“የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት”

“የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት”

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የትንሣኤና ዕርገት በዓል አደረሳችሁ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር የኖረችው ስልሣ አራት ዓመት ነው፡፡ ያረፈችው ጥር 21 ቀን ነው፤ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በመደነቅ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ” (ድጓ ዘአስተርእዮ ማርያም) በማለት ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት ገልጿል። ጥር 21 ቀን ጌታችን እልፍ አዕላፋት መላእክትን አስከትሎ መጥቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት እመቤታችንን ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ አሳርፏታል፡፡ በዚህም ዕለት ቅዱሳን ሐዋርያትን በደመና ጠቅሶ ሥጋዋን እንዲቀብሩ አዘዛቸው፤እነሱም ሊቀብሯት ወደ ጌቴ ሴማኒ ይዘዋት በሄዱ ጊዜ አይሁድ  ‹‹ እንደ ልጇ  ‹ ተነሣች፤ ዐረገች ›  እያሉ እንዳያውኩን ኑ ሥጋዋን በእሳት እናቃጥላት ብለው ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ቢጨብጠው የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጣው ከአጎበሩ ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፤በድያለሁ ብሎ በመለመኑ በእመቤታችን ምልጃ እጆቹ ተመልሰውለት እንደነበር ሆኑ፤ ከዚህ በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስንና እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ሐዋርያት ተመልሶ ሲመጣ ሐዋርያት የእመቤታችን የከበረ ሥጋ እንደምን ሆነ አሉት? ከገነት ዕፀ ሕይወት ሥር መኖሩን ነገራቸው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም ቅዱስ ዮሐንስ ያየውን ያዩ ዘንድ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ሁለት ሱባኤ ሲፈጸም ማለትም ነሐሴ 14 ቀን ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ ሥጋ ለሐዋርያት ሰጣቸው እነሱም በታላቅ ዝማሬ ወስደው በጌቴ ሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ ነገር ግን እመቤታችንን ሲቀብሯት ቅዱስ ቶማስ አልነበረምና በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› (መዝ. 131፥8) ብሎ ትንቢት የተናገረው ተፈጽሞ በሦስተኛውም ቀን “ከመ ትንሣኤ ወልዳ” እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ቅዱስ ቶማስም ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ አሁንም የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ብሎ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ሊወድቅ ወደደ እመቤታችን አትዘን ብላው ሌሎች ሐዋርያት ትንሣኤዋንና ዕርገቷን እንዳላዩ ነግራው አንተ አይተሃል ሄደህ ተነሣች ዐረገች ብለህ ንገራቸው ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ልካዋለች፡፡ከዚያም የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ ቢላቸው ቀበርናት አሉት፡፡ እሱም “ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር አይደረግም” አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ መጠራጠር ልማድህ ነው ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንም ብሎ ወደ መካነ መቃብር ሄደው መቃብሩን ቢከፍቱት አጧት ደነገጡ፤ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ ዐርጋለች ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው ሰበኑንም ሰጣቸው ለበረከትም ተካፈሉት በሰበኑም ሕሙማንን ሲፈውሱበት ገቢረ ተአምራት ሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆን በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው ልብስ፤ አባቶች ካህናት የሚጠመጥሙት ሻሽና በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ልብስ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን መምህራን ያስተምራሉ፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም በዓመቱ ቅዱስ ቶማስ ትንሣኤሽንና ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ ብለው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በነሐሴ 16 ቀን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የለመኑትን የማይነሳ ነውና እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ (ረዳት) ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሠናይ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡እመቤታችንን ሐዋርያት በግልጽ እያዩዋት ከጌታችን ጋር በክብር በይባቤና በዝማሬ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህንን መታሰቢያ በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን ምልጃ የሐዋርያት በረከት አይለየን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር!