“ኢየሱስም ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡” ማር 1÷9

“ኢየሱስም ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡” ማር 1÷9

ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድሰት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና ተወልዶ በተወለደ 40 ቀኑ ዕጉለ ርግብ ዘውገ ማዕነቅ ይዞ ወደ ቤተ መቅደስ በመግባት፣በዓመት ሦስት ጊዜ ለበዓል ኢየሩሳሌም በመውጣት ሕግ መጽሐፋዊን ሕግ ጠባያዊን እየፈጸመ “በበህቅ ልህቀ እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝመድሁ እንተ ይእቲ እሙ ” እንዲል ለእናቱ እየታዘዘ አድጎ 30 ዓመት ሲሆነው በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይጠመቅ ዘንድ ወደ ዮርዳኖስ በሄደ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ ወደ ፊት መፍሰሱን ትቶ ሸሽቶ ወደ ኋላ ተመለሰ “አቤቱ ውኆች አዩህ ፣ውኆችም አይተው ፈሩ፤የውኆች ጥልቆች ተነዋወጡ ውኆቻቸውም ጮኹ” (መዝ. 76፥16) ዳግመኛም “ባሕር አየች ሸሸችም ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ”(መዝ 113፥3) ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ገና የሚሸሸውን ውኃ በቃሉ ስልጣን መልሶ አጽንቶታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱስ ዮሐንስን አጥምቀኝ አለው፡፡አጥማቂው መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ሆነ በትንቢት
የአዋጅ ነጋሪ ቃል፣የእግዚአብሔር መንገድ ጠራጊ ተብሎ የተገለጠ ነበር፡፡(ኢሳ 40፥3) ቅዱስ ዮሐንስም “ጌታ ሆይ እኔ በአንተ ልጠመቅ ይገባል እንጂ አንተ በእኔ በባርያህ ልትጠመቅ አይገባህም፡፡ አለ ጌታችንም አሁንስ ፍቀድልኝ እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል” አለው (ማቴ 3÷14) ከዚያም ፈቀደለትና እንግዲያውስ በማን ስም ላጥምቅህ አለው? “አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጸዴቅ፤ወልዱ ለብሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ” እያልክ “አጥምቀኝ” አለው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም “አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጸዴቅ፤ወልዱ ለብሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ” እያለ አጥምቆታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ተጠምቆ ወዲያው ከውኃ በወጣ ጊዜ ሰማያት ተከፈቱ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በጌታችን ራስ ላይ ተቀመጠ፤እነሆም ድምፅ ከሰማያት መጥቶ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ነው እርሱን ስሙት ብሎ ልዩ የሆነች ምሥጢረ ሥላሴን በዮርዳኖስ ገልጾባታል፡፡ ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው አዳምን እና ሔዋንን ከባርነት ነፃ ለማውጣት ነውና በዮርዳኖስ ወንዝ በሰይጣን ተቀብሮ የነበረውን በጥምቀቱ የዕዳ ደብዳቤያቸውን ቀደደላቸው። ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሮታል። ‹‹እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። በእኛ
ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰ።›› (ቆላ 2፥13-14)

በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ለሰው ልጅ ታላቅ ምሥጢር ስለተገለጠ የክርስቶስን ጥምቀት በመዘከር ጌታችን ከገሊላ ተነስቶ ወደ ዮርዳኖስ መጓዙን በማሰብ በጥምቀት ዋዜማ የእግዚአብሔር ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው በምስጋና ወደ ወንዝ ዳር ተጉዘው በድንኳን በማደር ሌሊቱን ስብሐተ እግዚአብሔር ተደርሶ፣ሥርዓተ ቅዳሴው ተፈጽሞ፤በወንዝ ዳር (በተገደበው ውኃ) ጸሎተ አኰቴት ከተደረሰ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል፤ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ያሳየውን ትሕትና ለመመስከርና ከበረከተ ጥምቀት ለመሳተፍ የሚከናወን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር