋልና” ብሎ ያመሰግናታል፡፡ ማደሪያ ያለውን በግእዙ ታቦት እንደሆነ “ኮንኪ ታቦቶ ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር፡፡” ከሚለው ትርጉም መረዳት እንችላለን፡፡

ስለዚህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማናዊት ታቦት መሆኗን ከላይ ከተረዳን፤ ክቡር ዳዊት “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ፤አንተና የመቅደስህ ታቦት” ማለቱ አንድም ስለትንሳኤዋ መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር 21 ቀን 0050 ዓ.ም ካረፈች በኋላ ልጇ ሥጋዋን በዕፀ ሕይወት ሥር በገነት አስቀምጦት፤ በነሐሴ 14 ለሐዋርያት መልሶላቸው ነበር፡፡ እነሱም በጌቴሴማኒ ወስደው ቀብረዋት ተመለሱ፡፡ ልጇ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከሞት ከመቃብር አስነስቶ ነሐሴ 16 ቀን በሰማያዊያን ምሥጋናና ውዳሴ ወደማያልፈው መንግስት አሳርጓታል፡፡

ከሀገረ ስብከቱ በደመና ወደ ኢየሩሳሌም ይመለስ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም አግኝቷት፤ የተገነዘችበትን ሰበን ሰጥታው ወደ ሐዋርያት ወስዶት ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ በቀጣዩ ዓመትም ለቅዱስ ቶማስ የተገለጸ ትንሳኤዋ እንዲገለጽላቸው ሱባኤ ከነሐሴ 1 ጀምሮ ገብተው ልጇ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉም እናቱን አሳይቷቸዋል፡፡

እመቤታችን የሰማያዊት ቤተ መቅደስም ታቦት ናትና (ራዕይ 11÷19) በሰማይ ያለው ቤተ መቅደስ ሲከፈት እነደታየችው ታቦት እሷም በሰማያት ነግሳ ከልጇ ጋር ትኖራለች፡፡ ክቡር ዳዊት “ንግስቲቱ በወርቅ ማለትም በሥጋ በነፍስ በልቦና ንጽሕና አንድም በንጽሐ ቅድስና በንጽሐ ድንግልና ተጐናጽፋ በቀኝህ ትቆማለች” ብሎ ክቡር ዳዊት እንደዘመረላት በፍጥረት ሁሉ እየተመሰነገች በቃልኪዳኗ በምልጃዋ ፍጥረትን እያስማረች ትኖራለች፡፡ ልጇ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛንም በቃልኪዳኗ በአማላጅነቷ ይማረን ይቅር ይበለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር