ደብረ ዘይት
“እነሆ በቶሎ እመጣለሁ፡፡” ራዕይ 22÷12
እኩለጾም ማለትም የዓብይ ጾም አምስተኛ ሳምንት ታላቁ የጌታ በዓል ደብረዘይት ነው፡፡ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ተራራ ማለት ሲሆን በኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ይገኛል፡፡ ደብረዘይት ተራራ በማቴ.24÷1 እንደተገለጸው ደቀ መዛሙርቱ ወደ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበው ስለ መጨረሻው ዘመን የዓለም ፍጻሜ እና ስለመጨረሻው ፍርድ የጠየቁበት ሥፍራ ነው፡፡ የመጨረሻውን ፍርድ መቼ እንደሚሆንና ምልክቶቹም ምን ምን እንደሆኑ እሱም አብራርቶ ነግሯቸዋል፡፡
የመጀመሪያ ምልክት አድርጐ የነገራቸው “እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ብዙዎች ይመጣሉ“ የሚለውን ነው፡፡ በተጨማሪም ብዙዎችን እንደሚያሳስቱአቸው ነግሮአቸዋል፡፡ነገር ግን መፍትሔውንም “እንዳያስቷችሁ ተጠንቀቁ፣ እነሆ በአዳራሽ አለ ወይም በዚህ ወይም በዚያ አለ ቢሉአችሁ አትመኑ“ ብሎም መክሮአቸዋል፡፡ በእነሱ በኩልም እኛን መክሮናል አስተምሮናል፡፡ የጦርነት ዜና፣ የመሬት መናወጥ፣ ረሃብ፣ ቸነፈር፣ በልዩ ልዩ ሥፍራ ይሆናል፡፡ ሕዝብም በሕዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ ይነሳል አለ፡፡ ሕዝብ በራሱ ሕዝብ ወይም በሌላው ሕዝብ ላይ መንግስትም በውስጡ ወይም በሌላ መንግስት ላይ ይነሳል፡፡ እነዚህ መከራዎች የመጀመሪያ ናቸው፡፡
አምላክ ወልደአምላክ ነው ብላችሁ በስሜ በማመናችሁ፤ እናም ክርስቲያን ተብላችሁ በስሜ በመጠራታችሁ ምክንያት በአሕዛብ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ ለሞትም አሳልፈው ይሰጧችኋል፡፡ እስከመጨረሻ ብትጸኑ ትድናላችሁ (ማቴ. 24÷13) ብሎናል፡፡ ዘመናችን በጆሮአችን የሰማናቸውን ምልክቶች በአይናችን ያየንበት ነውና መጨረሻው መድረሱን ያመላክታል፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት ያልፈጸመ የለም፣ ወይም እየተፈጸመ ነው፡፡ ስለዚህም ከማሰናከያ እንድንጠነቀቅ በመከራም እስከመጨረሻው መጽናትን ገንዘብ ማድረግ ይገባል፡፡
ክርስቲያን ሆነው ኖረው ስለክርስቶስ የሚሞቱበት ጊዜም በደጅ ነው፤ ቃሉ እንደተናገረ፡፡ ስለሆነም ወደ አምላካቸው ለመሄድ ፍቅሩ አስቸኩሎአቸው፤ የሞትን የመከራ ጽዋ ደስ ብሎአቸው ሳይሳቀቁ የሚጠጡ ሰማዕታት በሰማያዊት መንግስት ከሁሉ ይከብራሉ፡፡ ዘለዓለማዊ ዋጋቸውንም ከጌታቸው ለመቀበል “አሜን! ጌታ ኢየሱስ ሆይ ፣ ና“ (ራዕይ 22÷20) እያሉ ይጠሩታል፡፡ እሱም ለእያንዳንዱ እንደሥራው ይከፍል ዘንድ ዋጋውን ይዞ ይመጣል፡፡ ከእናቱ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር፤ ከሊቃነ መላእክት ከሠራዊተ መላእክት ጋር፣ ከሐዋርያት ከነቢያት ጋር ይመጣል፡፡ የተወጋበት ጦሩን የተሰቀለበት መስቀሉን፣የተገረፈበት ጅራፉን፣ አክሊለሶኩን ይዞ ይመጣል፡፡ በክበበ ትስብእት በግርማ መለኮት ይመጣል፡፡ በኃይል ከፍ ባለ ክብር ይመጣል፡፡ ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሊቆሙ አይችሉምና እንደሰም ቀልጠው ይጠፋሉ፡፡ ከዚያም በሰማያዊት ኢየሩሳሌም በመንግስት ሰማያት
ይተካሉ፡፡ስለ ሲኦል ፈንታም ገሀነም ይኖራል፡፡ (ራዕይ 24÷1 እና 8)
ድል የነሱ ማለትም በሃይማኖት በምግባር የጸኑ፣ ንስሃ ገብተው ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የተቀበሉ፣ ልብሳቸውን አማናዊ በግ በተባለ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ያጠቡ የተባሉት ናቸው፡፡ እነዚህም በመጨረሻው የፍርድ ቀን በጌታችን በቀኙ ይቆማሉ። ”እናንተ የአባቴ ቡሩካን፣ ዓለም ሳይፈጠር ወደተዘጋጀላችሁ መንግስተ ሰማያት ግቡ፡፡“ ተብለው ሌሊትና ቀን ሳይፈራረቅባቸው፣ ጌታ ራሱ እያበራላቸው በሐሴት በደስታ ይኖራሉ፡፡ እንባቸው ከዓይናቸው ይታበሳል፤ ኀዘን፣ መከራ፣ ሥቃይ፣ ለቅሶ ይወገድላቸዋል። እነርሱም ሕዝብ፤ እርሱም አባትና አምላክ ሆኖአቸው አብረውት ይኖራሉ፡፡
ነገር ግን የማያምኑ፣ የነፍሰገዳዮች፣ የሴሰኞች፣ የአስማተኞች፣ በጣኦት የሚያመልኩ፣ የሐሰተኞች፣(ራዕይ 21÷8) እንዲሁም አውሬ ለተባለው ለዲያብሎስ የተገዙ ወደ እሳት ባህር ይጣላሉ፡፡ በዘለዓለም ሥቃይም ይወድቃሉ፡፡ በሁለተኛው ትንሳኤ ዕድል ፈንታው የዘለዓለም ሕይወት እንዲሆንና ከዘለዓለም ንጉሠ ነገሥታት ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ከባህርይ አባቱ ከአብና ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በሐሴት በደስታ ለመኖር በመጀመሪያው ትንሳኤ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያው ትንሳኤ የተባለው ትንሳኤ ልቡና ወይም ትንሳኤ ሕሊና ይኸውም በንስሃ ከኃጢአት ሞት መነሳት ነው፡፡ በመጀመሪያው ትንሳኤ ያልተነሳ በሁለተኛው ትንሳኤ የመንግስተ ሰማያት ዕድል የለውም፡፡ ስለዚህም በሃይማኖትና በበጐ ምግባር መጽናት፣ ተዘጋጅቶም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል፤ በዚሁም ሁሌ ተዘጋጅቶ መኖር ያስፈልጋል፡፡ “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንደሚመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ “(ማቴ.24÷42)፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር