ካናዳ ማእከል 21ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በኦታዋ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መመሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የካናዳ ማእከል 21ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በኦታዋ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በአካልና በበይነ መረብ ከሐምሌ 25/2017 ዓ.ም ጀምሮ ጉባኤውን እያከናወነ ይገኛል።
በጉባኤው የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ፣አባቶች ካህናት፣ የማኅበሩ አባላት፣ አጋርና ደጋፊ አባላት እንዲሁም የተሳታፊ ልጆች፣ ወጣቶች በብዙ የተገኙበት ሲሆን ከጠቅላላ ጉባኤው በተጨማሪ በልዩ ሁኔታ ለወጣቶችና ለሕጻናት ለብቻ መርሐ ግብር በማዘጋጀት ተተኪ ትውልድን ያሳተፈ ጠቅላላ ጉባኤ ነው።
በጸሎተ ወንጌል የተጀመረው ጉባኤ፣የዋናው ማእከል መልእክት፣ የማእከሉ የ2017 ዓ.ም የዕቅድ ክንውን ዘገባ ቀርቦ ከጉባኤው ተሳታፊዎች ሐሳብ አስተያየት ተሰጥቷል። አሁን በዋና ማእከል ልዑክ በአቶ ታምሩ ለጋ የአባላት አገልግሎት ሥምሪት በተመለከተ ገለጻ ቀርቦ በጉባኤው ሰፊ ውይይት ተከናውኖ የመፍትሔ ሐሳብ ተቀምጧል።
ከወጣቶቹና ከሕጻናት መርሐ ግብር በተወክሉ እኅቶች ስለማኅበረ ቅዱሳን አሳውቁን፣ወጣቶችንና ልጆችን አስተምሩን ምሩን የሚል ጥያቄ ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቧል፡፡ አሁን የተተኪ ትውልድ የአገልግሎት ዳሰሳና የውይይት መነሻ ሐሳብ እየቀረበ ይገኛል፡፡ ጉባኤው እስከ ሐምሌ 27/2017 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል።


