የቶሮንቶ ንዑስ ማእከል በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልዩ የሕይወት ጉዞ መርሐ ግብር አካሄደ፡፡

የቶሮንቶ ንዑስ ማእከል በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልዩ የሕይወት ጉዞ መርሐ ግብር አካሄደ፡፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ካናዳ ማእከል በቶሮንቶ ንዑስ ማእከል አዘጋጅነት መነሻውን ከቶሮንቶ ደብረ ገነት አቡነ ተክለ ሃይማኖት አድርጎ ወደ ብራምፕተን ቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ተክላ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሕይወት ጉዞ በማድረግ፤ጉዞው ተተኪ ትውልድን ከማነጽና የጋራ ትስስርን ከማጠናከር አንጻር ከኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልምድና ተሞክሮዎች የቀረቡበት ልዩ መርሐ ግብር እንደሆነ ተጠቁሟል።

ከ150 ምእመናን በላይ የተሳተፉበት ይህ መንፈሳዊ ጉዞ ምእመናን ከቶሮንቶ ደብረ ገነት አቡነ ተክለሃይማኖት በመነሣት ወደ ብራምኘተን ቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ተክላ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተካሄደ ጉዞ ነው፤ከመነሻ ጀምሮ በመንገድ ላይ ተሳታፊ ምእመናን በመንፈሳዊ ትምህርት እና በመዝሙር ምስጋና እያቀረቡ ለ1 ሰዓት ተጉዘው ብራምፕተን ቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ተክላ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ በቤተ ክርስቲያኑ አባቶች አቡነ ማርቆስ እና አባ ሚካኤል አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን። አቡነ ማርቆስ ለምእመናኑ እንኳን ወደ እኅት ቤተ ክርስቲያናችሁ በሰላም መጣችሁ ስለመጣችሁ በጣም ደስ ብሎናል ለሁላችሁም የአባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትን ስዕል በስጦታነት አዘጋጅተናል ብለው መርሐ ግብሩን አስጀምረዋል። በመቀጠልም መርሐ ግብሩ በጸሎት ከተከፈተ በኋላ የቁርስ ፕሮግራም ተካሂዷል። ከቁርስ መርሐ ግብር በኋላ ምእመኑን በእድሜ ከፋፍሎ ለማስተማር እንዲያመች በ3 ቡድን (ሕጻናት፣ወጣቶች፣ወላጆች) በማድረግ የቀኑ መርሐ ግብር ተከናውኗል።

የመጀመሪያው ቡድን የአዋቂዎች (ወላጆችን አባት እናት ወንድሞች እኅቶችን) የያዘ ሲሆን በዚህ ቡድን ላይ ምክረ አበው በክርስቲያናዊ የ‍ዕለት ከዕለት አኗኗር እና ክርስቲያናዊ የልጆች አስተዳደግ ላይ ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን እና ከኢትዮዽያ ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር ውይይት ጥያቄ እና መልስ ተካሂዷል። ሁለተኛው ቡድን ወጣቶችንና ታዳጊዎችን የያዘ ነበር (ከ 9 ዓመት እስከ 21 ዓመት) በዚህ ክፍል ላይ ወጣቶች እና
ታዳጊዎች ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆናት ጋር በወጣትነት እና ክርስቲያናዊ ሕይወት ላይ ትምህርት ውይይት እንዲሁም የጥያቄና መልስ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

በ3ተኛው ቡድን ሕጻናት ከ3 አመት እስከ 9/10 ዓመት የተሳተፉበት ሲሆን ሕጻናቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የቅዱስ ዳዊትን ታሪክ የተማሩ ሲሆን መዝሙር ፣ጥያቄና መልስ ፣ቤተ ክርስቲያኒቱ ተተኪ ትውልድን ለማነጽ ሕጻናት ልዩ የማስተማሪያ ዘዴ በመኖሩ ሕጻናት የተለያዩ መንፈሳዊ ጨዋታዎችን እየተጫወቱ ተምረዋል። ከዚያም በጉዞው የተሳተፉት ሁሉ የብራምፕተን ቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ተክላ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካቴድራል የጉብኝት መርሐ ግብር አካሂደዋል። በየመርሐ ግብራት መካከል ዝምሬዎችና መልእክቶች ቀርበዋል፡፡ ስለ ጉባኤው አጠቃላይ ከግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያለውን ትስስርና አንድነትን ብሎም አጠቃላይ መርሐ ግብሩን በተመለከተ ከኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ወጣት አገልጋዮች፣ ከአባቶች ካህናት፣ከወላጆች፣ከወጣቶች በጣም ገንቢ የሆኑ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም የጉባኤው መርሐ ግብር በጸሎት ተዘግቶ ጉዞ ወደ ቶሮንቶ ደብረ ገነት አቡነ ተክለሃይማኖት የተካሔደ ሲሆን በመንገድ ላይ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ካናዳ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤ ስለ ቶሮንቶ ንዑስ ማእከል አገልግሎት በማኅበሩ ወንድሞች እና እኅቶች ገለጻ ተደርጓል፤ከዚያም ምእመናን በመዝሙር እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደ ቶሮንቶ እንደደረሱ፤የጉዞው መርሐ ግብር በቶሮንቶ ደብረ ገነት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በጸሎት ተጠናቋል።