“ይህች ዕለት ቅድስት ናት” (ቅዱስ ያሬድ)

በዲ/ን አሰበልኝ ጨቡድ

የተወደዳችሁ አንባቢያን በሙሉ እንኳን ለዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት (ቅድስት) አደረሳችሁ፡፡ ስለ ቅድስት ስናነሳ ‹‹ቅድስት››ማለት ዘይቤያዊ ፍችው ‹‹የተቀደሰች የተለየች የከበረች›› ማለት ነው፡፡ ምሥጢራዊ መልእክቱ ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ከቆመ ሳያርፍ ከዘረጋ ሳያጥፍ ዐርባ መዓልት ዐርባ ሌሊት የጾመውን ጾም የጀመረባት ክብርትና ልዩ የሆነች እለት በመሆኗ በቅዱስ ያሬድ ስያሜ ቅድስት ተብላለች፡፡ (ማቴ. 4፥2)

በዚህም ዕለት ስለ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፡፡ “ዛቲ ዕለት ቅድስት ይእቲ” ይህች ዕለት ቅድስት ናት፡፡ ”ሰንበትየ ቅድስትየ እንተ አዕረፍኩ እምኩሉ ግብርየ ይቤ እግዚአብሔር” ፍጥረታትን ፈጥሬ ያረፍኩባት ቅድስት ሰንበት ናት ይላል እግዚአብሔር፡፡“ሰንበት ቅድስት ለውሉደ ሰብእ መድኃኒት” የከበረች ሰንበት ለሰው ልጆች መድኃኒት ናት፤ለሰው ልጆች ድኅነት የተፈጸመባት ትንሣኤ የተሰበከባት ናት፡፡ የሰንበት ጌታዋ እግዚአብሔር ነውና ድኅነት ሥጋዊ ድኅነት መንፈሳዊ ይገኝባታል፡፡ ሰንበት ቅድስት እንደሆነች በኦሪት ከሥራየ ያረፍኩባት ብሎ፤በሐዲስ ደግሞ ለሰው ልጅ መድኃኒት /ትንሣኤ/ ያደረኩባት ብሎ ሰንበትን እንዳከበራት ያስረዳናል፡፡ ሰንበትን አከበራት ስንል ሌሎች ዕለታት የከበሩ አይደሉም ለማለት ሳይሆን ከአንስተ ዓለም እመቤታችንን እንደመረጠ፤ ከሰውም መርጦ ለክህነት እንደሚሾም፤ሰንበትንም ከዕለታት መርጦ ቀደሳት አከበራት፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስ እንደሆነ የፈጠረው ሰው ቅድስናን መያዝ እንዳለበትም የሚያስገነዝብ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰማያትን ሠራ፤ ምስጋናና ውበት በፊቱ፣ቅድስናና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡ (መዝ 95፥5) እንዳለን መቅደሱ የተባለ የሰው ልጅ መሆኑንም መርሳት የለብንም፡፡ “ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቅምን?… ስለዚህ ሥጋችሁን አክብሩት፡፡” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (1ቆሮ 6፥19)

መጠን በሌለው ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን ፤ ለውርደት ሳይሆን ለክብር፤ ለርኩሰት ሳይሆን ለቅድስና፤ ለሞት ሳይሆን ለሕይወት ነው፡፡የመፈጠራችንም ዓላማ በፊቱ በፍጹም ምግባርና ሃይማኖት በመመላለስ ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው፡፡ብርሃን ከጨለማ ጽድቅ ከኃጢአት ጋር ኅብረት የለውምና ከእርሱ ጋር ለዘላለም ነግሠን ለመኖር በቅድስና መኖር ይጠበቅብናል፡፡ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኩሰት አልጠራንም›› ያለንም ለዚህ ነው፡፡(1ተሰ 4፥7) እግዚአብሔር ቅዱስ በመሆኑ የተቀደሰ ነገር ያስፈልገዋልና ሰው ሁሉ በቅድስና መንገድ በመመላለስ የክብሩ ባለቤት የመንግስቱ ወራሽ እንዲሆን እግዚአብሔር እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ በማለት አስተምሮናል፡፡(ዘሌ11፥45፤1ኛጴጥ1፥15) ሰውም፣መላእክትም፣ቦታም፣ ዕለትም ለእግዚአብሔር በእግዚአብሔር ተቀድሰዋል፡፡ ቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ሰዎች የእግዚአብሔርን ቅድስና ተረድተው እግዚአብሔርን በማመስገን ሲተጉ ቅዱሳት ቦታዎች እና ዕለታት የቅዱሳኑ ነገር ሲታሰብባቸው ፤ ጸሎት ሲደርስባቸው እና ለእግዚአብሔር እና እግዚአብሔር ለቀደሳቸው ቅዱሳን ስም መጠሪያ ሆነው ሲያገለግሉ ይኖራሉ፡፡ እኛም ዕለት ዕለት መልካም በማድረግ ቤተ መቅደስ ተብሎ የተነገረለትን ሰውነታችንን በመጠበቅ በልባችን አምነን በአፋችን መስክረን እግዚአብሔር እንደቀደሰን እና ልጅነትን እንደሰጠን በማመን በተቀደሰ ሕይወት መኖር ይገባናል፡፡ ስለዚህ ይህች ዕለት ቅድስት እንደሆነች ሁሉ ሁላችንም በሕይወታችን ሁሉ የምግባርና የሃይማኖት ፍሬ አፍርተን በመገኘት በተሰማራንበት የሥራ መስክ ፣ በማኅበራዊ ኑሮአችን ሁሉ እግዚአብሔርን በማክበር ራሳችንን ለቅድስና ልንለይ ይገባናል፡፡ ከኃጢአት ርቀን ሥጋዊ ምኞታችንን ገትተን አሮጌው ሰውነታችንን አስወግደን ንስሐ ገብተን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን በቅድስና እንድንኖር ያስፈልጋልና የባሕርይ አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር በቅድስና እንድንኖር ይርዳን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር