ኒቆዲሞስ እና አቋሙ
/ተክለ ማርያም/
ኒቆዲሞስ ማለት ቃሉ የግሪክ ሲሆን ድል አድራጊ ወይም አሸናፊ ማለት ነው::
በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን የዓቢይ ፆም ሳምንታት ስያሜ መሠረት ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ ተብሎ ይጠራል:: ይህ ስያሜ የተገኘው በወንጌል ውስጥ ታሪኩ ተፅፎ ከምናገኘው የአይሁድ ጉባኤ ( ሲንሃድርያ ) አባል እና የአይሁድም አለቃ ከነበረው ከኒቆዲሞስ ሲሆን በዮሃንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ታላቅ ምስጢር የሆነውን የእግዚአብሔር መንግስትን እና የልጅነት ጥምቀትን ወይም የዳግም መወለድን ትምህርት በኒቆዲሞስ ጥያቄ ላይ ተመስርቶ ያስተማረበት ነው:: ከዚህ በተጨማሪም በስነመለኮት ምሁራን ቋንቋ የመፅሐፍ ቅዱስ ልብ ተብሎ የሚነገርለት ታላቅ እና ወደር የማይገኝለትን ምሥጢር የተሸከመው የመ/ ቅ ጥቅስ በጌታችን አንደበት የተነገረበት ምዕራፍ ነው::
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”
የዮሐንስ ወንጌል 3፥16
ኒቆዲሞስ የነበረበትን ታላቅ የአይሁድ ስልጣን ትቶ በትህትና ዝቅ ብሎ: ህሊናውን በትክክል አዳምጦ በቅን ልቦና በሌሊት ወደ ጌታ የመምጣቱ አስገራሚ ታሪክ የኒቆዲሞስ ቅፅል ስሙ እስኪመስል ድረስ በተለያየ መልኩ እየተደጋገመ በብዙ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እየተመሰጠረ ሲደነቅ እና ሲነገር ዘመናት ተሻግረዋል:: በየዘመኑ ያለን ክርስቲያኖችም በጨለማ ና በሌሊት ከሚመሰለው እግዚአብሔርን ካለማወቅ ህይወት እና ከዚህ ዓለም ጭንቀት ወጥተን እውነተኛ ብርሃን : እውነተኛ ህይወት እና እውነተኛ መድኃኒት ወደ ሆነው ወደ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገስግሰን እንድንመጣ እና ከእርሱ ከጌታችን ከአንደበቱ የተነገረውን እውነተኛ ድምፅና ትምህርት ወደምንሰማባት ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በትጋት ሆነን የቃሉን ምስጢር እንድናውቅ እና እንድንመረምር እንዲሁም በህይወታችን ከክርስቶስ ጋር ብቻ ሆነን ድምፁን የምንሰማበት የፅሞና ግዜ እንዲኖረን ያስፈልጋል:: ይኸውም በቤተክርስቲያን ውስጥ ከክርስቶስ ጋር አንዲት ሰከንድ መቀመጥ ዘመንን ሁሉ በዓለም ውስጥ በኃጢያተኞች ጉባኤ እየተባበሩ ከመኖር ይልቅ የተሻለ ነው እያልን እንደ መዝሙረኛው ዳዊት እንድንዘምር ያበቃናል::
“ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ።”
መዳዊት 83፤10
ይኽው ሰዎችን እንዳያዩት ሌሊትን ተገን አድርጎ ወደ ክርስቶስ የገሰገሰው የመንፈስ ህፃንነት ላይ የነበረው ትሁቱ ኒቆዲሞስ በመንፈሳዊ ህይወቱ እና እውቀቱ ወደ ሙሉ ሰውነት እያደገ በመሄዱ በምዕራፍ ሰባት ላይ ለፃድቅ ሰው እና ለእውነት የሚከራከር እንዲሁም እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን የማይፈራ : ፊት አይቶ የማያዳላ ባለስልጣን ሆኖ እናገኘዋለን::
በመሆኑም ይህ ታላቅ ሰው ኒቆዲሞስ በምክረ አይሁድ ያልተባበረ የአይሁድ ሸንጎ አለቃ ተብሎ በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል 7 ፤ 50 – 51 ላይ እንደሚከተለው ተጠቅሷል::
” ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ፦ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው።”
ኒቆዲሞስ በዚህ ቆራጥ ውሳኔው ውስጥ ብቻውን በአይሁድ ምክር ቤት ጉባኤ ፊት ቆሞ እግዚአብሔርን ብቻ መፍራት ምን እንደሚመስል ታላቅ ዋጋ ከፍሎ በተግባር አሳይቷል::
ኒቆዲሞስ በአይሁድ አለቃነቱ የስልጣን ወንበር ይዞ የሚሳተፍበት የአይሁድ የበላይ የመወሰኛ ምክር ቤት ( ሲንሃድርያን ) በአይሁዳውያን የፖለቲካ : የሃይማኖት እና የማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሙሉ ስልጣን ያለው ኃያል ጉባኤ ከመሆኑም በተጨማሪ በወቅቱ የእስራኤል ቅኝ ገዥዎች የነበሩት የሮም ቄሳራውያን ከፍተኛ እውቅና እና እገዛ የሚያደርጉለት እና ሮማውያኑ አይሁዳውያንን እንደፈለጉ ለመቆጣጠር የሚጠቀሙበት አሻንጉሊት ጉባኤያቸው ነበር : እናም ኒቆዲሞስ ከዚህ ጉባኤ የተለየ ሃሳብ ይዞ በቁርጠኝነት ለአንድ ድሃ እና ምስኪን ሰው ፍፁም ጥብቅና መቆሙ በእርሱና በቤተሰቦቹ ዘንድ ከመገለል የሚበልጥ ብዙ ነገር ሊደርስበት ይችላል:: ነገር ግን ይህ ለኒቆዲሞስ ህሊናውን ብቻ ተጠቅሞ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝበት የመንፈሳዊ አገልግሎቱ በር ነበር::
የዘመናችንን የክርስትና ህይወት በአንፃረ ኒቆዲሞስ ስንፈትሸው :- ብዙዎች ሲያጨበጭቡ አብሮ አጨብጫቢ እና አስመሳይ መሆንን የተፈጥሮ ባህርይው እኪመስል ድረስ ከሊቅ እስከደቂቅ ያለው አብዛኛው ትውልድ ያለምንም ኃፍረት መንፈሳዊም ይሁን ምድራዊ አቋሙን ለቁጥር በሚያዳግት መልኩ እየቀያየረ በሞቀበት ሲዘፍን እና ሲቀድስ እንዲሁም ምድራዊ ነገር ሲጎድልበት ደግሞ ሲራገም እና ሲያምፅ የሚኖርበትን የኑሮ ዘይቤ በመምረጡ የእግዚአብሔር ክብር እርቆት ይገኛል::
ኒቆዲሞስ ግን ለተጎዱ በመቆሙ እና እውነት በመናገሩ ያስከፍለኛል ብሎ ስለሚገምተው ነገ ር ፈፅሞ አላሰበም: ይልቅስ ህሊናውን በትክክል ተጠቀመ:: እኛስ የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔር መንግስት ስለ እውነት ( የክርስቶስ ተከታይ ከመሆናችን የተነሳ ) በዚህ ዓለም ህይወታችን የደረሰብን አንዳች ምድራዊ ጉዳት አለ ወይ ? ወይስ በህይወታችን ውስጥ ትዝ የሚለን ስለክርስቶስ ስንል ያጣነው ወይም የጎደለብን ወይም ዋጋ ያስከፈለን አጋጣሚ አለን ወይ ? ይህ በህይወታችን ከጠፋ የክርስቶስ ተከታይነታችን ስጋት ላይ መውደቁን ልብ እንበል:: ምናልባትም አውቀንም ይሁን ሳናውቀው የክርስቶስ ተከታይነት ሳይሆን የአጨብጫቢነት ህይወት ላይ ሆነን እንዳይሆን እራሳችንን ልንፈትሽ ያስፈልጋል::
በጨረሻም ኒቆዲሞስ እግዚአብሔር ለታላቅ አገልግሎት መርጦት በዮሐንስ ወንጌል 19 : 39 እንዲህ ተፅፎለታል
” ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ።”
ይኸው የኒቆዲሞስ ፍፃሜው የሚገርም ነው:: የመከራ እና የአላዋቂነት ምሳሌ በሆነችው በሌለበት በጨለማ ተነስቶ ወደ እውነተኛ ብርሃን እና ወደ እውነተኛ እውቀት ወደ ክርስቶስ የሮጠው ኒቆዲሞስ አሁንም በለሊት እና በጨለማ የተመሰለችው ሁሉም ተሰናክለው ፈርተው ጥለውና ሸሽተው በጠፉባት የመከራ እና የጭንቅ ሰዓት ላይ ማንም ደፍሮ የማያደርገውን ያውም ከገዳዮች እና ከሰቃዮች ጋር በሃገር በስልጣን እና በዝምድናም አንድ ሆኖ ሳለ እርሱ ግን ግዜ ቀንቷቸው ስልጣን ተደላድሎላቸው የድሃውን ደም ማንም ከቁብ አይቆጥረውም ብለው በድፍረት ግፍ ከሚፈፅሙት ጨካኞች የስጋ ወገኖቹ እና የስልጣን አጋሮቹ ጋር ህብረት ሳይፈጥር ይልቅስ እጅግ ድንቅ የሆነውን የወልደ አብ የወልደ ማርያምን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮት ያልተለየውን አስከሬን የቀብር ስነስርዓት በመፈፀሙ ከሞት በኃላም ቢሆን ከእውነት ጋር እቆማለው ብሎ እስከ ጥግ ድረስ በመጓዝ ምድራዊ ስልጣኑን እና ማንነቱን ንቆ ለእግዚአብሔር መንግስት ሰማዕት እንበለ ደም ሆኗል:: እኛም በቀረው ዘመናችን ሁሉ ለእውነት በመመስከር እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ማንነትን ይዘን እስከፍፃሜው እንድንጓዝ እና የመንግስቱ ወራሾች እንድንሆን አምላከ ቅዱሳን ይርዳን::
ወስብሃት ለእግዚአብሔር