ፍልሰታ ለማርያም እና ሱባኤ
ፍልሰት ማለት ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ መወሰድ ማለት ነው፡፡ ፍልሰታ ለማርያም የሚለው አጠራርም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ከዚህኛው ዓለም ወደ ዘለዓለማዊው ዓለም በልጇ በወዳጇ በኢየሱስ ክርስቶስ መወሰድን የሚያስረዳ ነው፡፡
እመቤታችን በዚህ ዓለም ለ64 ዓመታት ከኖረች በኋላ ልጇ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በአካለ ነፍስ ወደራሱ ሊወስዳት እንደሆነ ቢነግራት፤ እሷ ግን “ልጄ ወዳጄ ሆይ የሰማይ የምድር ፈጣሪ የአንተ እናት ሆኜ ይህ እንዴት ይሆናል”? አለችው፡፡ እሱም በርካታ ነፍሳት በአንድ ቀን ተኮንነው ወደ ሲኦል ሲወርዱ አሳይቷት ምልጃዋ እንደሚያስፈልጋቸው ቢያስረዳት ተቀብላ ጥር 21 ቀን ዓ.ም ሞትን ቀምሳለች፡፡ (ነገረ ማርያም); “ንግስቲቱ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ በቀኝህ ትቆማለች”; (መዝ.44÷9) እንዳለ ክቡር ዳዊት፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንግስት የሆነች የንጉስ ሰማይ ወምድር የኢየሱስ ክርስቶስ እናት በሥጋ በነፍስ ንጽሕና ቅድስና ተጐናጽፋ በልጇ ቀኝ ለመኖር ሞትን (የነፍስን ከሥጋ መለየትን )አይታለች፡፡
ይህም በጣርና በጭንቀት ሳይሆን በደስታና በሐሴት መሆኑን ለመረዳ “ሰላም ለፀዐተ ነፍስኪ እንበለ ፃዕር ወፃማ፤ ለነቢር ዘልፈ በየማነ ወልድኪ ፌማ፤” ; ያለውን ከመልክዐ ማርያም ማየት ይቻላል፡፡ ትርጓሜውም ;”እመቤቴ ሆይ፣ በልጅሽ ቀኝ ለዘለዓለም ለመኖር ያለጭንቀት ያለህመም ለሆነው ለክብርት ነፍስሽ ከሥጋሽ መለየት እጅ እነሳለሁ”; ማለት ነው፡፡
ከዚህ በኋላ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለመቅበር ሐዋርያት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሲሄዱ ልጇ ከተቀበረ በኋላ ተነስቷል ያሉ ደቀመዛሙርቱ እናቱንም ነገ ተነሳች እንዳይሉን ሥጋዋን እናቃጥለው የሚሉ አይሁድ ታውፋንያ የተባለውን ሰው ላኩ፡፡ እሱም ለማቃጠል አልጋዋን በእጁ ሲይዝ በመልአክ ሰይፍ ቢቀጣም፣ በምልጃዋ እጁ ተመልሶለታል፡፡ የከበረ ሥጋዋም ወደ ገነት ተወስዶ ልጇ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወት ዛፍ ሥር አሳርፏታል፡፡ ;”የብርሃን
ድንኳኖች ወደተተከሉበት የገነት ማዕከል ለተደረገው የሥጋሽ ፍልሰት ሰላም እላለሁ”; እንዲል፡፡ ከሐዋርያት መካከልም ቅዱስ ዮሐንስ እየተነጠቀ ሄዶ ሥጋዋል አጥኖ ይመለስ ነበር፡፡
የፍልሰታ ለማርያም ሱባኤም የተጀመረው ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ሱባኤ ማለት ሰባት ማድረግ ማለት ነው። ሰባት ፍጹም ቁጥር እንደመሆኑ ሱባኤም ወደ እግዚአብሔር ፍጹም ልመና የሚቀርብበት ጾምና ጸሎት እንዲሁም ራስን በትህትና አዋርዶ፣ ቢቻል በአንድ ቦታ ተወስኖ የመማጸን ሥርዓት ነው፡፡ ሐዋርያትም ዮሐንስ ያያትን የድንግል ማርያም የከበረች ስጋ ለማየት እንዲችሉ ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ ሱባኤ ገብተው ተማጸኑ። በሁለተኛው ሱባኤ ማለትም ነሐሴ 14 ቀን እግዚአብሔር ልመናቸውን ተቀብሎ መላእክት ሥጋዋን መለሱላቸው፡፡ እነርሱም በጌቴ ሴማኒ ቀብሯት፡፡
ቀጣዩ ትምህርት ለጊዜው ይቆየንና እኛም ከሐዋርያት በተማርነው፤ በፍጹም ትህትና፣ በፍቅር፣ የተጣላነውን ታርቀን፣ የቀማነውን መልሰን፣ ንስሃ ገብተን ጸንተን በዚች ሱባኤ ብንጠቀም፣ ለኃጢአታችን ሥርየት፣ ለጥያቄአችን ምላሽ እናገኛለን፡፡ የሱባኤውን ጊዜም ከጸብ ከክርክር፣ከክፉ ተግባር ርቀን ብንችል በአንድ ቦታ ተወስነን፣ ከንግግራችንም ተቆጥበን፣ በጾም በጸሎት፣በሥግደት፣ ተዘጋችተንም ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደሙን በመቀበል ብናሳልፍ ልመናችን ፈጥኖ ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል፣ መልስም እናገኛለን፡፡ (ዳን9÷3)
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃዋና ቃልኪዳኗ አይለየን፡፡
ወስብሀት ለእግዚአብሔር