“ኢየሱስም ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡” ማር 1÷9

“ኢየሱስም ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡” ማር 1÷9

ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድሰት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና ተወልዶ በተወለደ 40 ቀኑ ዕጉለ ርግብ ዘውገ ማዕነቅ ይዞ ወደ ቤተ መቅደስ በመግባት፣በዓመት ሦስት ጊዜ ለበዓል ኢየሩሳሌም በመውጣት ሕግ መጽሐፋዊን ሕግ ጠባያዊን እየፈጸመ “በበህቅ ልህቀ እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝመድሁ እንተ ይእቲ እሙ ” እንዲል ለእናቱ እየታዘዘ አድጎ 30 ዓመት ሲሆነው በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይጠመቅ ዘንድ ወደ ዮርዳኖስ በሄደ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ ወደ ፊት መፍሰሱን ትቶ ሸሽቶ ወደ ኋላ ተመለሰ “አቤቱ ውኆች አዩህ ፣ውኆችም አይተው ፈሩ፤የውኆች ጥልቆች ተነዋወጡ ውኆቻቸውም ጮኹ” (መዝ. 76፥16) ዳግመኛም “ባሕር አየች ሸሸችም ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ”(መዝ 113፥3) ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ገና የሚሸሸውን ውኃ በቃሉ ስልጣን መልሶ አጽንቶታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱስ ዮሐንስን አጥምቀኝ አለው፡፡አጥማቂው መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ሆነ በትንቢት
የአዋጅ ነጋሪ ቃል፣የእግዚአብሔር መንገድ ጠራጊ ተብሎ የተገለጠ ነበር፡፡(ኢሳ 40፥3) ቅዱስ ዮሐንስም “ጌታ ሆይ እኔ በአንተ ልጠመቅ ይገባል እንጂ አንተ በእኔ በባርያህ ልትጠመቅ አይገባህም፡፡ አለ ጌታችንም አሁንስ ፍቀድልኝ እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል” አለው (ማቴ 3÷14) ከዚያም ፈቀደለትና እንግዲያውስ በማን ስም ላጥምቅህ አለው? “አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጸዴቅ፤ወልዱ ለብሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ” እያልክ “አጥምቀኝ” አለው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም “አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጸዴቅ፤ወልዱ ለብሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ” እያለ አጥምቆታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ተጠምቆ ወዲያው ከውኃ በወጣ ጊዜ ሰማያት ተከፈቱ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በጌታችን ራስ ላይ ተቀመጠ፤እነሆም ድምፅ ከሰማያት መጥቶ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ነው እርሱን ስሙት ብሎ ልዩ የሆነች ምሥጢረ ሥላሴን በዮርዳኖስ ገልጾባታል፡፡ ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው አዳምን እና ሔዋንን ከባርነት ነፃ ለማውጣት ነውና በዮርዳኖስ ወንዝ በሰይጣን ተቀብሮ የነበረውን በጥምቀቱ የዕዳ ደብዳቤያቸውን ቀደደላቸው። ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሮታል። ‹‹እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። በእኛ
ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰ።›› (ቆላ 2፥13-14)

በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ለሰው ልጅ ታላቅ ምሥጢር ስለተገለጠ የክርስቶስን ጥምቀት በመዘከር ጌታችን ከገሊላ ተነስቶ ወደ ዮርዳኖስ መጓዙን በማሰብ በጥምቀት ዋዜማ የእግዚአብሔር ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው በምስጋና ወደ ወንዝ ዳር ተጉዘው በድንኳን በማደር ሌሊቱን ስብሐተ እግዚአብሔር ተደርሶ፣ሥርዓተ ቅዳሴው ተፈጽሞ፤በወንዝ ዳር (በተገደበው ውኃ) ጸሎተ አኰቴት ከተደረሰ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል፤ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ያሳየውን ትሕትና ለመመስከርና ከበረከተ ጥምቀት ለመሳተፍ የሚከናወን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ!

እንኳን ለመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

እንኳን ለመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ቀን የመላእክት አለቃ የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። እርሱም በባቢሎን አገር ከነደደ እሳት ውስጥ በጨመሯቸው ጊዜ አናንያን አዛርያን ሚሳኤልን ያዳናቸው ነው።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአማልጅነቱ ይማረን ለዘለዓለሙ አሜን።

አርኬ
ሰላም ዕብል ኪያከ ክቡረ፤
ለስመ ዚአከ ገብርኤል እንዘ አነሥእ መዝሙረ፤
እግዚአብሔር መንበሮ ሰማየ ሰማያት ዘገብረ፤
ይትመሰል በአርአያከ አመ ጊዜ ሐወጸ ምድረ፤
እምነ መላእክት ኵሉ ስነከ አፍቀረ።

ስንክሳር ዘወርኃ ታኅሣሥ

(ሙሉ ታሪኩን ትንቢተ ዳንኤል 3፥1-ፍጻሜው ያንብቡ)

“መላእክት ዘወትር ምግብሽን እያመጡ፤በቤተ መቅደስ ኖርሽ” አንቀጸ ብርሃን

“መላእክት ዘወትር ምግብሽን እያመጡ፤በቤተ መቅደስ ኖርሽ” አንቀጸ ብርሃን

የእመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ መግባት

ኢያቄምና ሐና የሚባሉ በተቀደሰ ትዳር የሚኖሩ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም ፤ ሐናና ኢያቄም ልጅ ስለሌላቸው ያዝኑ ነበር፤ሁልጊዜም ወደ ቤተ እግዚአብሔር እየሄዱ እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ልመና ያቀርቡ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሲሄዱ ሐና “ርግቦች ከልጆቻቸቸው ጋር ሲጫወቱ” አየች ለእነዚህ አዕዋፋት ልጆች የሰጠህ ምነው እኔን ልጅ ነሳኸኝ? ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፡፡ ኋላም ከቤተ እግዚአብሔር ደርሰው ወንድ ልጅ ብትሰጠን አርሶ፣ቆፍሮ፣ወጥቶ ወርዶ፣ነግዶ ይርዳን አንልም፤ለቤት እግዚአብሔር አንጣፊ፣መጋረጃ ጋራጅ ይሆን ዘንድ እንሰጣለን፤ሴት ብትሰጠን ውኃ ቀድታ እንጨት ለቅማ ትርዳን አንልም፤ለቤተ እግዚአብሔር ማይ ቀድታ፣መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣መጋረጃ ፈትላ እንድታገለግል እንሰጣለን ብለው ተሳሉ፡፡ እግዚአብሔርም የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ኀዘናቸውንና ልመናቸውን ሰማ ልጅንም ሰጣቸው፡፡ ሐናም በፈቃደ አምላክ ነሐሴ ሰባት ቀን ጸንሳ በግንቦት አንድ ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደች፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት ሲሆናት፤ሐና ኢያቄምን በስለት ያገኘናት ልጃችን አፏ እህል ሳይለምድ ሆዷ ዘመድ ሳይወድ ለቤተ እግዚአብሔር እንስጥ? አለችው፡፡ እርሱም ፍቅርሽ ይወጣልሽ እንደሆነ ብየ ነው እንጂ ብሏት ይሁን ይሁን ተባብለው በተሳሉት ስለት መሠረት ልጃቸውን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፡፡ በቤተ መቅደስ የካህናት አለቃ የነበረው ካህኑ ዘካርያስ ተቀበላቸው፡፡ ሐና እና ኢያቄም ለእግዚአብሔር የገቡትን ቃል የተደረገላቸውንም ድንቅ ተአምር ነገሩት፡፡ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስም የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ እያደነቀ ሳለ አንድ ነገር አሳሰበው የሦስት ዓመት ብላቴና ምን እናበላታለን? ምን እናጠጣታለን? ብሎ ከካህናቱ ጋር ሲያወጡ ሲያወርዱ ወዲያው ከሰማይ መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ ይዞ ረቦ ታየ፡፡

ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ለእርሱ የወረደ መስሎት ቢነሣ ወደ ላይ ራቀበት፤ከካህናቱም ቢነሡ ራቀባቸው፤ሐናና ኢያቄምም ቢነሱ ራቀባቸው፤ሐናን ምናልባት ለዚህች ብላቴና የመጣ እነደሆነ እስቲ ፈቀቅ በይ አሏት፡፡ ትታት ፈቀቅ ብትል እመቤታችን ወደ እናቷ ድንኩል ድንኩል እያለች ስትሄድ መልአኩ ወርዶ እመቤታችንን በሰው ቁመት ያክል ከፍ አድርጎ አንድ ክንፉን አንጥፎ በአንድ ክንፉ ጋርዶ ኅብስቱን መግቧት ጽዋውን አጠጥቷት ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ “ወሶቤሃ ወረደ ፋኑኤል ሊቀ መላእክት ወጸለላ በአክናፊሁ ወተለዐለ ላዕለ መጠነ ቆመ ብእሲ ወወሀባ ወመጠዋ ወዐርገ ውስተ ሰማይ” እንዲል

ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስና ሕዝቡም እግዚአብሔር ምግቧን እና መጠጧን እንዳዘጋጀላት ተመለከቱ፡፡ ከዚያም ካህኑ ዘካርያስ የምግቧ ነገር ከተያዘልንማ ከሰው ጋር መኖር ምን ያደርግላታል ብሎ በፍጹም ደስታ እመቤታችንን ተቀብሎ ታኅሣሥ ሦስት ቀን በሦስት ዓመቷ ወደ ቤተ መቅደስ አስገባት ይህም ዕለት በዓታ ለማርያም ተብሎ በድምቀት ይከበራል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት መነጽር ንጽሕናዋን ቅድስናዋን አይቶ እግዚአብሔር ለእናትነት እንደመረጣት ተመልክቶ እንዳመሰገነ “ልጄ ሆይ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፣ወገንሽን የአባትሽንም ቤት እርሽ፣ ንጉሥ ውበትሽን ወዷልና፣እርሱ ጌታሽ ነው” መዝ 44÷10 ያለው ተፈጽሞ “በእግዚአብሔር ሥዕል የተሣሉ ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ እንቺ ነሽ” የተባለች መቅደስ እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ ገብታ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረች፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘእሑድ) መላእክት እየጎበኟት ምግቧን እያመጡ ዐሥራ ሁለት ዓመታትን በቤተ መቅደስ ስለመቆየቷ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን እንዲህ ብሎ ገልጿል “ከንጹሓን ይልቅ ንጽሕት የሆንሽ አንቺ ነሽ፤ ከማይነቅዝ ዕንጨት እንደተሠራ በወርቅ
እንደተጌጠና ዋጋው ብዙ በሆነ በሚያበራ ዕንቊ እንደተለበጠ ታቦት በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖርሽ የተመረጥሽ ድንግል ነሽ፤ እንዲህ ሆነሽ በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ፤ መላእክት ዘወትር ምግብሽን ያመጡ ነበር፤ መላእክት እየጎበኙሽ እንዲህ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖርሽ፤ መጠጥሽም የሕይወት መጠጥ ነበር፤ ምግብሽም የሰማይ ኅብስት ነበር፡፡” ብሏል አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው ስለጽንሰቷ ፣ መላእክት እየጎበኟት እየመገቧት በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ ስለመኖሯ እንዲህ ብሎ አመስግኗታል፡፡

“ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም፤በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጅ፤ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ፤ ድንግል ሆይ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ኅብስትን ነው እንጂ፤ ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ፤ ድንግል ሆይ ከአንቺ አስቀድሞ ከአንቺም በኋላ እንዳሉ ሴቶች መተዳደፍን የምታውቂ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና ያጌጥሽ ነሽ እንጂ፤ ድንግል ሆይ የሚያታልሉ ጐልማሶች ያረጋጉሽ አይደለም የሰማይ መላእክት ጎበኙሽ እንጂ እንደተነገረ ካህናትና የካህናት አለቆች አመሰገኑሽ እንጂ”

እመቤታችንን አመስግነን ንጽሕናዋን ተጎናጽፈን በቅድስና እንድንኖር የእግዚአብሔር ቸርነት የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ አይለየን።

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

“ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፡፡” መዝ 59÷4

“ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፡፡” መዝ 59÷4


✞  እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ✞

እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ በአርአያውና በምሳሌው አክብሮ የፈጠረው ፍጥረት ሰው ነው፡፡ ነገር ግን “ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ እንደ አላዋቂ ሆነ” ብሎ ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረው (መዝ 48 ÷12) ሰው ነጻነቱንና ታላቅነቱን ባለማወቁ ትዕዛዘ እግዚአብሔርን ጥሶ ሕጉን በማፍረሱ የሞት ሞት አገኘው፡፡ ኋላም እግዚአብሔር ሰውን ከሞት ያድነው ዘንድ እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኖ በዮርዳኖስ ተጠምቆ በቀራንዮ አደባባይ በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ ሞትን በሞቱ ገድሎ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን አጥፍቶ ሕይወትን ሰጥቶናል፡፡ በመስቀሉ ጥልን ገደለ እንዳለ፡፡ ኤፌ 2÷16

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሰቀሉት አይሁድ ምንም በደል የሌለበትን ሰቅለው ገደሉት ይሉናል በማለት የጌታችን ክቡር አካሉ ያረፈበት፣ እጆቹና እግሮቹ የተቸነከሩበት፣ ጎኑ በጦር ተወግቶ ደሙ የፈሰሰበትን ቅዱስ መስቀል ክርስቲያኖች እየተሳለሙና እየዳሰሱ በተአምራት እንዳይድኑበት መስቀሉን ጉድጓድ ቆፍረው ቀብረውታል፡፡ ይህ ቅዱስ መስቀል ተቀብሮ ሦስት መቶ ዓመት ቢያስቆጥርም ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ “የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለምና” እንዳለ (ማቴ 10÷26) እግዚአብሔር በጥበቡ የተሰወረው ተገልጦ እንዲወጣ ፈቃዱ በመሆኑ ቅድስት እሌኒንና ልጇ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን መስቀሉን እንዲፈልጉ አድርጎ አስነሣቸው፡፡ ቅድሰት እሌኒም መስቀሉን ፍለጋ ከሮም ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች፤ ልጇ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም የመስቀሉን ኃይልና አሸናፊነት በሰማይ ሰሌዳ በብርሃን ተቀርጾ ስላዬ ለእናቱ አስፈላጊውን ሁሉ አግዟታል፡፡ እሷም የመስቀሉን ነገር ስትመረምር ኪራኮስ የተባለ አረጋዊ መስቀሉ “ከሦስቱ ተራራዎች በአንዱ እንዳለ ይነገራል” ብሏታል

እርሷም ሱባኤ ብትገባ መልአከ እግዚአብሔር እያመለከታት ካህናትን ጠርታ ጸሎት አድርሰው ሕዝቡን ደመራ አሰብስባ ጸሎተ ዕጣን የተጸለየበትን ዕጣን በመጨመር ደመራው በእሳት ሲለኮስ የደመራው ጢስ (የዕጣኑ ጢስ) መስቀሉ ያለበትን ተራራ መስከረም ዐሥራ ስድስት ቀን አመላክቷታል፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ዳዊት “ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፡፡” ያለው፡፡ እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸው በመፍራት ለሚያመሰግኑት ኃይሉን በማመን በፍጹም ልብ ለሚፈልጉት ምልክትን እንደሚያሳይ የመስቀሉ ነገር ታላቅ ምስክር ነው፡፡

ቅድሰት ንግሥት እሌኒ ምልክቱን ኳየች በኋላ በተራራው የተቀበረውን መስቀል ለማስወጣት መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ማስቆፈር ጀምራ መጋቢት ዐሥር ቀን እንደ ፀሐይ የሚያበራው ጌታችን የተሰቀለበት መስቀል ከተቀበረበት ወጥቷል፡፡ ይህንን የደመራና የመስቀል በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ እኛ አማኞች ሁላችንም መስቀል የማያቋርጥ የእግዚአብሔር ኃይል መገለጫ መሆኑን በማመን በዓሉን ወደ ደመራ ቦታ በመሄድ “መስቀል ከሁሉ በላይ ነው፤ዛሬ መስቀል ከበረ፣ዓለም ለድኅነት ተጠራ፣ሰውም ነጻ ወጣ፡፡” በማለት የቅዱስ ያሬድን ዝማሬ እየዘመርን በታላቅ ድምቀት እናከብረዋለን፡፡ የመስቀሉ ኃይል ጽንዕ ይሁነን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡

“በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፡፡” (መዝ 64÷11)

“በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፡፡” (መዝ 64÷11)


የዘመናት ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር ከዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ አሸጋግሮ እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰን አደረሳችሁ፡፡ ከዓለም በፊት የነበረ ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛ ዓለምንም አሳልፎ የሚኖር ዘመናትን የሚያመላልስ ደቂቃን በሰዓት፣ሰዓትን በዕለት፣ ዕለትን በወር፣ወርን በዓመት የሚጠቀልል ዓመታትንም የሚያቀዳጅ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እርሱ ግን ለዘለዓለም የማይለወጥ መጀመሪያም መጨረሻም የሌለው አልፋና ዖሜጋ ራሱ የሆነ የዘለዓለም አባት ነው፡፡ (ዮሐ 22÷13)

“አንተሰ አንተ ክመ ወዓመቲከኒ ዘኢየኃልቅ” (መዝ 101÷27) አንተ መቼም መቼ አንተ ነህ፤ ዘመንህም ከቶ አይፈጸምም ተብሎ እንደተጻፈ ፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘመን የማይቆጠርለት ዘመናትን ለሰው ልጆች በምሕረቱ ዓመታትን እየባረከ ያቀዳጃል፡፡ የሰው ልጅ ከአባታችን ከአዳም ጀምሮ እስከ አሁን ብዙ ትውልድ እያለፈ ትውልድ እየተተካ ዘመናትም እያለፉ ዘመን እየተተካ ካለንበት ዘመን 2017 ዓመተ ምሕረት ላይ ደርሰናል፤እግዚአብሔር አምላካችን ፍጥረታትን በመግቦቱ ጠብቆ ተራሮችና ኮረብቶችን በዝናብ አጥግቦ ልምላሜን እንደዝናር እንዲታጠቁና አሸብርቀው ደስታን እንዲሞሉ አደረገ፤የሰው ልጅም በንስሐ ተመልሶ የለመለመ ሕይወትን ይኖር ዘንድ በቸርነቱ አዲስ ዓመትን አቀዳጀ፡፡ ስለሆነም በተሰጠን አዲስ ዓመት በኃጢአት የወደቅን ከኃጢአት በንስሐ ተመልሰን፤የተጣላን ታርቀን የተሰጠን የምሕረት ዓመት ነውና ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ (ኤፌ 4÷23)“በአእምሯችሁ መንፈስ ታደሱ”እንዳለ የጽድቅን ሥራ ሠርተን በፍጹም ተለውጠን አዲስ ሰው መሆን ይጠበቅብናል፡፡ አዲስ ዓመት የተቀየረው ለሰው ልጆች ነውና የእግዚአብሔርን ምሕረት በማሰብ ራሳቸንን ለጽድቅ በማስገዛት በንስሐ ታጥበን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን ለመንግሥቱ የተዘጋጀን የምንሆንበት ዓመት ያደርግልን ዘንድ የዘመናት ባለቤት የአምላካችን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

“ጻድቃን ወደ ጌታቸው ሄዱ እንጂ አልሞቱም” ቅዱስ ያሬድ

“ጻድቃንሰ ኢሞቱ ኀበ እግዚኦሙ ነገዱ”
“ጻድቃን ወደ ጌታቸው ሄዱ እንጂ አልሞቱም” ቅዱስ ያሬድ

በ መ/ር ሃፍታሙ ኣባዲ

ከአባታቸው ጸጋ ዘአብ ከእናታቸው እግዚእ ኀረያ በስእለት የተወlዱት ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሕጻንነታቸው ጀምሮ ድንቅ ተአምራትን እያደረጉ ዕውቀትንና ኃይልን ተመልተው በመንፈስ ቅዱስ የጸኑ ቅዱስ አባት ናቸው። ዲቁና ይሾሙ ዘንድ ወደ ጳጳስ በተወሰዱ ጊዜ “ይህ ልጅ የተመረጠ ዕቃ ይሆናል” ተብሎ ትንቢት ተነገረላቸው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስን ምርጥ ዕቃ ብሎ እንደጠራው አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ ጣዖታትን ለማጥፋት፣ ሃይማኖትን ለማጽናት በእግዚአብሔር የተመረጡ ዕቃ ሆኑ። በዚህም ቅዱስ ጳውሎስን መሰሉት። በወጣትነት ዕድሜያቸው አራዊትን ሊያድኑ በሄዱ ጊዜ ጌታችን መልኩ በሚያምር ጎልማሳ አምሳል ተገለጠላቸው። “ወዳጄ አትፍራ ከእንግዲህ ወዲህ የኃጢአተኞችን ነፍስ ወደ ሕይወት የምታጠምድ ትሆናለህ እንጂ አራዊትን የምታድን አትሆንም ስምህ ተክለ ሃይማኖት ይሁን” አላቸው። በዚህም ዓሣ ከማጥመድ በወንጌል መርከብ ለመንግሥተ እግዚአብሔር የሰዎችን ነፍስ ወደ ማጥመድ የተጠራውን ስሙም ከኬፋነት ወደ ጴጥሮስነት የተቀየረውን የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስን መሰሉት።

የጌታን ጥሪ ተቀብለው፣ ገንዘባቸውን ለድሆች ሰጥተው “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል” ብለው ወጡ። (ማቴ. 16፥26) ከሊቀ ጳጳሱም ዘንድ ቅስና ተቀብለው አገልግሎት ጀመሩ። በመላ ኢትዮጵያ እየተዟዟሩ ወንጌልን ሰበኩ። አስተምረው አጠመቁ፤ሕሙማንን ፈወሱ፤ ብዙ ተአምራትን አደረጉ። ጠንቋዮች እና ሟርተኞችን አጠፉ። ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ በጾምና በጸሎት በስግደት ተጠምደው መንፈሳዊ ተጋድሎን ተጋደሉ። በአንድ እግራቸው ለሰባት ዓመት ቆመው እስከ መጸለይ የበረቱ ሆኑ። ብዙ መከራም ተቀበሉ። “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔር ከሁሉ ያድናቸዋል። እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፥ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም።” (መዝ. 33፥19-20) ተብሎ እንደተጻፈ አባታችን ብዙ መከራ ተቀበሉ። እግዚአብሔርም ጠበቃቸው። “እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊልንም እሰጥሃለሁ” (ራእ. 2፥10) የተባለውን ቃል ኪዳን እያሰቡ እስከ መጨረሻ ጸኑ።

ጌታችንም “አንተ በመከራዬ መሰልከኝ እኔም በመንግሥቴ ከእኔ ጋራ እንድትመስለኝ አደርጋለሁ። እነሆ የዚህ ዓለም ድካምህ ተፈጸመልህ በእኔ ዘንድም የምቀበለው ሆነ ከእንግዲህ መንግሥተ ሰማያትን ትወርስ ዘንድ ና።” ብሎ ጠራቸው። በንዳድ በሽታ ጥቂት ታመው ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀን ዕድሜያቸው ነሐሴ 24 ቀን በለመለመ ዕርጅና ዐረፉ። “ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።” ተብሎ የተነገረውን በሕይወታቸው አሳዩ። (ሮሜ. 6፥5)አባታችን ቅዱስ ያሬድ “ጻድቃንሰ ኢሞቱ ኀበ እግዚኦሙ ነገዱ፥ በመንግሥተ ሰማይ ይሁቦሙ ዘፈደቁ” ጻድቃን ወደ ጌታቸው ሄዱ እንጂ አልሞቱም፤ በመንግሥተ ሰማይም የወደዱትን ይሰጣቸዋል፡፡ ብሎ እንዳመሰገነው የጻድቃን ዕረፍታቸው ሕይወታቸው ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ ሕያዋን ናቸው እንጂ ሙታን አይደሉም። “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል።” እንዲል። (ዮሐ. 11፥25) አምላካቸውም የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። (ማቴ 22፥31-32፤ማር 12፥27፤ሉቃ 20፥38) ጻድቃን ከአምላካቸው በተሰጣቸው ቃል ኪዳንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትና በረከትን ያሰጣሉ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት “ስምህን ለሚጠራ፣ መታሰቢያህን ለሚያደርግ፣ ገድልህን ለሚጽፍ፣ ለሚያነበውና ለሚሰማው፣ ቤተ ክርስቲያንህን ለሚሠራ፣ በስምህ መባዕ ለሚሠጥ፣ ለድሆች በስምህ ለሚመጸውት፣ በመታሰቢያህም ቀን ለሚቆርብ ስለ አንተ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሌ እኔ እስከ አሥር ትውልድ እምርልሃለሁ” ብሎ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። እኛም ከዚህ ቃል ኪዳን እንድንጠቀም “የጻድቅ መታሰቢያው ለበረከት ነው” (ምሳ. 10፥7) የሚለውን አምላካዊ ቃል እያሰብን በእምነት በጻድቁ ስም የጽድቅን ሥራ ልንሠራ ይገባናል።

በዓሉ የሰላምና የፍቅር በዓል ይሁንልን፤የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በረከታቸው ይደርብን። አሜን

“የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት”

“የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት”

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የትንሣኤና ዕርገት በዓል አደረሳችሁ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር የኖረችው ስልሣ አራት ዓመት ነው፡፡ ያረፈችው ጥር 21 ቀን ነው፤ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በመደነቅ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ” (ድጓ ዘአስተርእዮ ማርያም) በማለት ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት ገልጿል። ጥር 21 ቀን ጌታችን እልፍ አዕላፋት መላእክትን አስከትሎ መጥቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት እመቤታችንን ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ አሳርፏታል፡፡ በዚህም ዕለት ቅዱሳን ሐዋርያትን በደመና ጠቅሶ ሥጋዋን እንዲቀብሩ አዘዛቸው፤እነሱም ሊቀብሯት ወደ ጌቴ ሴማኒ ይዘዋት በሄዱ ጊዜ አይሁድ  ‹‹ እንደ ልጇ  ‹ ተነሣች፤ ዐረገች ›  እያሉ እንዳያውኩን ኑ ሥጋዋን በእሳት እናቃጥላት ብለው ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ቢጨብጠው የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጣው ከአጎበሩ ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፤በድያለሁ ብሎ በመለመኑ በእመቤታችን ምልጃ እጆቹ ተመልሰውለት እንደነበር ሆኑ፤ ከዚህ በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስንና እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ሐዋርያት ተመልሶ ሲመጣ ሐዋርያት የእመቤታችን የከበረ ሥጋ እንደምን ሆነ አሉት? ከገነት ዕፀ ሕይወት ሥር መኖሩን ነገራቸው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም ቅዱስ ዮሐንስ ያየውን ያዩ ዘንድ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ሁለት ሱባኤ ሲፈጸም ማለትም ነሐሴ 14 ቀን ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ ሥጋ ለሐዋርያት ሰጣቸው እነሱም በታላቅ ዝማሬ ወስደው በጌቴ ሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ ነገር ግን እመቤታችንን ሲቀብሯት ቅዱስ ቶማስ አልነበረምና በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› (መዝ. 131፥8) ብሎ ትንቢት የተናገረው ተፈጽሞ በሦስተኛውም ቀን “ከመ ትንሣኤ ወልዳ” እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ቅዱስ ቶማስም ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ አሁንም የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ብሎ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ሊወድቅ ወደደ እመቤታችን አትዘን ብላው ሌሎች ሐዋርያት ትንሣኤዋንና ዕርገቷን እንዳላዩ ነግራው አንተ አይተሃል ሄደህ ተነሣች ዐረገች ብለህ ንገራቸው ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ልካዋለች፡፡ከዚያም የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ ቢላቸው ቀበርናት አሉት፡፡ እሱም “ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር አይደረግም” አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ መጠራጠር ልማድህ ነው ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንም ብሎ ወደ መካነ መቃብር ሄደው መቃብሩን ቢከፍቱት አጧት ደነገጡ፤ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ ዐርጋለች ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው ሰበኑንም ሰጣቸው ለበረከትም ተካፈሉት በሰበኑም ሕሙማንን ሲፈውሱበት ገቢረ ተአምራት ሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆን በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው ልብስ፤ አባቶች ካህናት የሚጠመጥሙት ሻሽና በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ልብስ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን መምህራን ያስተምራሉ፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም በዓመቱ ቅዱስ ቶማስ ትንሣኤሽንና ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ ብለው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በነሐሴ 16 ቀን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የለመኑትን የማይነሳ ነውና እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ (ረዳት) ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሠናይ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡እመቤታችንን ሐዋርያት በግልጽ እያዩዋት ከጌታችን ጋር በክብር በይባቤና በዝማሬ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህንን መታሰቢያ በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን ምልጃ የሐዋርያት በረከት አይለየን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር!

አምናለሁ አትቀሪም

አምናለሁ አትቀሪም

/በ ሃይማኖት ተካ/

የታደለ ድንጋይ በአምላክ ተቀድሶ ታቦት ያሳድራል፤
ስሙ ተቀይሮ እየተሳለምነው ከብሮ ያስከብራል፤
የረገጥነው አፈር የተደገፍነው ግንድ ልጅሽ ከወደደ፤
ዘግነን ተቀብተን ቆርጠንም አጭሰን መዳኛ ይሆናል
እሱ ከፈቀደ::

ርግበ ጸዓዳ ሀገረ ክርስቶስ ቤተ ሃይማኖቴ፤
የመማጸኛዬ ቃልና ቀለሜ የምታረቅብሽ ርቱዕ አንደበቴ::
ነያ ሠናይት ጎትተሽ ውሰጂኝ አቅርቢኝ ከደጁ
ነያ ዕፀ ሕይወት ከበሩ አዝልቂኝ አስዳሺኝ በእጁ::
እንደተራራቁት እንደኒያ ድንጋዮች እንደታነጹብሽ፤
እጠብቅሻለሁ አንድ እስክታደርጊኝ አማልደሽ ከልጅሽ::
አምናለሁ አትቀሪም. . .

እንደሚለመልም ሰም እሳት ሲያቀልጠው፤
በስምሽ ተጠርቶ ድንጋዩ ተስቦ በእጅ በታነጸው::
ከምሥጢር እንዳንጎድል በቤተ መቅደሱ ተሰብስበንበት፤
በተሠራልን ልክ አውቀን እንድንኖር እንድንበቃበት፤
ነይ እመብርሃን ቦዶነታችንን ፍቅርሽን ሙይበት::
አምናለሁ አትቀሪም::