ፍሬውን ለመብላት ሥሩን ውሃ ማጠጣት

/ሊቀ ጠበብት ማኅቶት የሻው/

> ፍሬውን ለመብላት ሥሩን ውሃ ማጠጣት

ይህ በምሳሌነት የቀረበ የአንድ ዕጽ /ዛፍ/ የእድገት ባህርይ ሲሆን ለሚሰጠው ፍሬና ጥቅም እውነተኛ አባባል ነው ። አንድ  ዛፍ አድጎ አንሰራፍቶ ጥሩ ፍሬ አፍርቶ ጥቅም ሊሰጥና ሊበላ የሚችለው ፣ ከምግብነት አልፎ በዛፍነቱም ለአዕዋፋት እና ለእንስሳት መጠለያ መከላከያ ሊሆን የሚችለው ቀጥ ብሎ አድጎ ሲፈለግ ለተለያየ አገልግሎትም እንዳደረጉት የሚሆነው ሥሩ ውሃ ሲጠጣ ነው ሉቃ 13፥8 ። በተጨማሪም የሚስማማውን ማዳበሪያ ፣ ልዩ ልዩ ማዳበሪያ ከሥሩ ሲያስታቅፉት ሲኮተኩቱትና ሲንከባከቡት ጥሩ ዛፍና ጥሩ ፍሬ ይወጣዋል ዮሐ 15፥1። ነገር ግን ችግኙ እንደተተከለ ምንም አይነት እንክብካቤ ካልተደረገለት ላያድግና ፈጽሞ ሊደርቅም ይችላል:: ምናልባት በተፈጥሮው ችግርን ተቋቁሞ ሊያድግ ቢሞክርም ይቀነጭራል እንጅ አያድግም:: ስሙም ዛፍ ሳይሆን ቁጥቋጦ ይባላል:: ቁጥቋጦ ደግሞ ለምንም አይሆንም። የደረሰ ሁሉ እንደፈለገ ይጎነትለዋል ፣ ይቆርጠዋል ረብ የለሽ ይሆናል። እንግዲህ ይሄ ለራሱ ለዛፉ የቀረበ እውነተኛ ታሪኩ ነው ። ምሳሌነቱ ወይም ንጽጽሩ ደግሞ ስለሕፃናት ወይም ስለሰው አስተዳደግ ነው ። ዛፍ ይተከላል ፣ያድጋል፣ይሞታል ለዚህ ነው ሳይንስ ዛፍ ሕይወት አለው እሚለው ። ሰውም ይወለዳል፣ያድጋል፣ይሞታል ክቡር የሆነው የሰው ልጅ በእናቱ ማኅጸን ከተቀረጸ ጀምሮ እንክብካቤ ይፈልጋል። ምክንያቱም በአዕምሮም በአካልም ለማደግ እንክብካቤ በመሆኑ በተለይም ተወልዶ በቋንቋ መናገር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ልክ እንደዛፉ በጥሩ ሁኔታ አድጎ ሰው ለመሆን ሥሩን ውሃ ማጠጣት ነውና ከዛፉ እጅግ በተለየ መልኩ እንክብካቤ ያስፈልገዋል ።

ዛፍ ለራሱ ምግብ ብቻ ነው እሚፈልገው አያስብም ፣አይናገርም ፣አይሠራም ምንም ኃላፊነት የለበትም ሰው ግን ያስባል፣ይናገራል፣ይሠራል በዚህም የተነሳ ነገ ከነገ ወዲያ በሥጋዊም በመንፈሳዊም ህይወት አድጎ ሰው ብቻ ሳይሆን መልካም ሰው ፣ጥሩ ዜጋ፣ ቀና አመለካከት፣ በጥሩ እውቀት የተሞላ ሆኖ  ጥቅሙን ለማየት«ፍሬውን ለመብላት ሥሩን ውሃ ማጠጣት» ተገቢ ነው:: ወላጆች በልጆች አስተዳደግ ሂደት ይህን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው:: ልጆችን የመንግሥተ ሰማይ አርበኞች ፣የክርስቶስ ወታደሮች አድርገን በማሰልጠን በተሰማሩበት ህይወት ያለፍርሃት በፅኑ እምነት የእግዚአብሔርን መንግስት የሚመሰክሩ እንዲሆኑ ካረግናቸው ፍሬውን በላን ማለት ነው::

«ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው መዝ 127፥3» ይህን ውድ ስጦታ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ህይወት ኮትኩቶ ማሳደግ ያስፈልጋል:: በሥጋዊ አስተዳደግ በአሁኑ ሰዓት ብዙ ወላጅ ራሱን ጎድቶም ቢሆን የልጆቹን ፍላጎት ለማሟላት አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል:: ልጆች ግን ይህን ውለታ ያውቁት ይሆን?  በተለይም በውጭው አለም ያለው የልጅ አስተዳደግ ዘይቤ /ሲስተም/ እጅግ የተለየና እንክብካቤውም የበዛ  ከመሆኑም በላይ፣ ልጆችን ጭራሽ ግዴለሽ እንዲሆኑ ሲያደርጋቸውና በፍቅር ፈንታ ለወላጆቻቸው ግድ ከማጣት አልፎም አንዳንዶቹም ጥላቻ ሲያሳድርባቸው ይስተዋላል:: ከዚህም አልፎ ጥቂት ነገር ከጎደለባቸው ወይንም አጥፍቶ ከተቆጡት ለፖሊስ ስለሚደውሉ  ወላጅም ፖሊስ መቶ እኔንም ከሚያሥረኝ ልጄንም ከሚቀማኝ ይልና እንደ አደራ /እንደሌላ ሰው/ ልጅ ተሳቆ አንጀቱ እያረረ የራሱ ልጅ እስከማይመስለው ድረስ ሲያጠፋ ማለትም ተጣሞ ሲያድግ እያየ ዝም ይላል።  እንደ ሀገራችን የዘመናዊ ተማሪ ቆይ 18 አመቴ ይድረስ እያለ ወላጁን ሲያስፈራራ ከመታየት አልፎም ልጆች በውጭው አለም እውነተኛ ምስክሮች ናቸው ተብሎ ይታመናል ። ስለዚህ ወላጅ «ከነገሩ ጦም እደሩ »ብሎ ችግሩ ቀጥሏል። ልጅን ሲያጠፋ እያረቁ፣ ጥሩ ሲሆን እየሳቁ፣ እያስተማሩ፣ እየመከሩ በቁምነገረኛነቱ እየኮሩ እንዲያድግ ማድረግ ነው::  ታዲያ አንድ ወላጅ አጥፍቶ ቢቆጣ ምንድነው ችግሩ ? ጉዳቱ ምን ይሆን? ወላጅ ልጁን እንደሰው ልጅ መሳቀቁ ለምን ? በሥጋዊ ህይወት ማሳደግ ሲባልኮ እንዲወፍርና የማይጠቅም ሥጋ ተሸክሞ እንዲቀጥል ፣ ስለሥጋ ብቻ እያሰበ  እንዲያድግ አይደለም::  ልጅን መቅጣት በጡት እሸት መብላትን በጥቅምት እንዲሉ አድጎ  ብዙ ለሚጠብቀው ነገር ሰዶ ማሳደድ  እንዳይሆን ስለቤተሰብ ፍቅር፣  ስለባህል፣ስለሃይማኖት ፣ስለ ሥነ-ምግባር እንደሙሴ እናት እንደ  ቆስጠንጢኖስ እናት አድርጎ ማሳደግ ያስፈልጋል::

መንፈሳዊ ህይወት

መንፈሳዊ ህይወት ሲባል ብቻውን መንፈሳዊ ህይወት ሳይሆን ሥጋዊ ህይወትን ይዞ  መንፈሳዊነትን መጨመር ማለት ነው፡፡ የዛሬን አያድርገውና ቀደም ሲል አባቶቻችን ንጉሥ ሁነው ካህን ካህን ሁነው ንጉሥ ነበሩ:: ንግሥት ሁነው ዳዊት ደጋሚ ቆራቢ አስቀዳሽ ጸሎተኛ ነበሩ:: በዚህም የተነሳ የተናገሩት ተደማጭነት እያገኘ ሀገርን አኩርተው ወገንን አክብረው በፈራሄ እግዚአብሔር በእዉነት ሲያስተዳድሩ ህዝቡም እጅግ በጣም ያከብራቸው ነበር። ምክንያቱ ደግሞ በሥጋዊም በመንፈሳዊም ህይወት በግብረ ገብ ተኮትኩተው በማደጋቸው ነበር። ይህን ተረት ተረት እሚመስል እውነት እንድናይ ከተፈለገ ዛሬም የሙሴን እናት ዮካብድን የመሰለች እናት ኦ .ዘኁ 26፥29 እንደ እስዋ ያለ እናት ካለች እንደ ሙሴ ያለ ጎበዝና ሃይማኖተኛ በሥጋዊም በመንፈሳዊ የተዋጣለት ጠንካራ ልጅ መውለድ ብቻ ሳይሆን ማሳደግም ይቻላል ፣ ሙሴ እናቱ የነገረችውን እንደጡት እየጠባ በሥጋዊ ሲጠነክር ግብጻዊውን ገሎ ወገኑን ከሞት ሲታደግ በዚሁ አድጎበት በኋላም ፈርኦንን ያህል ኃያል አስፈሪ ንጉሥ ሣይፈራ ወገኖቹን ከባርነት ቀንበር ነጻ አውጥቷል እግዚአብሔርም አግዞታል ።

 • በመንፈሳዊም ሲጠነክር 40 ቀን እና 40 ሌሊት በሲና ተራራ ጹሞ ጸልዮ ለማንም ፍጡር ያልተሰጠ ሽልማት ታቦተ ጽዮንን ከእግዚአብሔር እጅ ተቀብሏል ።
 • የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒም በአሕዛብ እጅ ቁጥጥር ሥር ሁና ልጅ ብትወልድ ልጅዋን ለሃይማኖቱ ስለሀገሩ ስለፈራሄ እግዚአብሔር በሚገባ እያስተማረች አሳድጋዋለች። በሃይማኖት ቆራጥዋ እናት በገባችዉ ብጽዓት መሠረት በአካልም በመንፈስም ጠንክሮ ልጅዋ ለንግሥና ሲደርስላት በእርስዋ አሳሳቢነት ቢሆንም የእናቱን ትእዛዝ የሚቀበለዉ ቆስጠንጢኖስ የፈጣሪዉን የክርስቶስን ዕጸ መስቀል ለ6 ተከታታይ ወራት ቆፍሮ ያወጣ ያገኝ ታላቅ መሪ ነበር። እኛስ ? የኛ ልጆችስ ? እኛማ ሦስት ነገር እንኳን ማስተማር አቅቶናል የራሳችነን ቋንቋ ፣ባህል፣ ሃይማኖት እነዚህን ካስተማርን ሥነ-ምግባሩም በዚሁ ሊመጣ ይችላል ግን ስንቶቻችን ነን በነዚህ ጉዳዮች ከቤተሰባችን ጋር የምንግባባው ? ያልሆነ ምክንያት እየደረደርን ይደጉ ገና ናቸው፣ አናስጨንቃቸውም፣ የሀገሩ ህግ አይፈቅድም ወዘተ በማለት እንቆይና ገና ከፍ ሳይሉ ውሃ በብርጭቆ ቀድተህ አጠጣኝ ተብለው ቢታዘዙ እራስህ ተነስተህ ቀድተህ ጠጣ ሲሉ በዚህ መራገምና እራስን መውቀስ እንጀምራለን:: እንክብካቤ እንደጎደለው ቁጥቋጦ ተንጋዶ ስላደገ የት የተማረውን ያድርግ ቤተሰብ አላስተማረውማ:: እጅ ማስታጠብ፣ታላቅን ማክበር፣እግር ማጠብ አብርሐም ከነዘሩ የተባረከበት ይሄ ሥርዓት ነበር። ስለዚህ ለ8ኛው ሺህ ትውልድ ተጠያቂው የ8ኛው ሺህ ወላጅ ነው ። እስኪ ወገኖቸ ሁላችሁም በዓይነ ህሊናችሁ ወደኋላ ተመልከቱ እንዴት ነበር እናንተ ያደጋችሁት? አንዳንዱ ያልገባዉ ልጅማ እንደእኔ ሁኖ እንዲያድግ አልፈልግም ይላል። እንዲርበው እንዲጠማውኮ አይደለም የነገው ትልቅ ሰውነት የሚለካው ዛሬ ባሳደግንው ልክ ነው:: አንድ ሕጻን  በወላጆቹ፣በአካባቢው ማሕበረሰብ እና በትምህርት ቤት ተቀርጾ ያድጋል፤  ዋናዉ መሠረቱ ግን ቤት ውስጥ ነው:: ትልቁ ፈተናም ልጅ መውለዱ ሳይሆን ማሳደጉ ነው ። ቤተሰብ ትልቅ ተቋም ነው ።

ወላጆች ልጆቻችሁን እንደምትወዱ ምንም ጥርጥር የለውም:: ልጆችስ ወላጆቻችሁን ትወዳላችሁ? መልሱን ለራሳችሁ መልሱ:: በውጭው አለም ያለ ሁሉን ነገር ልመና ነው ብሉ፣ ጠጡ፣ ልበሱ፣ ተማሩ፣ ጎድሎበት ወላጁን በፍቅር የጠየቀው ነገር የለም በፍላጎት ያላደረጋው ነገር ስለሆነ ከላይ እንደተባለው ደንታቢስ ያደርገዋል የወላጅንም ዉለታ ከቁምነገር ካለመቁጠር አልፎም ከራሱ ፍላጎት ዉጭ ከሆነ ማን ውለደኝ ብሎሃል እስከማለት ይደርሳል። በዚህም የተነሳ የዘመኑ ልጆች ከወላጅ ይልቅ ገንዘብን፣ ከሰው ይልቅ ቁስ ነገርን የሚወዱት አሳዳጊ አጫዋቻቸዉ ሞባይል ስለሆነ እምታጎርሰው እናቱን እንኳን ቀና ብሎ ሳያይ እየተለመነ እየጎረሰ ስላደገ አይገነዘበውም:: ታዲያ በዚህ መልኩ ያደገ ልጅ ለየትኛዉ ቤተሰብ ለየትኛዉ አባትና እናቱ ለየትኛዉ እህት ወንድሙ ለየትኛዉ ዘመዱ ነው ፍቅር የሚያድርበት? በውነት እጅግ ያሳስባል፣እንቅልፍ ያሳጣል፣ ጉዳዩ ከባድ ነው::

መፍትሄዉ ምን ይሁን ?

 • ስልክ ይወዳሉ እያልን በር አንክፈት፣
 • እሚያስፈልገዉን ወላጅ ሊመርጥለት ይገባል፣
 • ቋንቋን ፣ባህልን፣ ሃይማኖትን ፣ሥርዓትን ፣ሥራንም ጭምር በአግባቡ ልናስተምራቸው ይገባል። 
 • በተቻለ መጠን ክጥሩ ጓደኛ ጋር እንዲውሉ ማድረግ «፡ከቅን ሰው ጋር ከዋልክ ቅን ትሆናለህ ከጠማማ ጋር ከዋልክ ጠማማ ሁነህ ትገኛለህ » መዝ 18- 25 ፣ አትሳቱ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋዋል 1ኛ ቆሮ 15-33       
 • ለተወሰን ደቂቃም ቢሆን መንፈሳዊነትን ለማስርጽ ከልጆች ጋር መጸለይ፣ ምግብ ሲቀርብ ጸሎት አድርጎ /አባታችን ሆይ/ ብሎ መብላትን ማሳየት
 • ቅዱሳት ሥዕላትን በቤታችን አስቀምጠን መማጸኛ መለመኛ መጸለያ መማለጃ መሆናቸዉን ማስተማር/ በስእሉ ላይ በመንፈስ አድሮ እግዚአብሔር እንደሚሰማን መንገር፣ለሥእሉም ክብር መስጠትና ማሳየት
 • በተገኘው አጋጣሚ ሁልጊዜ ስለቤተ ክርስቲያን መወያየት፣ፍቅሩ እንዲያድርባቸው ተነሱ ብሎ የባህል ልብስን ለባብሶ ቤተ ክርስቲያን ሄደን እንሳለም ማለት ፣መሄድ አይወዱም እያልን አለማመካኘት ፣ ስለመስቀል መሳለም፣ ስለእምነት፣ ስድንግል ማርያም ክብርና አማላጅነት ፣ስለቅዱሳን ክብርና አማላጅነት፣እንዴት ማማተብ እንዳለብን ማሳየት፣ ሙዳየ ምጽዋት ማጠራቅምና መባ መስጠት ማሳየት ፣እንዲያደርጉ ማበረታታት ያስፈልጋል ለዚህ ሁሉ እንግዲህ የግድ ሰባኪ በየቤቱ አያስፈልግም። ቤተሰቡ በየቀኑ ትንሽ ትንሽ መጽሕፍ ቅዱስ በየተራ ማንበብ ፣  አይደለም ለነፍስ ጥቅም ለሥጋም ጥቅም ቢሆን ስንፍናን የምናበረታታ እንጀራ መቁረስ እንኳን የማናስተምር መሆን የለብንም::
 • በዚህ የግንኙነት ሰንሰለት ውስጥ እግዚአብሔር ሕጻናትን እንደሚወድ ማስረዳት እግዚአብሔር ሕጻናትን ይጠብቃልና
 • ሕጻናት ወደኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ማቴ 19፥14
 • ማቴ18፥3 ካልተመለሳችሁ እንደሕጻናትም ካልሆናችሁ ወደመንግሥተ ሰማያት አትገቡም
 • እግዚአብሔር ሕጻናትን አስተዋዮች ያደርጋል መዝ 119፥130
 •  ከሕጻናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዝጋጀህ መዝ8፥2

ማጠቃለያ

በአግባቡ ጊዜና ትኩረት በመስጠት ከያዝናቸው ልጆቻችን መምህሮቻችን ይሆናሉ:: አለባበስንም ሥርዓትንም ሁሉንም ካሳየናቸው በደንብ ያኮሩናል በመንፈሳዊ ህይወት እንዴት እንደምናሳድጋቸው ልዩ ትኩረት መስጠት ግድ ይለናል:: ብንችል በተገኘው አጋጣሚ አስፈላጊውን መሥዋዕትነት እየከፈልን በኦን ላይንም ሆነ በአካል ከፊደል ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲማሩ ማድረግ አለብን:: የአባቶቻችን ማንነት በዚህ የተመሠረተ ነውና ። « ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደሆነ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደተወለዱ ሕጻናት  ተንኮል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ » 1ጴጥ. 2፥2።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር