የማኅበረ ቅዱሳን ካናዳ ማእከል 20ኛ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ።
የማኅበረ ቅዱሳን ካናዳ ማእከል 20ኛ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ።
ማኀበረ ቅዱሳን ካናዳ ማእከል 20ኛ ዓመት የምሥረታ እና ጠቅላላ ጉባኤ መርሐ ግብር ከሐምሌ 26-28/2016 ዓ.ም በካልጋሪ አልበርታ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊና የደብረ ምሕረት መድኃኔ ዓለም ወቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ መልአከ ሳህል ቀሲስ አሐዱ፣የካልጋሪ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ቀሲስ ኃይሉ፣የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግዛቸው ሲሳይ፣አባቶች ካህናት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣የማኅበሩ አባላት ተጋባዥ እንግዶች በአካል በተገኙበትና እንዲሁም በተለያየ ምክንያት በአካል መገኘት ያልቻሉ በበይነ መረብ በተሳተፉበት ጠቅላላ ጉባኤው ተካሂዷል፡፡
በጸሎተ ወንጌል የተጀመረው የካናዳ ማእከል 20ኛ ዓመት ምሥረታና ጠቅላላ ጉባኤ የእንኳን አደረሳችሁና የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት (በማእከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር ደረጀ አሸብር) ተላልፏል፤በዓርብና በቅዳሜ መርሐ ግብራት ላይ ስብከተ ወንጌል (በሊቀ ጠበብት ሐረገ ወይን አገዘ እና በቀሲስ ዶ/ር ደረጀ) ተሰጥቷል።
የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ግዛቸው ሲሳይ የዋና ማእከል መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ለሦስት ቀናት በተከናወነው ጉባኤ የማኅበሩን ተቋማዊ ለውጥ ግንዛቤ ማስጨበጫ፤ የቤተ ክርስቲያንና የማኅበራችን አገልግሎት አሁናዊ ሁኔታ ገለጻ አድርገው ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ እንዲሁም የማእከሉ የ2016 ዓ.ም ዕቅድ ክንውን ሪፖርት ቀርቦ ጸድቋል፡፡
በዚህ ጉባኤ የተገኙት ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “በዚህ ዘመን በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን እንደ ማኅበረ ቅዱሳን የሠራ የለም፤ማኅበረ ቅዱሳን ጠንካራ ማኅበር ነው፤እኛ የምንተቸው የምናወጣው የምናወርደው አይደለም፤መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወደው የቤተ ክርስቲያናችን አለኝታ ነው፤በምዕራብ ካናዳ በትጋት እንድትሠሩ እናደርጋለን እኛም አብረን እንሠራለን” ብለዋል፤የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊና የደብረ ምሕረት መድኃኔ ዓለም ወቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ መልአከ ሳህል ቀሲስ አሐዱ እና የካልጋሪ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ቀሲስ ኃይሉ በሀገረ ስብከቱና በአጥቢያዎች ማኅበረ ቅዱሳን ከምዕመናን ጋራ በመሆን ጠንካራ አገልግሎት መፈጸም እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል።
በጠቅላላ ጉባኤው፡-
የካናዳ ማእከል የ20 ዓመት ጉዞውን የሚያሳይ ቪዲዮ በአቶ ሳምሶን መሐሪ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን ብዙዎችን በትዝታ የመለሰና አሁንስ ምን ማድረግ አለብን የሚል መንፈሳዊ ቁጭት ያሳደረ እንደሆነ ከአባላት አስተያየት መረዳት ተችሏል፤በመጀመሪያውና በሁለተኛ የማእከሉ ጠቅላላ ጉባኤ የነበሩት ሊ/ኅሩያን ቀሲስ አልዓዛር እና አቶ ሲሳይ ደስታ በዛሬው 20ኛ ጠቅላላ ጉባኤም በአካል በመገኘታቸው ደስታቸውን ገልጸው፤ እግዚአብሔር በማኅበር ሰብስቦን ፍቅርን መንፈሳዊነትን አስተምሮናል፤በጥቂት አባላትም ሥራ እንድንሠራ አድርጓል፤ወደ ፊትም ፈተናዎችን ተቋቁመን በቤተሰባዊ ፍቅር አገልግሎታችንን ማጠናከር እንደሚገባን አሳስበዋል፡፡
እንዲሁም የ2017 ዓ.ም ስልታዊ ዕቅድ እና ካናዳ ማእከል ሊሠራቸው የታሰቡ የማኅበረ ቅዱሳን የፕሮጀክት ሥራዎች ቀርበው ሐሳብና አስተያየት ተሰጥቶባቸው ጸድቀዋል። በጉባኤው ፍጻሜ እንግዶች ሐሳባቸውን እንደሰጡት በተደረገላቸው አቀባበል በካልጋሪ ያሉ የማኅበሩ አባላትን በማመስገን፤ካልጋሪ ባሉ ጥቂት ወንድሞችና እኅቶች ይህን የመሰለ የተሳካ ጉባኤና መስተንግዶ ማድረጋቸው በመጽሐፍ እንደተማርነውም ራሳችንን ለእግዚአብሔር ከሰጠን በአንድም በሁለትም ሰዎች እግዚብሔር ድንቅ ሥራውን እንደሚሠራ ያየንበት የተማርንበት ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ፤የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊ መልአከ ሳህል ቀሲስ አሐዱ ጥሪያችንን አክበረው በመገኘት የማእከሉን አገልግሎት ለማጠናከር በሰጡት ተስፋ የሚሰጥ
መልእክት፤ጉባኤውም የተሳካ እንዲሆን ላደረጉ የካልጋሪ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የማእከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር ደረጀ አሸብር የላቀ ምስጋና አቀርበው ተሳታፊዎች ሁሉም በአንድነት የኅብረት መዝሙር በመዘመር ጉባኤው በጸሎት ተፈጽሟል::