ካናዳ ማዕከል 19ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ
በማኅበረ ቅዱሳን የካናዳ ማዕከል ፩፱ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ከሐምሌ ፪፰ እስከ ሐምሌ ፴ ቀን ፳፩፭ ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ኦንቴሪዮ ኪችነር ከተማ በሚገኘው የኢ/ኦ/ተ ቤተ ክርስቲያን የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምህረት ውስጥ አካሄደ። የደብሩ አባቶች ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራንና እንዲሁም ከተለያዩ ከተሞች እና ንዑሳን ማዕከላት የመጡ የማኅበሩ አባላት የተሳተፉ ሲሆን እንዲሁም በአካልና በተለያዩ የግል ምክንያቶች መገኘት ሳይችሉ ቀርተው የቨርችዋል መገናኛ ዘዴ በመጠቀም በዙም በገቡ የማኅበሩ አባላትና የዋናው ማዕከል ተወካይን ጨምሮ በተሰባሰቡበት በዚህ ጉባኤ የማዕከሉ አጠቃላይ ሪፖርት በካናዳ ማዕከል ሰብሳቢ በወሮ ልዩ ከቀረበ በኃላ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል:: በውይይቱም ማዕከሉ አጠቃላይ የአገልግሎት ሪፖርቱን ካዳመጠ በኃላ ክፍሎች የሰጣቸውን አገልግሎቶች ተበረታተውና የሰው ሃይል በመጨመር በቀጣዩ ዓመታት የበለጠ በመጠናከር እንዲሰሩ ለማስቻል እጅግ ልዩ ትኩረት ያለባቸው ክፍሎች ላይ ብቻ በጠንካራ ሁኔታ ለመስራት እና ከዕቅድ በታች የሚከናወኑ አገልግሎቶች እንዳይኖሩም በማሰብ አይተኬ ሚና ያላቸውን ክፍላት ብቻ ማስቀጠል ይቻል ዘንድ ምክንያታዊ ነጥቦችን በማስቀመጥ አስፈላጊ ባላቸው በተመረጡ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት በመስጠት ለማገልገል ተስማምቶአል::
ጉባኤው ከዋናው ማዕከል ሪፖርትና መልዕክት በተወካዩ አማካይነት በማድመጥ ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ በተነሱት ሀሳቦችና የመወያያ ነጥቦች ላይም እንዲሁ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎአል:: ከተሰብሳቢዎች ለተነሱት ጥያቄዎችም የሚመለከታቸው ክፍላት ተገቢውን መልስ በመስጠትና መፍትሔ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔውም አካል ሆኖ በሕብረት መሥራት ለተሻለ አገልግሎት መቀላጠፍ የሚረዳ መሆኑንም እግረመንገድ በመጠቆም ጉባኤው አስገንዝቧል::
በመጨረሻም የሥራ አስፈጻሚ በመምረጥ ለተመረጡ የአመራር አባላት ብቻ ኃላፊነቱን ትቶ መለያየት ሳይሆን ገብቶ አብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል:: የደብሩ አስተዳደሪ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ አልዓዛር ተሰማ ጥሪአቸውን አክብረው የመጡትን እንግዶች አመስግነዋል:: እንግዶችም በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልና መስተንግዶ መደሰታቸውን በምስጋና በመግለጽ በጸሎት የተጀመረው መርሐ ግብር በጸሎት ተፈጽሞ በደመቀ የሕብረት መዝሙር በአንድነት በመዘመርና የማስታወሻ ፎቶ በመነሳት የጉባኤው ፍጻሜ ሆኗል::